በአፍጋኒስታን ሴት የቴሌቪዥን አቅራቢዎች ፊታቸውን መሸፈን ጀመሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታሊባን ያስተላለፈውን ትዕዛዝ ተከትሎ በአፍጋኒስታን በቴሌቪዥን የሚታዩ ዘጋቢዎች እና አቅራቢዎች ከትላንት ዕሁድ ጀምሮ ፊታቸውን መሸፈን ጀምረዋል።
ይህ ትዕዛዝ ከመተግበሩ በፊት የተወሰኑ አቅራቢዎች ውሳኔውን በግልጽ ሲቃወሙት እና ፊታቸውን ሳይሸፍኑ በቴሌቪዥን መስኮት ታይተዋል።
ሴት የቴሌቪዥን ተቀጣሪዎች ውሳኔውን አንቀበልም ብለው የተቃወሙ ቢሆንም ከአሰሪዎቻቸው ጫና እንደተደረገባቸው አንዲት የቴሌቪዥን አቅራቢ ተናግራለች።
ባለፈው ዓመት ስልጣን መልሶ የተቆጣጠረው ታሊባን ሴቶችን የሚመለከቱ ክልከላዎችን በብዛት እያወጣ ይገኛል።
ሴት የቴሌቪዥን አቅራቢዎች ሂጃብ እንዲለብሱ እና ፊታቸውን እንዲሸፍኑ ከተላለፉት ትዕዛዞች መካከል አንዱ ነው።
በሀገሪቱ ከሚታወቁ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አንዱ በሆነው የምትሰራው ፋሪዳ ሲላ "ሙስሊም ስለሆንን ሂጃብ ለብሰን ጸጉራችንን ብንሸፍን ችግር የለውም። ነገር ግን ፊት ተሸፍኖ ለተከታታይ ሁለት ወይም ሶስት ሰዓት መቆየት እና ማውራት ከባድ ነው" ስትል ለቢቢሲ አስረድታለች።
ውሳኔው እንዲቀለበስ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያደርግም ጠይቃለች።
"ሴቶችን ከማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ህይወት ማስወገድ ይፈልጋሉ" ስትልም አክላለች።
ከዚህ ቀደም ታሊባን በአፍጋኒስታን የሚገኙ ሁሉም ሴቶች ፊታቸውን እንዲሸፍኑ አሊያም ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ያዘዘ ሲሆን ይህንን ውሳኔ ከትላንት ጀምሮ ወደ ቴሌቪዥን ላይ በሚሰሩ ሴቶች እንዲተገበር ወስኗል።

ሶኒያ ኒያዚ የምትባል ሌላ ቴሌቪዥን አቅራቢ ደግሞ "ፊታችንን አንሸፍንም ብለን ተቃውመን ነበር" ስትል ለኤኤፍፒ ተናግራለች።
ሆኖም ለውሳኔው የማይገዙ ከሆነ የሚሰሩባቸው ተቋማት ሴት አቅራቢያዎችን ወደ ሌላ ስራ እንዲያዘዋውሩ አሊያም እንዲያባርሩ ጫና እንደተደረገባቸው ተናግራለች።
በአፍጋኒስታን የሚገኝ አንድ የቴሌቪዥን ምክትል ዳይሬክተር "ዛሬ በጥልቅ ሃዘን ውስጥ ነን" ሲል በፌስቡክ ገጹ ጽፏል።
ሌላ ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች አፍጋኒስታናዊ ጋዜጠኛ "ዛሬ ለሀገሬ ሴቶች ሌላ ጥቁር ቀን ነው" ብላለች።
ሴት ጋዜጠኞች ቀጣዩ እርምጃ ሴቶችን ሙሉ በሙሉ ከቴሌቪዥን ማገድ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ተናግራለች።
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሙስሊም ሴቶች በአደባባይ ፊታቸውን መሸፈን የሃይማኖት ግዴታቸው አይደለም ብለው ያምናሉ።
ይሁን እንጂ ታሊባን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሴቶች ላይ ከበድ ያሉ ክልከላዎችን እያጣለ ይገኛል። ይህም ፓርኮችን የሚጎበኙበትን የተለየ ቀን መመደብ እና ያለጣባቂ ወንድ ረጅም ጉዞ እንዳይሄዱ መከልከልን ይጨምራል።












