የሶማሊያ አዲስ ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት በሰኔ ወር ይጠበቃል

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ቤተ መንግሥት ገብተዋል፡፡ ሥራ ጀምረዋል፡፡
ነገር ግን ይፋዊ በዓለ ሲመት ገና አልተደረላቸውም፡፡
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይኽ መሐሙድ ወደ ሥራ የገቡት በፓርላማ አባላት ድምጽ ባገኙ በሳምንቱ ነበር፡፡
ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ (ፋርማጆ) ሥልጣናቸውን ያስረከቡትም ወዲያውኑ ነበር፡፡
አሁን በቪላ ሶማሊያ ቤተ መንግሥት የሚገኙት አዲሱ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይኽ መሐሙድ ናቸው፡፡
የሥልጣን ርክክቡ በሞቃዲሾ ሲደረግ ሥነ ሥርዓቱ ለሕዝብ በብሔራዊ ቴሌቪዥን በቀጥታ ተላልፏል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሕዝብ ተወካዮች እና የታችኛው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እንዲሁም የጦር ኃይሎች አባላትም ተገኝተዋል፡፡
ይሁንና ይፋዊ በዓለ ሲመት ሥነ ሥርዓቱ ገና በሚቀጥለው የፈረንጆች ሰኔ ወር ላይ ነው የሚደረገው፡፡
በሥልጣን ርክክቡ ወቅት ፋርማጆ ሶማሊያዊያን ከአዲሱ ፕሬዝዳንት ጋር በትብብር መንፈስ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አዲሱ ፕሬዝዳንት በበኩላቸው በመቶዎቹ የመጀመርያ ቀናት ዋንኛ አጀንዳዎቻቸው የሶማሊያን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ ብሔራዊ እርቀ ሰላም ማውረድና አገሪቱ ከተዘፈቀችበት ዕዳ ማውጣት ይሆናል ብለዋል፡፡
አዲሱ ፕሬዝዳንት መሐሙድ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ የመጀመርያቸው አይደለም፡፡
ከዚህ ቀደም በፈረንጆቹ ከ2012 እስከ 2017 አገሪቱን መርተዋል፡፡












