በኩባ ዋና ከተማ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል በደረሰ ከባድ ፍንዳታ 22 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኩባ፣ ሐቫና ውስጥ በሚገኝ ሆቴል ላይ የተነሳውን ፍንዳታ ተከትሎ ቢያንስ 22 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።
ከ60 በላይ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና እየተሰጣቸው ይገኛል።
ባለ አምስት ኮከቡ ሳራቶጋ ሆቴል ኩባ ውስጥ ካሉ ቅንጡ ሆቴሎች በዋናነት ይጠቀሳል።
ከሆቴሉ ውጭ ቆሞ የነበረ ነዳጅ የጫነ አሮጌ ቦቴ ፈንድቶ አደጋው እንደተከሰተ ተገልጿል።
በፍንዳታው ሳቢያ የሆቴሉ ብዙ ክፍሎች ተጎድተዋል።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽ ምክንያት ተዘግቶ የቆየው ሆቴሉ፣ በቀጣዩ ሳምንት ሥራ ይጀምራል ተብሎ እየተጠበቀ ነበር።
በሆቴሉ ፍርስራሽ ስር ታፍነው መውጣት ያልቻሉ ሰዎችን ነፍስ ለማዳን አሁንም ፍለጋው ቀጥሏል።
በፍንዳታው ከሞቱት መካከል ነፍሰ ጡር ሴትና ሕፃን እንደሚገኙበት ይፋ ተደርጓል።
ከሆቴሉ ጀርባ የሚኖሩ ያዚራ ደ ላ ካሪዳድ የተባሉ ግለሰብ ለሲቢሲ "ፍንዳታው የመሬት መንቀጥቀጥ መስሎኝ ነበር" ብለዋል።
ፍንዳታው ከተሰማ በኋላ አካባቢው በጥቁር ጭስ ታፍኖ እንደነበር የዓይን እማኞች ተናግረዋል።
ከሆቴሉ ጀርባ የሚገኝ ትምህርት ቤት ላይ ጉዳት እንዳልደረሰና ተማሪዎች ከአካባቢው እንዲወጡ መደረጉም ተገልጿል።
የኩባው ፕሬዝዳንት ሚጌል ዲያዝካናል ሆቴሉን ጎብኘተው "ቦንብ አልፈነዳም። ጥቃትም አልተሰነዘረም። አሳዛኝ አደጋ ነው የተከሰተው" ብለዋል።
ኩባ በወረርሽኙ ሳቢያ የተቀዛቀዘ ቱሪዝሟ ሊያገግም ሲል ነው ይህ አደጋ የተከሰተው።
ሳራቶጋ ሆቴል በታሪካዊነቱ ይታወቃል። በወረርሽኙ ሳቢያ ሲዘጋ እድሳት ተደርጎለትም ነበር።
በ19ኛው ክፍል ዘመን የተሠራው የሆቴሉ ሕንፃ ሐቫና ውስጥ ዝነኛ ከሆኑ ቦታዎች ይጠቀሳል።
ማዶና፣ ቢዮንሴ፣ ሚክ ጃገር በሆቴሉ ካረፉ ታዋቂ ግለሰቦች መካከል ይጠቀሳሉ።












