ኢትዮጵያ ውስጥ 'ለመዝናናት' የሚደረግ አደን አለ? እንዴትስ ይከናወናል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዱር እንስሳትን በሕጋዊም ሆነ በሕገ-ወጥ መልኩ አድኖ መያዝ ወይም ለምግብነት ማዋል ለረዥም ዓመታት ከሰው ልጅ ጋር የዘለቀ ተግባር ነው።
በዓለም ዙሪያ የእንስሳት አደን ጉዳይ እጅጉን አከራካሪ ነው።
ለእንስሳት መብቶች እና አያያዝ የሚከራከሩ ወገኖች በሕጋዊም ሆነ በሕገ-ወጥ መልኩ የሚፈፀም አደን በፍፁም መከናወን የለበትም ሲሉ ይሞግታሉ።
ይህ በአብዛኛው ጊዜ በግልጽ የማይነገርለት የኢኮኖሚ ዘርፍ በኢትዮጵያ ውስጥ አለ? እንዴትስ ይከናወናል?
ምን ዓይነት እንስሳቶችስ በምን ሁኔታ ይታደናሉ? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ፈልገናል።
*በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ያሉ ምስሎች እና ገለጻዎች የተወሰኑ አንባቢዎችን ሊረብሹ ይችላሉ

በኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ድርጅት ውስጥ የዱር እንስሳት ልማትና አጠቃቀም ባለሙያ የሆኑት አቶ ጨመረ ዘውዴ ሕጋዊ አደን በሁለት መልኩ ይካሄዳል ይላሉ።
የመጀመሪያው ፈቃድ ያላቸው ድርጅቶች በፈቃድ ያገኙት ቦታ እና ኮታ ላይ ደንበኞችን ከውጪ አገራት በማምጣት ያሳድናሉ። ሌላኛው ደግሞ በአገሪቱ ዜጎች ፈቃድ ማግኘትም ይችላሉ።
እነዚህኞቹ ግን ከባህር ማዶ እንደሚመጡት ሰዎች፣ ማደን የሚችሏቸው እንስሳት እና አእዋፋት ብዛት ብዙ አይደለም፤ ገደብ አለው።
ባለሙያው ለቢቢሲ እንዳስረዱት እንዲያድኑ የሚፈቀደው እስከ ስድስት ዓይነት እንስሳቶችን ነው።
ስፖርታዊ አደን
አቶ ጨመረ፣ ሰዎች ከውጪ አገራት በመምጣት በአገሪቱ ውስጥ በአደን ላይ የሚሰማሩበትን ምክንያት ከስፖርት ጋር ያያይዙታል።
አትሌቶች ግባቸው ወይንም አላማቸው ተፎካካሪ መሆን፣ ተፎካክረው አሸንፈው መውጣት መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ጨመረ፣ "በተመሳሳይ እነዚህ ሕጋዊ አደን የሚያካሄዱ ሰዎችም ብዙ ሐብት ያላቸው ሰዎች ናቸው። ለእነርሱ እንደ አንድ የመዝናኛ ምንጭ ነው ተብሎ ይወሰዳል" ይላሉ።
ይህ ስፖርታዊ አደን በመባል የሚጠራ ዘርፍ "ወጥተው፣ ወርደው፤ ወድቀው፣ ተነስተው፤ ትልቅ የሚባለውን እንስሳ በመፈለግ አግኝተው ሲያድኑ እንደ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ነው የሚወሰደው። ይህ ደግሞ ደስታን ይሰጣቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ከአደን በኋላ ውጤቱን ይዘው ወደ አገራቸው ይገባሉ። ይህም ጎፍላ (Trophy) ይባላል" ሲሉ ስለ ስፖርታዊ አደን ያብራራሉ።
እነዚህ ሰዎች አድነው የገደሏቸውን እንስሳት በተለያዩ ኬሚካሎች በማድረቅ እና በተለያዩ መንገዶች በሕይወት ያሉ እንዲመስል በማድረግ በሙዚየሞች እና የራሳቸው ስብስቦች ውስጥ ለማሳየት ይጠቀማሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሚታደኑት ምን ዓይነት እንስሳት ናቸው? ገደብስ አለው?
የአደን ዓይነት እና ሂደቱ እንደ የአገሩ ተጨባጭ ሁኔታ ይለያያል። ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ለማደን የሚፈቀደው አጥቢ እንስሳትን ብቻ ነው።
ከእነዚህ ውስጥም 52 የእንስሳት ዓይነቶችን ማደን ይፈቀዳል፤ ከሚዳቋ አንስቶ እስከ ጎሽ ድረስ።
ሴት እንስሳት አይታደኑም። ወንዱ ብቻ ነው የሚታደነው።
ወንዱም ቢሆን አርጅቶ እድሜው ለሞት የደረሰ መሆን እንዳለበት ተቀምጧል።
"የደጋ አጋዘን ብንወስድ ቀንዱ ነው የሚለካው። ልኬቱ ወይንም ቁመቱ 28.5 ኢንች በላይ መሆን አለበት" ይላሉ የዱር እንስሳት ባለሙያው አቶ ጨመረ።
እነዚህን የዱር እንስሳት በሚያድኑበት ወቅት፣ የጦር መሳሪያዎችን የሚጠቀሙ ሲሆን የትኛውን እንስሳ በምን ዓይነት የጦር መሳርያ እና ምን ያህል የጥይት መጠን መጠቀም እንዳለባቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠ መመርያ አለ።
"ለዝሆን የሚሆን ጥይት ለሚዳቋ መጠቀም አይቻልም" የሚሉት አቶ ጨመረ፣ ለአደን ከባህር ማዶ የሚመጡት ሰዎች ሙሉ የጦር መሳርያ ትጥቃቸውን ይዘው እንደሚመጡ ይናገራሉ።
ለአእዋፋትም ቢሆን የሚታደኑበት ጥይት እንደሚለይ እኚህ የዱር እንስሳት ባለሙያ ይናገራሉ።
ይህንን ተግባራዊነቱን ለማረጋገጥም የተቀመጠ ሕግ አለ።
"ለምሳሌ አንድ ሰው ከእድሜው ከተፈቀደው ያነሰ ወንድ እንስሳ ወይንም ሴት ከገደለ የከፈለውን ክፍያ እጥፍ ይቀጣል። በተጨማሪም ከመንግሥት አካል በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰራ ባለሙያ ከሚያድኑት ሰዎች ጋር በመሰማራት መመሪያው ተግባራዊ መሆኑን ይከታተላል" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Social Media
'ትልቅ ገቢ ያስገኛል'
እኚህ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ ይህ የአደን ዘርፍ ለአገሪቱ ትልቅ ገቢ ያስገኛል ይላሉ።
"እንደ እኛ ላሉ አገራት ትልቅ የገቢ ምንጭ ነው። ይህ የሚሸጠው የዱር እንስሳ እድሜውን ጨርሶ ተፈጥሯዊ ሞት ለመሞት የተቃረበ ስለሆነ ቢሸጥም፣ ባይሸጥም፤ ዛሬም ሆነ ሌላ ጊዜ በተፈጥሯዊ ሞት መሞቱ አይቀሬ ነው። ስለዚህ ይህንን ለሞት የተዘጋጀ እንስሳ ወደ ገንዘብ እንደ መቀየር ማለት ነው" ይላሉ።
ለጋዜጠኛ ሔኖክ ስዩም ግን ይህ የሚዋጥ ሃሳብ አይደለም።
"እንስሳት ተፈጥሯዊ ሞታቸውን እንዳይሞቱ ማደን ራስ ወዳድነት ነው" ይላል።
አቶ ጨመረ በበኩላቸው የሚፈፀመውን ክፍያ በመጥቀስ የውጪ ምንዛሬ ማግኛ መንገድ እንደሆነና አዳኞችም አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ የተለያዩ ወጪዎችንም በማውጣት ለአገሪቷ ገቢ እንደሚያስገኙ ይናገራሉ።
እንደ ምሳሌም የደጋ አጋዘንን ያነሳሉ። ይህ እንስሳ በዓለም አቀፍ ደረጃ በባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ብቻ ነው የሚገኘው።
"አንድ ግለሰብ ከውጪ አገር ሲመጣ ይህንን እንስሳ ለማደን 15 ሺህ ዶላር ወይንም በኢትዮጵያ ብር ወደ 800 ሺህ ብር የሚጠጋ ያወጣል" ይላሉ።
እኚህ ባለሙያ እንደሚሉት ይህንን እንስሳ ለማደን የሚመጣ ግለሰብ 15 ሺህ ዶላር ፈቃድ ለማግኘት ብቻ ያውጣ እንጂ በአጠቃላይ ከአገር እስኪወጣ ድረስ ከ 80 ሺህ በላይ ዶላር ሊያወጣ እንደሚችል ያስረዳሉ።
ይህም በኢትዮጵያ 4 ሚሊዮን ብር ያህል ማለት ነው።
ማደን የሚቻለው የት አካባቢ ነው?
የሚታደኑት እንስሳዎች ተለይተው እንደተቀመጡት ሁሉ፣ የት የት ቦታዎች ማደን ይቻላል የሚለውም በሕግ ላይ ተቀምጧል።
አቶ ጨመረ እንደሚሉት በኢትዮጵያ በብሔራዊ ፓርኮች እና የዱር እንስሳት መጠለያዎች ውስጥ አደን ማካሄድ አይቻልም።
"ለአደን ይሆናሉ ተብለው በጥናት ተለይተው የተከለሉ ቦታዎች ላይ በየሦስት ዓመቱ ቆጠራ ይካሄዳል። ኢትዮጵያ ውስጥ አራት ክልሎች ማለትም በኦሮሚያ፣ በደቡብ ሕዝቦች፣ በአፋር እና በሶማሊያ ክልሎች ውስጥ አደን ይካሄዳል።
ከእነዚህ ውስጥም 85 በመቶ የሚሆነው አደን የሚካሄደው በኦሮሚያ ውስጥ ነው።
ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ለአደን ከሚፈለጉት እንስሳቶች መካከል ለዓለም ገበያ የሚቀርቡት ሦስቱ የሚገኙት በኦሮሚያ ውስጥ ብቻ በመሆኑ ነው።
እነርሱም የደጋ አጋዘን፣ የምንሊክ ድኩላ እና የጭላዳ ዝንጀሮ ናቸው።
ሌላው ምክንያት ደግሞ "አደን ከሚካሄድባቸው ቦታዎች መካከል በመጀመሪያ ደረጃ የሚገኙት ኦሮሚያ ውስጥ በመሆኑ ነው" በማለት ሁለት ዓይነት የአደን ቦታዎች እንደሚገኙ ያስረዳሉ።
የመጀመሪያ የቁጥጥር አደን ቦታዎች እና ክፍት የአደን ቦታ በማለት ይለያሉ።
በሌላ በኩል ለአደን የሚውለው ቦታ ከፓርክ ድንበር ላይ ቢያንስ 5 ኪሎ ሜትር ርቆ መገኘት አለበት።
ስለዚህ ማደን የሚቻለው በእነዚህ በተከለሉ ስፍራዎችን ያሉ እንስሳቶችን ብቻ ነው።
ለምሳሌ በባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ አቅራቢያ የሚገኙ እንደ እነሀንቶ፣ ሸነን በርበሬ፣ በስመና ኦዶ ቡሉ እና አባ ሸባ ደመሮ የሚባሉ ቦታዎች ውስጥ የደጋ አጋዘንን ማደን ይቻላል።

የፎቶው ባለመብት, Shimelis Lemma
በአደን ላይ ያለው ተቃውሞ
ኢትዮጵያ ውስጥ በተደራጀ መልኩ ስለ እንስሳት አደን የሚሟገቱ አካላት ባይኖሩም ጋዜጠኛ ሔኖክ ስዩም ግን አደንን ከማይደግፉት ሰዎች መካከል አንዱ ነው።
በዓለም ላይ ለአደን ያለው አመለካከት የተከፋፈለ ነው። ለእንስሳት መብቶች እና ደህንነት የሚሟገቱ አካላት ለመዝናኛ ወይንም ለስፖርት በማለት እንስሳትን ማደን ጭካኔ፣ የማያስፈልግ እና ከሥነ ምግባር ውጪ ነው ይላሉ።
በእነዚህ እንስሳት ይደርሳል ያሉትን ሕመምና ስቃይ እንዲሁም ጭካኔ አጥብቀው ይቃወማሉ።
ለእንስሳት መብት እና አያየዝ የሚሟገተው መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ፔታ የተባለው ድርጅት በግንባር ቀደምትነት አደንን ከሚቃወሙ አካላት መካከል አንዱ ነው።
ይህ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት በዓለም ዙርያ 9 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አባላት እና ደጋፊዎች እንዳሉት ይናገራል።
ይህ ድርጅት እንደሚያምነው ከሆነ በሰው ልጅ የመቶ ሺህ ዓመታት ታሪክ ውስጥ አደን ለሰው ልጅ የመኖር ህልውና ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል።
አሁን ላይ ላለው የሰው ልጅ ግን በፍጹም የሚያስፈልገው ተግባር አይደለም ሲል ይገልጻል።
"ጭካኔ እየፈጸምን እንዝናና ካልሆነ በስተቀር አስፈላጊ አይደለም" ሲልም አጥብቆ ይሞግታል።
በተጨማሪም በዓለም ላይ ዝርያቸው ከጠፋ እንስሳት መካከል ለተወሰኑት አደን አስተዋጽኦ ማድረጉን ይገልጻል።
ታስማኒያን ታይገር [Tasmanian tiger] እና ግሬት ኦክ [great auk] የሚባሉ እንስሳት የጠፉት በዚሁ ምክንያት ነው ይላል ድርጅቱ።
የአደን ልምድ በሌላቸው የሚጎዱት አብዛኛዎቹ እንስሳት ለተራዘመ እና ስቃይ ለበዛበት ሞት ይጋለጣሉ።
ከዚህም ባሻገር አደን የእንስሳትን ከቦታ ቦታ መዘዋወር ሂደት ያዛባል፤ ቤተሰቦችንም ያጠፋል ይላል ፔታ።
"ተፈጥሮ ለራሱ የሚያስፈልገውን ነገር ያውቃል። ሥነ ምህዳሩ ካልተረበሸ እና ካልተነካካበት እንዴት ራሱን ማደስ እንዳለበት ያውቃል" ሲልም ይናገራል።
















