በኤርትራ የሰለጠኑ ከ5 ሺህ በላይ የሶማሊያ ወታደሮች ወደ አገራቸው የመመለሳቸው ጉዳይ

ልጆቻችን የት ደረሱ ብለው የተቃወሙ የሶማሊያ እናቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኤርትራ ውስጥ የሰለጠኑ ቢያንስ 5 ሺህ የሶማሊያ ወታደሮች በቅርቡ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ አረጋገጡ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ምክር ቤት መጋቢት ወር ላይ ባወጣው ሪፖርት በኤርትራ የሰለጠኑ የሶማሊያ ወታደሮች ከኤርትራ ወታደሮች ጋር በመሆን በትግራይ ጦርነት መሳተፋቸውን ይፋ አድርጎ ነበር።

በኤርትራ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ያተኮረው ሰነዱ በሥልጠና ላይ የነበሩ የሶማሊያ ወታደሮች ወደ ትግራይ ጦር ግንባሮች መወሰዳቸውንና እንዲሁም በአክሱም እንደነበሩ የሚገልጹ መረጃዎችን ይዟል።

የሶማሊያ መንግሥት በኤርትራ ምንም አይነት የሶማሊያ ወታደሮች የሉም ሲል የቆየ ቢሆንም በኋላ ግን ኤርትራ ውስጥ ወታደሮች መኖራቸውን አምኗል።

ሆኖም በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ አልተሳተፉም ሲል ያስተባበለ ሲሆን ኤርትራም በበኩሏ የሶማሊያ ወታደሮችን አሰልጥናለች፣ በትግራይ ጦርነት አሳትፋለች የሚለውን ክስ ውድቅ አድርጋዋለች።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በጦርነቱ የሶማሊያ ሠራዊት ተሳትፏል መባሉን ሐሰት ነው ማለቱ የሚታወስ ነው።

ትናንትና ግንቦት 15/2014 ዓ.ም በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ በተካሄደው የሥልጣን ርክክብ ወቅት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ በኤርትራ ሥልጠና የወሰዱ 5 ሺህ ወታደሮች መኖራቸውን አምነዋል።

ለአምስት ዓመታት አገሪቷን ሲያስተዳድሩ የቆዩት ፋርማጆ ወታደሮቹ በኤርትራ የነበራቸውን ሥልጠና ባለፈው ዓመት ቢያጠናቅቁም ሶማሊያ ውስጥ ባለው ፖለቲካዊ ሁኔታ እና በምርጫ ላይ ተጽእኖ እንዳያሳድሩ በመስጋት የመመለሳቸው ሁኔታ መጓተቱቱን ተናግረዋል።

በሥልጣን ርክክቡ ወቅት ፋርማጆ የወታደሮቹን ፋይል ለአዲሱ መሪ ሐሰን ሼይክ መሐሙድ ተላልፎ መሰጠቱን አረጋግጠዋል።

አገሪቷን ከዚህ ቀደም ከአውሮፓውያኑ 2012 እስከ 2017 የመሩት አዲሱ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼይክ መሀሙድ በበኩላቸው በኤርትራ የሰለጠኑ የሶማሊያ ወታደሮች ወደ ወደ አገራቸው በአፋጣኝ እንደሚመለሱና "አገሪቱን ነጻ ለማውጣት እንደሚሰሩ" መናገራቸውን የሶማሊያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የሶማሊያ ወታደሮች በጦርነቱ ተሳትፈዋል?

ወታደሮቹ በ2019 ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኤርትራ የተላኩ መሆናቸውን ሪፖርቶች ያመላከቱ ሲሆን ወታደሮቹ ሶማሊያን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት ኳታር እንደሚመደቡ ተነግሯቸው ነበር ተብሏል።

ወደ ኤርትራ ለውትድርና ሥልጠና የተላኩ ሶማሊያውያን ወታደሮች በትግራይ ጦርነት ተሳትፈዋል የሚለውንም ሪፖርት ተከትሎ የሶማሊያውያን ወላጆች በተለይም እናቶች "ልጆቻችንን የት ናቸው? ልጆቻችንን አምጡ" በሚል በሞቃዲሾ እና በሌሎች ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውን የሶማሊያው ጋሮው ኦንላይንን ጨምሮ ሮይተርስ፣ ግሎብ ኤንድ ሜይልና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘገባዎች ያሳያል።

እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ የሶማሊያ ወታደሮች በትግራይ ጦርነት መሰማራታቸውን ግሎብ ኤንድ ሜይል የቀድሞ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን ዋቢ አድርጎ የዘገበ ሲሆን በዚሀም በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች መሞታቸው ተነግሯል።

በዚህም ዘገባ ላይ የሶማሊያ ወታደሮች በኤርትራ ጦር ቁጥጥር ስር ባሉ የትግራይ ክልል መንደሮች ንጹሃን ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ እንደጨፈጨፉ የተረፉ የዓይን እማኖችን ዋቢ አድርጎ አካቷል።

ሮይተርስ ያናገራቸው አሊ ጂማክ ዱዲ የተባሉ አባት የሚያውቁት ልጃቸው ኳታር ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ በጥበቃ ሠራተኝነት ይሰራ እንደነበር ሲሆን፣ የሶማሊያ የብሔራዊ መረጃ ኤጀንሲ ባለሥልጣናት 10 ሺህ ዶላር ሰጥተዋቸዋል።

ልጃቸው መሞቱንና በኳታር ሳይሆን በኤርትራ እንደሞተም መረዳታቸውን ተናግረዋል። በርካታ ወላጆችም ልጆቻቸው የት እንዳሉ እንደማያውቁ ለሮይተርስ አስረድተዋል።

የኳታር የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ "ወደ ኳታር ለሥራ ዕድል የተባለው ሐሰተኛ ምልመላንም ሆነ በውሸት ብዝበዛ" እንደሚያወግዝ ገልጾ፣ እንደዚህ አይነት ጥሰቶች ላይ ምርመራ እንዲከፈት መጠየቁም ተዘግቧል።

የሶማሊያ መንግሥት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የውስጥ ፖለቲካ ነው በሚል በትግራይ ጦርነት አልተሳተፍኩም ሲል ማስተባበሉን ሮይተርስ ዘግቦ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት የሶማሊያ ወታደሮች በጦርነቱ ተሳትፈዋል የሚለውን ሪፖርትን ተከትሎ ኤርትራ ቅሬታዋን ለድርጅቱ በደብዳቤ አሳውቃ ነበር።

የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በፃፉት ደብዳቤ "አሜሪካ ህወሓትን በመደገፍ እና በአካባቢው ጣልቃ በመግባት እንዲሁም በማስፈራራት ተጨማሪ ግጭት እንዲፈጠር አድጋለች" ሲሉ መወንጀላቸውን ሮይተርስ መጋቢት ወር ላይ ይዞት የወጣው ሪፖርት ያሳያል።

በትግራይ ጦርነት ተሳታፊ የሆነችው ኤርትራ ጦሯ ጅምላ ግድያ፣ መድፈርን ጨምሮ እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ መጠነ ሰፊ ጥሰቶች ፈፅሟል ሲሉ የተባባሩት መንግሥታትና አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ ሰብዓዊ መብት ተቋማት ተደጋጋሚ ሪፖርቶችን አውጥተዋል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

በትግራይ 400 ሺህ ሕዝብ የሚሆን በረሃብ አፋፍ ላይ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችም አስቸኳይ የምግብ እና መድኃኒት እርዳታም ይሻሉ ተብሏል።

በኢትዮጵያ መንግሥትና በትግራይ ኃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎ ለአስራ ስምንት ወራት የዘለቀው ጦርነት መቋጫ ሊሆን ይችላል የሚል ተስፋን ዘርቶ የነበረ ቢሆንም ከሰሞኑ ዳግም ጦርነት ይከሰት ይሆን የሚሉ ፍንጮች ጥያቄ ፈጥረዋል።

ለዚህም እንደ ማሳያ የሚሆኑት ከኤርትራ፤ ከትግራይና ከአማራ ክልሎች የተሰሙ መግለጫዎች እንዲሁም በድንበሮች አካባቢ አልፎ አልፎ ተከስተዋል የተባሉ ግጭቶች ናቸው።

ከሰሞኑ የኤርትራ መንግሥት በማስታወቂያ ሚኒስቴሩ በኩል ባሰፈረው መልዕክት ህወሓት በኤርትራ ድንበር በኩል እና በምዕራብ ትግራይ አቅጣጫ በሁለት ግንባሮች ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጀ ነው ብሎ ነበር።

ለዚህም ከትግራይ አመራሮች በኩል በተሰጠው ምላሽ ኤርትራ በጦርነቱ በርካታ ጥሰቶችን እንደፈጸመችና እንዲሁም የትግራይን ግዛቶች ተቆጣጥራ እንደምትገኝ ጠቅሰው በሰላምም ይሁን በሌላ መንገድ ከእነዚህ ግዛቶች ነጻ ይወጣሉ ብለዋል።

የፌደራል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ከሰሞኑ ከሰሞኑ ህወሃት ለጦርነት በይፋ እየተዘጋጀ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን ከሰሞኑ ደግሞ የአማራ ክልል ከህወሓት በኩል ሊሰነዘር ይችላል ላለው ሌላ ዙር ወረራ የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ዝግጁ እንዲሆን ትዕዛዝ አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራል መንግሥት ኃይሎች መካከል ውጥረት እየጨመረ መምጣቱ እንዲሁም አልፎ አልፎም ግጭቶች ሪፖርት መደረጋቸው እንዳሳሰበው ገልጾ ነበር።