ኮሮናቫይረስ፡ "ኮሮና ቤቴን አፈረሰው" ከወለደች በኋላ በኮቪድ-19 ሚስቱን ያጣው ባል

ካሳሁን፣ ሁለት ሴት ልጆቻቸውና ባለቤቱ አስከዳር

የፎቶው ባለመብት, FAMILY

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መከሰቱ ከተረጋገጠ ከወራት በኋላ የጤና ሚኒስቴር አንዲት በኮቪድ-19 የተያዘች እናት ከቫይረሱ ነጸ የሆነ ልጅ በቀዶ ህክምና መውለዷን ሲገልጽ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ከ15 ቀናት በኋላ ግን የጨቅላው እናት በቫይረሱ ምክንያት ህይወቷ ማለፉ በርካቶችን አሳዝኗል።

ወረርሽኙ በኢትዮጵያ መገኘቱ የተገለጸበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የሟች ባለቤትና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባል የሆነው መቶ አለቃ ካሳሁን አበራ ስለጨቅላው፣ ስለቤተሰቡ፣ ስለራሱና አሁን ስላሉበት ለቢቢሲ ታሪኩን አጋርቷል።

መስመር

መቶ አለቃ ካሳሁንና ባለቤቱ እስከዳር ክፍሌ የተዋወቁት በ1995 ዓ.ም ነበር። ለሰባት ዓመታት በጓደኝነት ከቆየን በኋላ በ2002 የትዳር ህይወትን ጀመሩ። ለአስር ዓመታት በዘለቀው ትዳራቸው ሁለት ሴት ልጆች ያፈሩ ሲሆን በመጨረሻም በቀዶ ህክምና የተወለደው ልጃቸው ወንድ ነው።

ሁለቱን ጥንዶች የኮሮናቫይረስ ተከስቶ እከወዲያኛው እስኪለያያቸው ድረስ በፍቅር እንደኖሩ መቶ አለቃ ካሳሁን ይናገራል።

"ፖሊስ በመሆኔ ከብዙ ሰዎች ጋር እገናኛለሁ፤ እሷም መውለጃዋ አስኪደርስ ድረስ በአንድ ክሊኒክ ውስጥ ትሰራ ስለነበረ ሁለታኛንም ለበሽታው ተጋላጭ ነበርን" ይላል።

በጓደኝነትም በትዳርም ውስጥ በቆዩባቸው ዓመታት ሁለቱ ጥንዶች ቤታቸው ሰላምና ፍቅር የሞላበት ነበር። ሁለቱም ጥረው በሚያገኙት ገቢ ልጆቻቸውን ተጋግዘው ያሳድጉ ነበር። "በተለይ ልጆቻችን ከእሷ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ነበራቸው" ይላል ካሳሁን።

ባለፈው ዓመት መጋቢት ላይ የኮሮናቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ በታወቀበት ጊዜ ነፍሰጡር የነበረችው አስከዳር መደበኛ የህክምና ክትትል በምታደርግበት ጊዜ ድካምና የምግብ ፍላጎቷ ቢቀንስም ሐኪሞች ጽንሱ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሆነ ተነግረዋት ነበር።

ነገር ግን በወቅቱ ከሚነገረው የበሽታው ምልክት አንጻር ስጋት የነበራት አስከዳር ለቤተሰቧና ለጽንሷ ደኅንነት ስትል የኮሮናቫይረስ ምርመራ ለማድረግ ወስና ናሙና በመስጠት ወደ ቤቷ ከተመለሰች ከሁለት ቀን በኋላ ቫይረሱ እንደተገኘባት ተነገራት።

አዲሱ በሽታ የተገኘባት ነፍሰጡሯ አስከዳር ሁኔታውን እንደሰማች እራሷን አዘጋጅታ የጤና ባለሙያዎች መጥተው እስኪወስዷት ተዘጋጅታ ስጥጠብቅ "እኛ በጣም ነበር የተረበሽነው" ይላል ባለቤቷ።

የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲቲዩት የጤና ባለሙያዎች አስከዳርን በለይቶ ማቆያ ውስጥ ቆይታ ህክምና እንድታገኝ ለማድረግ በምሽት መጥተው ከቤቷ ሲወስዷት ባለቤቷ መቶ አለቃ ካሳሁንና ሁለት ልጆቹ ብቻቸውን ከቤት ቀሩ።

በወቅቱ ምንነቱ በደንብ ባልታወቀው ገዳይ በሽታ የተያዘች ባለቤቱ ብቻዋን ወደ ለይቶ ማቆያ የተወሰደችበት ካሳሁን በድንጋጤ ውስጥ ሆኖ ምን እንደሚያደርግ አያውቅም ነበር።

በአንድ በኩል ልጆቹን ብቻቸውን ትቶ ሚስቱ ወደተወሰደችበት የጤና ተቋም ተከትሎ በመሄድ ከጎኗ በመሆን ጭንቀቷን ለመጋራት ቢፈልግም የልጆቹ ነገር አሳሰበው።

በሌላ ወገን ደግሞ ነፍሰጡሯ ባለቤቱ በገዳዩ የኮሮናቫይረስ ተይዛ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ብቻዋን ትሆናለች በሚል ጭንቅ ውስጥ ገባ።

በመጨረሻ ግን ቢያንስ ተወሰደች ወደተባለበት ቦታ ሄዶ ማድረግ የሚችለውን ለመሞከር ወስኖ ወደ ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ቢሄድም ከህሙማን በስተቀር ማንም መግባት እንደማይችል ተነግሮት በተሰበራ ስሜት ከበር ተመለሰ።

ደስታና ሐዘን

ከታመመችው ባለቤቱ ጎን ሆኖ ሊያበረታት ባይችልም በስልክ መገናኘት ዕድልን አግኝቶ ነበር። በአንዱ ቀንም ባለቤቱ እስከዳር ስልክ ደወለችለት። በዚሁ ጊዜም "መውለድ አለብሽ ብለው ኦፕሬሽን ሊያደርጉኝ ነው" ብላ ነገረችው።

ካሳሁን የሚሆነውን ከርቀት ሆኖ ከመስማማት ውጪ ምንም አማራጭ ስላልነበረው ሐኪሞቹ የደረሱበት ውሳኔን ውጤት መጠበቅ ጀመረ።

ባለቤቱ የዚያኑ ዕለት አመሻሽ 12 ሰዓት አካባቢ ቀዶ ህክምና ተደርጎላት ወንድ ልጅ ወለደች። "በቀጣይ ቀናት ቅዳሜ እንዲሁም ዕሁድ ዕለት ለምታውቀው ሰው ሁሉ ስልክ እየደወለች 'እግዚያብሔር ይመስገን በሰላም ተገላገልኩ' እየለች ደስታዋን ስትገልጽ ነበረች" ይላል።

ካሳሁን ባለቤቱ መውለዷን ካወቀ በኋላ የእራሱና የልጆቹ የጤና ሁኔታ ጥያቄ ሆነበት። ተከትሎም በተደረገላቸው ምርመራ አሱና ትንሿ ልጁ ላይ ቫይረሱ በመገኘቱ ባለቤቱ ህክምና እየተከታተለች ወደለበት ሆስፒታል እንዲገቡ ተደረገ። የባለቤቱ ወንድምም በኮሮናቫይረስ ተይዞ ወደሆስፒታሉ መጥቶ ተገናኙ።

በዚህ ጊዜ ባለቤቱን የማየት እድል አገኘ። ከቤት ከወጣች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሆስፒታል ውስጥ ሲያገኛት "ኦክስጅን ተደርጎላት ደርስኩ። እሷም 'እንዳትወጣ' ብላኝ እዚያው አብሪያት እስከ ሌሊቱ ሰባት ሰዓት ቆየሁ" ይላል።

ዶክተሮች "'ከዚህ በኋላ በዚህ ሁኔታ ልትቀጥል አትችልም' አሉና ቬንትሌተር [የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ] ወዳለበት ክፍል አስገቧት። ያቺ ጊዜ ዓይን ለዓይን ለመጨረሻ ጊዜ የምነተያይበት ጊዜ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም ነበር" ሲል በሐዘን በተሰበረ ድምጽ ያስታውሳል።

ከዚያ በኋላ መቶ አለቃ ካሳሁን ባለቤቱን ከተኛችበት ክፍል እየሄደ ለማየት ቢጠይቅም ሐኪሞቹ እንዲታገስ እየነገሩት ለቀናት ቆየ። መጨረሻ ላይ ህይወቷ ከማለፉ በፊት ቅዳሜ [ግንቦት 29/2012 ዓ.ም] "የናፈቀችኝን ባለቤቴን ዛሬ ማየት አለብኝ ብዬ አጥብቄ ስለጠየቅኳቸው ፈቀዱልኝ።"

"ስገባ አስከዳር የለችም፤ አታየኝም። በጣም ደክማለች ከዚያ በኋላ እኔም እራሴን ሳትኩ [ሳግ እየተናነቀው]" አሱ ቢያየትም ባለቤቱ አታየውም ነበር።

ያቺ ዕለትም የመጨረሻቸው ሆነች።

የካሳሁን ቤተሰብ ሐዘን በዚህ አላበቃም ነበር። ከቀናት በኋላ ከሕበረተሰብ ጤና ኢኒስቲቲዩት ተደውሎ የትልቋን ልጁን የጤና ሁኔታ ለማወቅ በድጋሚ ምርመራ ማድረግ እንዳለባት ተነግሮት ውጤቷ ፖዘቲቭ ሆነ፤ ሌላ ጭንቀት ተጨመረበት።

ካሳሁን የልጆቹ እናት የቀናት ዕድሜ ብቻ ያለውን ጨቅላ ልጇን ትታ በኮሮናቫይረስ ሰበብ ለሞት ስትዳረግ። ሰማይ እላዩ ላይ የተደፋበት ያህል ነበር የተሰማው። ዙሪያ ገባው ጨለማ ሆነበት።

በዚያ ላይ እሱም ሆነ ሁለቱ ሴት ልጆቹ በቫይረሱ ተይዘው ነበር። የእናት፣ የአባትና የሁለት እህቶቹ እንክብካቤና ፍቅር የሚያስፈልገው ጨቅላው ልጅ ከእነሱ ተነጥሎ በሐኪሞች እንክብካቤ እየተደረገለት ነው።

አብይስማክ

የፎቶው ባለመብት, FAMILY

"አብይስማክ"

ሦስት ልጆቹን እናት የኮሮናቫይረስ የነጠቀው ካሳሁን የባለቤቱ ያለመኖር የፈጠረበት ሐዘን ከወራት በኋላ አሁንም ድረስ ትኩስ ነው።

የባለቤቱ ሞት በህይወቱ ላይ የፈጠረው ክፈተት በምንም የሚሞላ አልሆነለትም "እንቅልፍ የለኝም። አልተኛም። እንደገና....[ለቅሶ]...እና ያው ሳልወድ በግዴ ከልጆቼ ጋር ተለያይቻለሁ። አሁን ትልቋ በተለይ በጣም እየተረበሸች ነው። እና በጣም ከባድ ነው....[ሳግ እየተናነቀው]"

ሁለት ሴት ልጆች ያሏት አስከዳር ሦስተኛውን እርግዝና ካወቀች በኋላ ወንድ መሆኑን ስታውቅ በእጅጉ ተደስታ እንደነበር ካሳሁን ያስታውሳል። እናቱን በኮሮናቫይረስ ከመሞቷ በፊት "አብይስማክ" ብላ ስም ያወጣችለትና የጓጓችለት ልጇ ካለእሷ አሁን ዘጠኝ ወር ሆኖታል።

በወረርሽኙ ምክንያት የቤተሰቡ ራስ የሆነችውን እስከዳርን የተነጠቀው ቤተሰብ፤ እድለኛ ሆነው ለክፉ ባይሰጣቸውም ቫይረሱ የቤተሰቡን አባላት በሙሉ አዳርሶ ነበር።

በዚህም ሳቢያ ቤተሰቡን ገጥሞት የነበረው ማግለል በጣም ከባድ እንደነበር ካሳሁን ያስታውሰዋል። በሽታው በተከሰተበት የመጀመሪያዎቹ ወራት የነበረው ፍርሃት ሁሉንም ተጠራጣሪና ፈሪ አድርጎት ስለነበር በርካታ ሰዎች እሱንና ልጆቹን ይርቁ ነበር።

ቤት ለመከራየትም አስቸጋሪ እንደሆነበት ይናገራል።

"በቃ ቀብር አትሄድም"

የኮሮናቫይረስ የታመመ ወዳጅ ዘመድን ማስታመምና መጠየቅ ብቻ ሳይሆን በርካታ ነገሮችን አመሰቃቅሏል። በሞት የተለየን የቅርብ ሰው አልቅሶ መቅበርና የመጨረሻ ስንብት ማድረግን የማይቻል ነገር አድርጎታል።

ካሳሁንም እንደፍላጎቱ ሳያስታምማት ወረርሽኙ የነጠቀውን ባለቤቱን ከአስከሬኗ ጎን ሆኖ እንባውን አፍስሶ፣ ሐዘኑን በመግለጽ የመጨረሻ ስንብት ለማድረግ ከማይቻልበት ሁኔታ ላይ እንደነበረ ያስታውሳል።

"በጣም ከባድ ነበር። የሆነ ቀን ጠሩኝና 'ተሰናበታት' አሉኝ። 'ምንድን ነው መሰናበት' ስላቸው አይ 'በቃ ቀብር አትሄድም' አሉኝ። 'ለምን' ስላቸው 'ከዚህ [ከሆስፒታሉ] አይወጣም' አሉኝ።"

ይህ ለካሳሁን ፈጽሞ የሚዋጥለት ሐሳብ አልነበረም። አብረውት ደግሞ የባለቤቱ እናት ነበሩ። "'አይ እኔና እናቷማ እንቀብራለን' በሚል ጭቅጭቅ ተፈጠረ። እነሱም ተረዱን መሰለኝ እኔና እናቷ ቀብሯ ላይ እንድንገኝ ተደረገ።"

ይህም ቢሆን ግን ካሳሁን ለውድ ባለቤቱ እሱ የሚፈልገውን አይነት የቀብር ሥነ ሥርዓት ስላልተፈጸመላት አሁን ድረስ ይቆጫል። "በቃ ይህ በህይወት እካለሁ ድረስ የእግር እሳት እንደሆነብኝ ይኖራል" ሲል በሐዘን በተሰበረ ድምጽ ይናገራል።

ያልበረደ ሐዘን

"ክረምት ነበር። በቀብሩ ቦታ የነበረው ሁኔታ በጣም ከባድ ነበር። በወቅቱ አስክሬኗና እኛ ታጅበን የሄድነው በፖሊስ ነው። ወደ ቀብር ቦታ ከአምስት ሰው በላይ አልገባም። እኔም እናቷም ወደ መቃብር ቦታው አልሄድንም ያመጣን መኪና ጋር ቆመን ነበር የተሰናበትናት።"

አሁን ድረስ የባለቤቱን ሞት ለመቀበል የተቸገረው ካሳሁን "በእንደዚህ አይነት መልኩ እሷን ማጣት ከባድ ነው። ከባድ ህይወት ነው እየመራሁ ያለሁት። አሁንም ግራ ነው የሚገባኝ የሆነ ቦታ.......[ለቅሶ]........ደርሼ ስመጣ. . . የማገኛት ነው የሚመስለኝ። እና አሁንም ማመን አቅቶኛል" ይላል ሐዘኑ እንደ አዲስ እያገረሸበት።

መቶ አለቃ ካሳሁን በደረሰበት መሪር ሐዘን ምክንያት አስካሁን አልተረጋጋም ልጆቹን የባለቤቱ እናት እየተንከባከቡለት ነው። ትልቆቹ ሴት ልጆቹ ጎበዞችና ጠንካሮች እንደሆኑ ይናገራል። ከዚህም በላይ እንዲበረቱለት ቢፈልግም ካለበት ጭንቀት የተነሳ የእሱ አለመረጋጋት ተጽእኖ እንዳይፈጥርባቸው ይሰጋል።

በተጨማሪም የባለቤቱ ምትክ የሆነውን የመጨረሻውን ልጁን በልዩ ሁኔታ እንደሚመለከተው የሚናገረው ካሳሁን "ልጄን ሳየው በጣም ነው ደስ የሚለኝ። ባለቤቴ እራሷን አሳልፍ የሰጠችበት ልጄ ነው። በጣም ስትጓጓለት የነበረ ልጅ ነው። በቃ እሱን ሳየው እሷን የማይ ነው የሚመስለኝ።"

ባለቤቱን ነጥቆ ፍቅር የሞላበትን የሞቀ ቤቱን ያቀዘቀዘበት የኮሮናቫይረስ ለመቶ አለቃ ካሳሁን ደመኛ ጠላቱ ነው። "ኮሮና ቤቴን ነው ያፈረሰው። ከምወዳት ባለቤቴ ተለይቻለው። ልጆቼን እያየኋቸው በብዙ ችግር ምክንያት አብሬያቸው አይደለሁም። በአንድ ጎጆ ተሰብሰበን የነበርን ሰዎችን በትኖናል።"