የሩሲያው ዲፕሎማት የዩክሬንን ጦርነት በመቃወም ሥራ ለቀቁ

ቦሪስ ቦምዳሬቭ

የፎቶው ባለመብት, BORIS BONDAREV

ቦሪስ ቦምዳሬቭ የተባሉ የሩሲያ ዲፕሎማት በዩክሬን ያለውን ጦርነት በመቃወም ሥራቸውን መልቀቃቸውን ገለጹ።

"ፑቲን ዩክሬን ላይ የከፈተውን ደም አፋሳሽ ጦርነት እቃወማለሁ" ብለዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በጄኔቫ፣ በተባበሩት መንግሥታት የሩሲያ ልዑክ መሆናቸው ተጽፏል።

ሥራ ለመልቀቅ መወሰናቸውን ለቢቢሲ ያረጋገጡት ዲፕሎማቱ "ሩሲያ ከእንግዲህ ወዲያ እንደ ባንዳ ነው የምትቆጥረኝ" ብለዋል።

ጦርነቱ "የዩክሬን ሕዝብ ላይ እና የሩሲያ ሕዝብ ላይ የሚፈጸም ወንጀል" ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

ሩሲያ "ልዩ ወታደራዊ ኦፕሬሽን" ስትል የምትጠራውን ይህን ጦርነት የሚቃወሙ ወይም የሚተቹ ሰዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ ትወስዳለች።

ሆኖም ግን ዲፕሎማቱ የ20 ዓመት ሥራቸውን ለማቆም መወሰናቸውን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ለሙያ አጋሮቻቸው ባቀረቡት ደብዳቤ አስታውቀዋል።

"ከዚህ በኋላ የዚህ ረብ የለሽ፣ ደም አፋሳሽ ጦርነት አካል መሆን አልፈልግም። ይህንን ጦርነት ያስነሱት ሰዎች አላማ ሥልጣን ላይ መቆየት ብቻ ነው። ሕልማቸውን ለማሳካት የብዙዎችን ሕይወት ለመቅጠፍ ዝግጁ ናቸው። ዘንድሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሩሲያውያን እና ዩክሬናውያን ሞተዋል።"

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቭሮቭ በደብዳቤው ወቀሳ ቀርቦባቸዋል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከዲፕሎማሲ ይልቅ "በውሸትና ጥላቻ" ተበርዟል ሲሉም ተችተዋል።

የሩሲያ ባለሥልጣን እንደዚህ አመራሩን ሲተች መስማት አልተለመደም።

ይህንን ጦርነት ላለፉት ሦስት ወራት የሚደግፉ እንጂ የሚነቅፉ የሩሲያ ድምጾች ብዙም አይደሉም።

አሁንም አንድ ዲፕሎማት ሥራቸውን በመልቀቃቸው ብቻ ሌሎችም ይከተሏቸዋል ማለት ላይሆን ይችላል።

እኚህ ዲፕሎማት "ለውጥ ይመጣል ብዬ አላምንም። ነገር ግን ትልቁን ግንብ የሚገዳደር ትንሽ እርምጃ ነው" ብለዋል።

የሙያ አጋሮቻቸው ሩሲያ ዩክሬንን በመውረሯ ደስተኛ እንደሆኑ ሳይናገሩም አላለፉም።

ሆኖም ግን በጦርነቱ ሳቢያ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ሲያጋጥም ጦርነቱን የሚደግፉ የሩሲያ ባለሥልጣኖች ጥርጣሬ እንደገባቸው ገልጸዋል።

"አብዛኞቹ እንደ መጀመሪያው ጊዜ ነውጠኛ ባይሆኑም ሰላማዊ ሆነዋል ማለት አልችልም" ብለዋል።

ሩሲያ ዩክሬንን የወረረችበት ቀን በአገራቸው የሚያፍሩበት ዕለት እንደሆነም ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ሥራውን የለቀቀ ሩሲያዊ አመራር መኖሩ ግልጽ ባይሆንም፣ እስካሁን በይፋ የተሰማ ነገር የለም።

ሩሲያ ከዚህ በኋላ እንደ ጠላት እንደምታያቸው ቢጠብቁም "አንዳችም ሕገ ወጥ ድርጊት አልፈጸምኩም። የተሰማኝን ተናግሬ ሥራዬን ለቅቄያለሁ። ለደኅንነቴ መስጋቴ ግን አይቀርም" ይላሉ።