የኮቪድ ህሙማንን የሚያክመው ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል እየሞላ ነው ተባለ

የኮቪድ ሕመምተኛ

የፎቶው ባለመብት, AMANUEL SILESHI

የኮቪድ-19 ሕሙማንን ተቀብሎ ህክምና የሚሰጠው ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በኮቪድ-19 ታካሚሞች እየሞላ እንደሚገኝ የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ያሬድ አግደው ለቢቢሲ ተናገሩ።

በተመሳሳይ ከትናንት በሰቲያ የጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በኮቪድ-19 ምክንያት በጽኑ የሚታመሙ እና ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር አሻቅቧል ብለው ነበር።

ከጤና ሚንስቴር የተገኘው ዕለታዊ የኮቪድ-19 አሃዝ እንደሚያመለክተው መስከረም 11 እና 12 ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ በእያንዳንዱ ቀን ከ40 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ያሬድ፤ ኮቪድ-19 ኢትዮጵያ መግባቱ ከተገለጸ ጀምሮ ሆስፒታላቸው በቫይረሱ የተያዙ ህሙማንን ሲያክም የቆየ መሆኑን አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሕሙማን ወደ ሆስፒታሉ እየገቡ እንደሆነ ተናግረዋል።

"ከአንድ ወር ከ15 ቀን ወዲህ የጽኑ ሕሙማን ክፍላችን ሙሉ ነው። የተቀሩት አልጋዎችም እየሞሉ ይገኛሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ወደ 5ሺህ የሚጠጉ ታማሚዎችን ተቀብሎ ማከሙን የሚናገሩት ዶ/ር ያሬድ፤ በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሉ ወደ 200 የሚጠጉ ሕሙማን የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ ይናገራሉ።

ዶ/ር ያሬድ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ለመጨመሩ ዋናው ምክንያት ዴልታ የተሰኘው የኮቪድ ዝርያ በኢትዮጵያ መገኘቱ እንደሆነም ተናግረዋል።

ዶ/ር ያሬድ፤ በቅርቡ በኢትዮጵያ እንደተከሰተ የተገለጸው ዴልታ ቫይረስ ከፍተኛ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ አቅም ያለውና የሚያስከትለውም ሕመም የከበደ መሆኑን በማስታወሰ ሕብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።

የጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ፍጥነት በመስፋፋት ሰዎችን ለከባድ ህመም የሚዳርግ እና ለሞት የሚያበቃው አደገኛው የዴልታ ዝርያ በአገራችን መኖሩ የተረጋገጠ ቢሆንም፤ በኅብረተሰቡ ዘንድ እየተወሰደ ያለው የመከላከያ እርምጃ አነስተኛ ነው ብለዋል።

በቀጣይ የትምህርት ቤቶች መከፈት፣ ልዩ ልዩ በዓላትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ምረቃ እና ሌሎች ለቫይረሱ ስርጭት አጋላጭ ሁኔታዎች መከናወናቸው ለቫይረሱ ስርጭት ምክንያት እንደሚሆኑ አሳስበው፤ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የወጣው መመሪያ እንዲተገበር ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ሦስተኛው ዙር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ማዕበል መከሰቱን የጤና ባለሙያዎች የሚናገሩ ሲሆን፤ ይህም ዴልታ ከተባለው ከባድ የቫይረሱ ዝርያ ጋር ተዳምሮ በበሽታው የሚያዙና ሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር ከፍ አድርጎታል ይላሉ።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ በበሽታው የሚያዙ፣ በጽኑ የሚታመሙና ለህልፈት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እጨመረ መሄዱ በሽታው በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያመለክታል።

የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት በአገሪቱ ያለውን የወረርሽኙን ሁኔታ በተመለከተ የሚያወጡት መረጃ እንደሚያመለክተው በአገሪቱ በሽታው መኖሩ ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ ከ335 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው መያዛቸው በምርመራ ተረጋግጧል።

ከእነዚህ ውስጥም አብዛኞቹ ከወረርሽኙ ያገገሙ ሲሆን በበሽታው ሰበብ ከ5260 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

ኢትዮጵያ በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ ክትባቶችን መስጠት ከጀመረች ወራት የተቆጠሩ ሲሆን አስካሁን ከ2.6 ሚሊዮን ሰዎች በላይ መከተባቸው ተገልጿል።