የአንጎላ አማፂ ቡድን መሪ ከሞቱ ከ17 ዓመታት በኋላ ድጋሚ ተቀብረዋል

የአንጎላ አማፂ ቡድን መሪ ጆናስ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ዩኒታ የተሰኘው የአንጎላ አማፂ ቡድን መሪ የነበሩት ጆናስ ሳቪምቢ ከሞቱ 17 ዓመታት ቢሆናቸውም ከሰሞኑ እንደ አዲስ ግብዓተ መሬታቸው ተፈፅሟል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ፀዓዳ የለበሱ የአማፂ ቡድኑ አባላት የቀድሞ መሪያቸውን ዳግማዊ ግብዓተ መሬት ሲያደምቁት ታይተዋል።

የእርስ በርስ ጦርነት ሲያምሳት የነበረችው አንጎላ ከጆናስ ሞት በኋላ ወደ ቀልቧ የተመለሰች መሰለች፤ ሰውዬው የሞቱት በግሪጎሪሳውያን አቆጣጠር 2002 ላይ ነበር።

የጆናስ አፅም ከ17 ዓመታት በኋላ ለቤተሰቦቹ ተሰጥቷል። የዩኒታ አባላትም የመሪያቸው ዳግመኛ መቀበር ለሃገራዊ መግባባት ይረዳል ሲሉ ተሰምተዋል።

ኤኤፍፒ የተሰኘው የዜና ወኪል አንድም የመንግሥተ መሪ በሥርዓተ ቀብሩ ላይ እንዳልተገኘ አስተውያለሁ ሲል ዘግቧል።

የአንጎላ እርስ በርስ ጦርነት ለ27 ዓመታት ሲዘልቅ ቢያንስ ግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ እንደቀጠፈ ይነገርለታል።

'ጥቁሩ አውራ ዶራ' በተሰኘ ቅፅል ስሙ የሚታወቀው ጆናስ ለበርካቶች እንደ ጠንካራ መሪ ቢታይም ጨካኝ ነበር የሚሉ አልጠፉም።

2002 ላይ ነበር የመንግሥት ወታደሮች ጆናስን ከገደሉት በኋላ በፍጥነት አፈር እንዲለብስ ያደረጉት።

የጆናስ ቤተሰቦችም ሆኑ የአማፂ ቡድኑ አባላት መሪያቸው አፅሙ ወጥቶ ድጋሚ እንዲቀበር መንግሥትን ለዓመታት ሲጎተጉቱ ከርመዋል።

ከጆናስ ጋር ዓይንና ናጫ የነበሩት የአንጎላው ፕሬዝደንት ኤድዋርዶ ዶስ ሳንቶስ 2017 ላይ ከሥልጣን መውረዳቸው የአማፂ ቡድኑ አባላት ጉትጎታ እንዲሰማ አስተዋፅኦ ሳያደርግ እንዳልቀረ ይነገራል።