ከአራስ እስከ 114 ዓመት ዕድሜ የኮቪድ-19 ሕሙማንን ያከመው የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ውለታ

የፎቶው ባለመብት, AMANUEL SILESHI
ላለፉት ሁለት ዓመታት መላውን ዓለም አዳርሶ 15 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት የመጀመሪያ ወቅት ሥራ የጀመረው ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በኢትዮጵያ የወረርሽኑ ጥረት ውስጥ ጉልህ ቦታን ይዟል።
ስለ ወረርሽኙ ምንነትና አጠቃላይ ሁኔታ ዝርዝር መረጃ ባልነበረበት ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕሙማንን ተቀብሎ ያስተናገደው ሆስፒታሉ፣ ባለፈው ሐሙስ በእንክብካቤው ስር የነበሩት ብቸኛ ታካሚ አገግመው ወደ ቤታቸው በመሄዳቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ሆስፒታሉ ውስጥ የኮቪድ ታማሚ እንደሌለ አሳውቋል።
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ያሬድ አግደው ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ታካሚው አገግመው ወደ ቤታቸው በመሸኘታቸው ላለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ የኮቪድ-19 የሕክምና ማዕከል ሆኖ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለው ሆስፒታል ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ታካሚ ውሎ አድሯል።
የሕክምና ማዕከሉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽን በኢትዮጵያ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በሁሉም የበሽታው ማዕበል ደረጃዎች ወቅት ሕምና የሚያስፈልጋቸውን ሕሙማን ሲያገለግል ቆይቷል።
አገሪቱን ባጋጠሟት አራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማዕበሎች ውስጥ ባለፉት ሁለት ዓመታት ምንም ታካሚ ሳይኖር ያሳለፉበት ጊዜ እንዳልነበረ ዶ/ር ያሬድ አስታውሰዋል።
በአራተኛው ማዕበል ተቀብለው ሕክምና ሲሰጧቸው ከነበሩ ሕሙማን መካከል የሕክምና ባለሙያ የሆኑት ታካሚ አስፈላጊውን ድጋፍ አግኝተው በማገገማቸው ነው ሐሙስ መጋቢት 27/2041ዓ. ም. ከሆስፒታሉ የተሸኙት።
በዚህም ሆስፒታሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕክምና የሚያስፈልገው አንድም ታማሚ ሳይረኖረው 24 ሰዓታትን አሳልፏል።
"ሕክምናውን በተሳካ ሁኔታ ጨርሶ የተሸኘው ሰው፣ በወረርሽኙ አራተኛ ማዕበል አገግሞ ከሆስፒታሉ የወጣ የመጨረሻው ሰው ይሆናል ብለን ተስፋ እንዳርጋለን" ሲሉ ዶ/ር ያሬድ ለቢቢሲ ምኞታቸውን ተናግረዋል።
ኮቪድ-19 መጋቢት 04/2012 ዓ. ም. በኢትዮጵያ ውሰጥ መገኘቱ ሲረጋገጥ በአገሪቱ የተገኘ የመጀመሪያውን ጃፓናዊ ታማሚ በመቀበል ሥራ የጀመረው የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል፣ ከሁለት ዓመታት ያልተቋረጠ አገልግሎት በኋላ ስማቸው ያልተገለጹትን ለአሁኑ የመጨረሻው ሊባሉ የሚችሉትን ሕመምተኛ አክሞ ለመሸኘት በቅቷል።
በሁለት ዓመታት ውስጥ ሐሙስ ዕለት አገግመው እስከወጡት ታካሚ ድረስ ሆስፒታሉ 6546 የኮሮናቫይረስ ሕሙማንን ያስተናገደ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ወይም 87 በመቶ የሚሆኑት ባገኙት ሕክምና አገግመው መውጣታቸውን ዶ/ር ያሬድ ገልጸዋል።
ከዚህ ባሻገር ከ800 በላይ የሚሆኑት ወይም አጠቃላይ ሆስፒታሉ ካስተናገዳቸው ሕሙማን መካከል 13 በመቶው ደግሞ በወረርሽኙ ሰበብ ለህልፈት ተዳርገዋል።

የፎቶው ባለመብት, AMANUEL SILESHI
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ይህንን አገልግሎት በሰጠባቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ወረርሽኙ የተለያዩ ጫናዎች ባለሙያዎች ላይ አሳድሮ እንደነበር የሚያስታውሱት ዶ/ር ያሬድ "በተለይ በመጀመሪያው ጊዜ ላይ ስለ በሽታው ዝርዝር ሁኔታ ከነበረው ዝቅተኛ መረጃ አንጻር ባለሙያዎች ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና ገጥሟቸው ነበር" ይላሉ።
ነገር ግን የሕክምና ባለሙያዎቹ ቃል ኪዳናቸውን ጠቀብቀው አገራቸውንና ሕዝባቸውን በማስቀደም በዚያ አስፈሪና አስቸጋሪ ወቅት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ባለፉት ሁለት ዓመታት ያለማቋረጥ ለመወጣት ችለዋል።
በተለይ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሕሙማን ወደ ሆስፒታሉ በብዛት መምጣት በጀመሩበት በሁለተኛው እና በሦስተኛ ዙር የወረርሽኑ ማዕበል ወቅት፣ የሰው ሠራሽ መተንፈሻ ድጋፍ የሚፈልጉ እና ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች መጨመሩ ከባድ ጫናን በሆስፒታሉ ላይ አስከትሎ ነበር።
በተጨማሪ ደግሞ ለሌሎች ሕክምናዎች ከሚሰጡ የሆስፒታሉ ባለሙያዎች መካከልም በበሽታው የሚያዙ ስለነበሩ ከባድ ሥራና ኃላፊነትን ከሚወጡት ባለሙያዎች ሲቀነሱ የሰው ኃይል እጥረት ገጥሟቸው የነበረበት ጊዜ እንደነበር ዶ/ር ያሬድ ይጠቅሳሉ።
ከባለሙያዎቹ መካከል በተደጋጋሚ ጭምር በበሽታው የመያዝ ሁኔታ የገጠማቸው ቢኖሩም ለሞት የተዳረገ የሆስፒታሉ ባልደረባ አልነበረም።
የመጀመሪያው የኮቪድ-19 ሕክምና ማዕከል የሆነው የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ከወረርሽኙ መከሰት ጀምሮ በሆስፒታል ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን፣ የመተንፈሻ ድጋፍ የሚያሻቸውን እንዲሁም የጽኑ ሕሙማን ሕክምና ድጋፍ የሚፈልጉ የኮቪድ-19 ሕሙማንን አስተናግዷል።
በተጨማሪም በኮሮናቫይረስ ተይዘው ተጓዳኝ ሕመም ኖሮባቸው የሐኪም የቅርብ ክትትልና ድጋፍ የሚያስፍለጋቸው፣ ነፍሰ ጡሮችና የመውለጃ ጊዜያቸው የደረሱ ሕሙማንን ጭምር በመቀበል ከወረርሽኙ ጋር የተያያዙ ዘርፈ ብዙ የሕክምና አገልግሎቶችን ሲሰጥ ቆይቷል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ሆስፒታሉ በሰጠው አገልግሎት ከወረርሽኙ የዳኑ ሰዎች በተለያየ የዕድሜ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
እዚያው የተወለዱ የአንድ ቀን ዕድሜ ካላቸው አራስ ሕጻናት አንስቶ አስከ 114 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አዛውንት ድረስ የኮቪድ ሕሙማንን ሆስፒታሉ አስተናግዷል።
ከአንድ ወር በታች ዕድሜ ያላቸው በበሽታው ተይዘው ለሕክምና የገቡት ሁሉም ጨቅላ ሕጻናት አገግመው እንደወጡ ዶ/ር ያሬድ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በሁለት ዓመታት ውስጥ በርካታ መልካምና አሳዛኝ አጋጣሚዎች በሆስፒታሉ ውስጥ ማጋጠሙን በመጥቀስ፣ እነዚህን የሆስፒታሉን ክስተቶች እና ሌሎች የሚነገሩ ታሪኮችን በመጽሐፍ የማቅረብ ሐሳብ እንዳላቸው ዶ/ር ያሬድ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ መገኘቱን ተከትሎ በአገሪቱ ውስጥ በተደረጉ ምርመራዎች ከ470 ሺህ በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ከ7500 በላይ ሰዎች ደግሞ በወረርሽኙ ሰበብ ለሞት መዳረጋቸውን ከጤና ሚኒስቴር የወጣው ወቅታዊ መረጃ ያመለክታል።
















