የአሜሪካ የዲሞክራት ፓርቲ እጩ በርኒ ሳንደርስን ልዩ የሚያደርጓቸው 18 ነጥቦች

በርኒ ሳንደርስ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በርኒ ሳንደርስ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት

ሽማግሌው በርኒ የቬርሞን ግዛት ሴናተር ናቸው። 78 ደፍነዋል። ቢሆንም ድጋፋቸው በዋናነት የሚመነጨው ከወጣቶች ነው። እርሳቸውም መወዳደር አይሰለቻቸውም። እነሆ የ2ኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ ለክፍል አለቅነት መወዳደር የጀመሩ ዛሬም ድረስ እንደተወዳደሩ አሉ።

እስካሁን በዲሞክራቶች የዕጩ ፉክክር በለስ እየቀናቸው ይመስላል።

ባለፈው ምርጫ ጥሩ ሄደው ሄደው በሂላሪ ተረ'ተው ነበር። ዘንድሮ ከጆ ባይደን፣ ማይክ ብሉምበርግ እና ኤልዛቤት ዋረን ጋር አንገት ላንገት ተናንቀዋል።

የበርኒ ግራ ዘመም የፖለቲካ ዝንባሌያቸው ለአንዳንድ አሜሪካዊያን ግራ ነው። ለመሆኑ ሳንደርስ ምን ልዩ ያደርጋቸዋል?

18 ነጥቦችን ከታች ዘርዝረናል። ከዚያ በፊት ግን በአንድ አንቀጽ የአጭር አጭር የሕይወት ታሪካቸውን ብንነግራችሁስ?

በርናርድ ሳንደርስ የተወለዱት በፈረንጆች በ1941 በብሩክሊን፤ ኒውዮርክ ነው። ከመካከለኛም ዝቅ ያለ ገቢ ከነበረው የአይሁድ ቤተሰብ ነው የተገኙት። አባታቸው አይሁዶች ላይ ከተቃጣው የያኔው ጭፍጨፋ አምልጠው ነው ከፖላንድ በ17 ዓመታቸው ቤሳ ቤስቲን ሳይዙ በስደት ወደ አሜሪካ የገቡት።

የበርኒ አብዛኛው ቤተሰባቸው በናዚ ተጨፍጭፎ አልቋል። ሳንደርስ ለአጭር ጊዜ አናጢም፣ አስተማሪ ሆነው ሠርተዋል። ወደ ቨርሞንት ግዛት ከሄዱ በኋላ የበርሊንግተን ከተማ ከንቲባ ሆነዋል። ተወዳጅ ከንቲባ ነበሩ፤ አራት ጊዜ ተመርጠው 8 ዓመት አገልግለዋል።

ሌላው አስገራሚ ነገር በርኒን ወደ ፖለቲካ የሳባቸው ሰው አዶልፍ ሂትለር መሆኑ ነው። አንድ ሰው በፖለቲካ ይህን ያህል አደጋ ሊያደርስ ከቻለ በበጎም ተጽእኖ ማሳደር ይችላል የሚል እምነት አጎልብተው ነው በርኒ ወደ ፖለቲካ የተወሰወሱት።

እነሆ በቀጥታ ወደ 18ቱ ነጥቦች።

  • ግራ ዘመምነታቸው፦ "እኔ የዲሞክራት ሶሻሊስት ነኝ" እያሉ አፋቸውን ሞልተው ይናገራሉ፤ ሳንደርስ። ይህ የፖለቲካ ግንዛቤ ለሌላቸው አብዛኞቹ አሜሪካዊያን "እኔ አሸባሪ ነኝ" ከማለት እምብዛምም አይለይ ይሆናል። ሳንደርስ ብዙ ደክመዋል፤ ዲሞክራቲክ ሶሻሊስት መሆን ምን ማለት እንደሆነ ለማስረዳት። ሳንደርስ ሶሻሊስት ነኝ ሲሉ ምን ማለትዎ እንደሆነ በአጭሩ ያስረዱን ተብለው ነበር በአንድ ወቅት። "ዲሞክራቲክ ሶሻሊዝም ማለት እጅግ ሃብታሞችን የበለጠ ሀብታም ማድረግ ቀርቶ ድሀውንም የሚጠቅም ኢኮኖሚን መፍጠር ነው።" ሲሉ መልሰዋል።
  • የአየር ንብረት ለውጥ ቀልድ አይደለም፦ ሳንደርስ እንደ ትራምፕ የአየር ንብረት ለውጥ ብሎ ነገር "ጭቦ ነው" ብለው አይሳለቁም። እንዲያውም ይህንኑ ለመቀልበስ 16 ትሪሊየን ዶላር እንዲመደብ ሐሳብ አቅርበዋል። አዲሱ "አረንጓዴው ቃል ኪዳን" በሚሉት በዚህ ምክረ ሐሳብ 20 ሚሊዮን አዳዲስ የሥራ ዕድሎች በቀጣዮቹ 15 ዓመታት ይፈጠራሉ።
  • ረ ሕዝብ በዛ! ፦ ሳንደርስ የቤተሰብ ምጣኔ ደጋፊ ናቸው። ጽንስን ለማቋረጥ ለሚሹ አቅርቦት ለማድረስ፣ በድሀ አገራት የወሊድ መከላከያን ለማበረታታት እሰራለሁ ይላሉ።
  • ትምህርት በነጻ፦ የኮሌጅ ትምህርት ለዜጎች መብት መሆን አለበት የሚሉት ሳንደርስ አሁን ግን ለሃብታሞች ብቻ የተሰጠ ገጸ በረከት ሆኗል ሲሉ ይተቻሉ። 45 ሚሊዮን አሜሪካዊያን ለትምህርት የወሰዱትን ብድር ቢሰሩዙ ደስታቸውን አይችሉትም፤ በርኒ።
  • የመሣሪያ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግ፦ "ዓለም እየተለወጠ ነው፤ የኔም አስተሳሰብ እንዲሁ" አሉ በርኒ በኒውሃምሻየር በነበረ የእጩዎች የክርክር መድረክ። ከጦር መሣሪያ ጋር በፍቅር ከወደቀችው ቬርሞን ግዛት የመጡት ሳንደርስ አሁን በጦር መሣሪያ አያያዝ ላይ ያላቸው ጥብቅ አቋም መላላቱ ለብዙዎች አስገራሚ ነው። የጦር መሣሪያ ባለቤት ለመሆን የሚሻ ሰው ጀርባው ይጠና ይላሉ ሳንደርስ።
በርኒ ሳንደርስና ባለቤታቸው ጄን ኦሜራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

6. የጥቁሮች ጉዳይ ያገባኛል፦ ሳንደርስ በአሜሪካ ጥቁሮች ላይ የሚደርሰው በደል የመደብ እንጂ የቀለም ጉዳይ አይደለም ብለው ያምኑ ነበር። አሁን ግን የጥቁሮች ሕይወት ግድ ይለኛል! ("ብላክ ላይቭስ ማተር") የሚለው እንቅስቃሴ መሥራቾች በርኒን ድጋፍ እየሰጧቸው ይገኛሉ። በርኒ ሳንደርስ በባርነት ለተሰቃዩ አፍሪካ-አሜሪካዊያን የልጅ ልጆች ካሳ ይገባቸዋል የሚለውን ሐሳብ ከዚህ ቀደም አጣጥለውታል። ሆኖም ባለፈው ዓመት በባሪያ ንግድና ብዝበዛ አሜሪካ በጥቁሮች ላይ ያደረሰችውን በደል የሚያጠና ኮሚሽን እንዲቋቋም ድጋፍ እንደሚሰጡ ሳንደርስ ተናግረዋል። የሚገርመው ሳንደርስ ወጣት ሳሉ ማርቲን ሉተር ኪንግ በሚያዘጋጃቸው ሰልፎች ይሳተፉ ነበር። የጥቁሮችን መገለል በመቃወማቸውም ፖሊስ አስሯቸው በ25 ዶላር ነው በዋስ የወጡት።

7• ከእያንዳንዱ እጩ ጀርባ ቢሊየነሮች ለምን?፦ የአሜሪካ ምርጫ ሚሊዮን ብቻ ሳይሆን ቢሊዮን ዶላሮች ሳይዙ የሚወጡት ዳገት አይደለም። ከብዙ እጩዎች ጀርባ ትልልቅ ኮርፖሬሽኖች ያሉትም ለዚሁ ነው። በርኒ ግን ታች ካለው ማኅበረሰብ በሚገኝ መዋጮ ነው ለጊዜው እየተነፈሱ ያሉት ማለት ይቻላል። ገንዘቡን የሚሰበስብላቸው "አወር ሪቮሉሽን" የሚባል ለትርፍ ያልቆመ ፖለቲካ ድርጅት አላቸው። ሆኖም ገንዘቡን የሚያዋጡላቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር ይፋ ባለማድረጋቸው በርኒ አልፎ አልፎ ይተቻሉ።

8• ዝቅተኛ ክፍያ በሰዓት 15 ዶላር ይሁን፡ አሁን አሜሪካ በፌዴራል ደረጃ ዝቅተኛው ክፍያ በሰዓት 7.25 ዶላር ነው። በርኒ ግን 15 ዶላር እንዲሆን ይሻሉ። የምጣኔ ሐብት ጠበብቶች ግን እጥፍ ጭማሪ ቢደረግ ትንንሽ ከተሞችንና ትንንሽ ቢዝነሳቸውን ጨርሶውኑ ይገድላል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

9• ሁለት ግዙፍ ፓርቲ ብቻ ለምን? በርኒ ሳንደርስ ሴናተር የሆኑት በግል ተወዳድረው ነው። አሜሪካ በሪፐብሊካንና በዲሞክራቶች የፖለቲካ ጫፍ መወጠሯ ከድሮም ጀምሮ ምቾት አይሰጣቸውም። ዲሞክራቶችና ሪፐብሊካን በኮርፖሬሽን ገንዘብ ጫንቃ ላይ ነው ያሉት፤ በውለታ ይታሰራሉ፤ በእከክልኝ ልከክልህ የሚሰሩ ፓርቲዎች ሆነዋል ሲሉም ይተቻሉ።

10• የድሆች አባት፦ በርኒ ሳንደርስ የድሆች አባት የሚል ቅጽል ይሰጣቸዋል። በገንዘብ ብክነት አይታሙም። አውሮፕላን ሲሳፈሩ እንኳ ቢዝነስ ክፍል ንክች አያደርጉም ይባላል። ከሕዝብ ጋ ተሰልፈው እንደ ተራ ተሳፋሪ በጭቁን የኢኮኖሚ ክፍል አውሮፕላን ሲበሩ የሚያሳዩ ምሥሎች አሉ። አንድ ቀን ግን ቢዝነስ ክፍል ተንፈላሰው ታይተው "ምነው በርኒ? ምነው ምነው?" ተብለዋል።

11. የጤና መድህን ለሁሉም፦ ሳንደርስ ሁሉም አሜሪካዊ ተጠቃሚ የሚሆንበት መንግሥታዊ የጤና መድህን ሊዘረጋ ይገባል፤ መብትም ነው ሲሉ ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ። ለዚህም 30 ትሪሊዮን ዶላር ያስፈልገናል ብለው ተነስተዋል።

12. የአሜሪካ መሠረተ ልማት ላሽቋል፦ በርኒ ሳንደርስና ትራምፕ አንድ የሚያመሳስላቸው ነገር አለ ከተባለ ይህ ነው የሚሆነው። አሜሪካ መሠረተ ልማቷን ማደስ አለባት፤ ለዚህም አንድ ትሪሊዮን ዶላር ያስፈልገናል ይላሉ።

13• ከሀብታሞች ግብር መሰብሰብ፦ ባርኒ ሳንደርስ ሀብታቸው ከ32 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሆኑ ዲታዎች ጫን ያለ ግብር እንዲከፍሉ ይፈልጋሉ። በዎልስትሪት የስቶክ ገበያ ዝውውር ላይ አዲስ ግብር እንዲጣልም ይፈልጋሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን ሥራ ያላቸው ዜጎችም ላይ መጠነኛ ግብር እየተጣለ የጤና መድህን አቅርቦትን ለማገዝ ያልማሉ።

14• ጦርነት ሱስ ሆኖብናል፦ በርኒ ሳንደርስ ድሮም ቢሆን የቬትናም ጦርነትን ይቃወሙ ነበር። አሜሪካ በማያገባት እየገባች ጦርነት ውስጥ መማገዷ ይብቃ ብለው የተነሱት ዛሬ አደለም። በፈረንጆቹ 2002 የአሜሪካ ኢራቅን መውረር ያበሳጫቸው ነበር። ያኔም ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያነሱ ነበር። ኢራቅን መውረራችን በአሜሪካ ታሪክ እጅግ አሳፋሪው የውጭ ፖሊሲ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

የሳንደርስ ደጋፊዎች የሰውየውን ጨብራራ ጸጉር መለያቸው አድርገውታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የበርኒ ሳንደርስ ደጋፊዎች የሰውየውን ጨብራራ ጸጉር ልዩ መለያቸው አድርገውታል

15. መቆነጃጀት ጊዜ ማባከን ነው፦ ሳንደርስ ለአለባበሳቸው ግድ የሌላቸው ሰው ናቸው። ባለቤታቸው እንዳውም ሲቀልዱባቸው "ምን እሱ'ኮ ሦስት ሹራብ ቢኖረው ራሱ ብዙ ነው ይላል" ብላቸዋለች። ደጋፊዎቻቸው የበርኒ ሳንደርስ መልክ ያልያዘ ጸጉር ቲሸርቶቻቸው ላይ እየሳሉ ለርሳቸው ያላቸውን ፍቅር ይገልጻሉ። በርኒ ጸጉሩዎትን ለምን ያንጨበርራሉ ሲባሉ፡ "ምናገባችሁ? ሚዲያዎች ስትባሉ እዚህ ግባ በማይባል ጉዳይ ጊዜያችሁን ታጠፋላችሁ፤ ስለኔ ጨብራራ ጸጉር ከምታወሩ አሜሪካንን የሚያህል ታላቅ አገር ስለምን የጤና መድህን ላይኖራት ቻለ ብላችሁ አትጠይቁም??" ሲሉ ተሰምተዋል።

16. የፊደል ካስትሮ አድናቂ? በጥቅምት ወር ሳንደርስ በሲቢኤስ ላይ ቀርበው ሁሉም አምባገነን መጥፎ ነው ማለት አይቻልም የሚል አነጋጋሪ አስተያት ሰጥተዋል። የኩባ አብዮት ሁሉም ነገሩ ስህተት ነው ብሎ መናገር አይቻልም ሲሉ ተናግረዋል። ተቺዎቻቸው ታዲያ ታሪክ ጉርጉረው አወጡባቸው። በ1980ዎቹ በቬርሞን ግዛት የበርሊንግተን ከንቲባ ሳሉ የኒካራግዋ ሶሻሊስት መሪ ዳንኤል ኦርቴጋን "ድንቅ ሰው ነው" ብለው ተናግረው ነበር። ኦርቴጋ ያደርስ የነበረውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ቸል በማለታቸውም ክፉኛ ተችተዋቸዋል

17• እነ ፌስቡክና አማዞን 'አንድ ሊባሉ ይገባል'፦ በርኒ ሳንደርስ ጡንቻቸው የፈረጠሙ አይነኬ ኮርፖሬሽኖች ምቾት አይሰጧቸውም። ኤልዛቤጥ ዋረንም እንደርሳቸው ናት። እነ አማዞን፣ ፌስቡክ እና ጉግል ነገሩን ሁሉ ተቆጣጥረውት "እግዜሩን" ሊሆኑ ምን ቀራቸው? ይላሉ። ስለዚህ ሕግና ደንብ ተበጅቶላቸው፣ ሜዳው ለውድድር ክፍት ሊሆን ይገባል፤ ለነፌስቡክም ልጓም ይበጅ ሲሉ ይሟገታሉ።

18• እስራኤል 'ታበዘዋለች'፦ "በአይሁድነቴ እጅግ ብኮራም..." እስራኤል ግን ዘረኛ ሆናለች፤ አሁን በሥልጣን ያሉትም ሰዎች ጨቋኝ ናቸው ሲሉ ይተቻሉ። ለዚህ ምላሽ የሰጡት የእስራኤሉ ናታንያሁ 'በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ አልገባም' ሲሉ ተናግረዋል።

በርኒ ሳንደርስ ቀንቷቸው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመርያው አይሁድ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ።