ቱሪዝም፡ ኢትዮጵያ የዱር እንስሳቶቿን በአግባቡ እየጠበቀች ነውን?

ስዋይን ቆርኬ፣ ቀይ ቀበሮ፣ የሜዳ አህያ፣ ዝሆን

የፎቶው ባለመብት, EWLA/Getty Images

ኢትዮጵያ በዱር እንስሳት ሀብት ስማቸው ከሚጠሩ አገራት መካከል ቀዳሚዋ ነች። በዓለም በርካታ ብርቅዬ እንስሳት ካላቸው አገራት መካከልም ስሟ በቀዳሚነት ይጠራል።

ነገር ግን እነዚህን ብርቅዬ እንስሳት በአግባቡ መጠበቅና መከታተል ባለመቻሉ እስካሁን እዚህ ግባ የሚባል ጥቅም አልተገኘባቸውም።

የዱር እንስሳትን በየምድባቸውና ዘርፋቸው መቁጠር፣ ስርጭታቸውን እንዲሁም አይነታቸውን መከታተልና መተንተን መሰረታዊ የጥበቃ ስራ ነው።

በተለይ በደቡብና ምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ አገራት ይህንን ስራ በአግባቡና በዘመናዊ መንገድ ሲያከናውኑ ይታያል።

ከኢትዮጵያም አንጻር በደንብ የተሟላም ባይሆን የተወሰኑ ስራዎች በተለይ እንደ ዋልያ ያሉ ብርቅዬ የሆኑ ዱር እንስሳት አስመልክቶ በየዓመቱ የቆጠራ ስራ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ይገልጻል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ አጠቃላይ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙትን የዱር እንስሳት የመቁጠርና መረጃውን በተገቢ ሁኔታ ማደራጀት ከፍተኛ አቅም እንደሚጠይቅ ይናገራሉ።

''ዘመናዊ ሎጂስቲክስ፣ የሰለጠነ የሰው ሃይል እንዲሁም ከፍተኛ በጀት ስለሚጠይቅ በዚህ ደረጃ ስራው ኢትዮጵያ ውስጥ አይሰራም። እንደ ዋልያ፣ የደጋ አጋዘን እና ቆርኬ ያሉ ብርቅዬ እንስሳት ብዛትና እንቅስቃሴ ይታወቃል። ክትትልም ይደረግባቸዋል። ነገር ግን መጠናቸው አነስተኛ የሆኑ አጥቢ እንስሳት እንዲሁም እንደ የሌሊት ወፍ ያሉ ዝርያዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የመረጃ ክፍተት አለ።''

በተለያዩ የአገሪቱ ፓርኮች የሚገኙ የዱር እንስሳት ከሞላ ጎደል ቆጠራ የሚደረግላቸው ቢሆንም ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ግን በቂ የሆነና አስተማማኝ መረጃ ማግኘት ከባድ ነው።

''ይሄ ቆጠራ የሚካሄደው የደረቅና እርጥብ ወራት ተብሎ ነው። ስርጭታቸውና ብዛታቸውም በትክክል የሚታወቀው በዚሁ መንገድ ነው''

ከቴክኖሎጂ አንጻር ከአየር ላይ የሚካሄድ ቆጠራ መኖሩን የሚናገሩት አቶ ኩመራ "ይህ ዘመናዊ የቆጠራ መንገድ በሌሎች በቱሪዝሙ በበለጸጉ አገራት የተለመደ ቢሆንም ለእኛ ግን በጣም ከባድ ነው። በዚህ በኩል በአግባቡ የሰለጠነ ባለሙያም ሆነ ለቆጠራ አገልግሎት የሚውሉ አውሮፕላኖች በበቂ ሁኔታ የሉንም።'' ሲሉ ያለውን ተግዳሮት ያስረዳሉ።

ቀይ ቀበሮ (አቢሲኒያ ዎልፍ)

የፎቶው ባለመብት, Education Images

የምስሉ መግለጫ, ቀይ ቀበሮ (አቢሲኒያ ዎልፍ)

ብርቅዬ እንስሳት

በኢትዮጵያ ብቻ እንደሚገኙ የተመዘገቡ ከ 55 በላይ አጥቢ እንስሰት እንዳሉ ዋና ዳይሬክተሩ፣ አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ነግረውናል።

ከአእዋፍ ደግሞ ከ18 በላይ የሚሆኑ ወፎች በኢትዮጵያ ብቻ ይገኛሉ።

ከተሳቢ ከ15 በላይ ብርቅዬ እንስሳት አሏት።

በውሃ እና በየብስ የሚኖሩ ተሳቢዎች ደግሞ ከ30 በላይ ናቸው። በተጨማሪም ከ600 በላይ የእጽዋት ዝርያዎች በኢትዮጵያ ብቻ እንደተመዘገቡ መረጃ አለ።

በነፍሳት ደረጃ ደግሞ በቂ ቆጠራና ክትትል ስላልተደረገላቸው ቁጥራቸው በትክክል ባይታወቅም በርካታ ብርቅዬ ነፍሳት እንዳሉ ይታመናል ብለውናል አቶ ኩመራ።

''ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት አንጻር በእጽዋትም ሆነ በእንስሳት በርከት ያሉ ብርቅዬ እንስሳት አሏት። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የመልክዓ ምድሩ አቀማመጥ ወሳኝነት አለው'' ይላሉ።

እንደ ዳይሬክተሩ ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ተራራ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ ጫካ፣ ቆላማ ቦታ ፣ ቀዝቃዛ ቦታ፣ በረሃ ፣ ረግረጋማ ስፍራዎች በብዛት አሉ። በርካታ የውሃ አካላትም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተሰራጭተው ይገኛሉ።

"እነዚህ ሁሉ ላሉን በርካታ ብርቅዬ እንስሳት አስተዋጽኦ አላቸው።''

በዘርፉ ከፍተኛ ጥቅም የሚያገኙ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ከኢትዮጵያ የተሻለ መልክዓ ምድር አቀማመጥና በርካታ ብርቅዬ እንስሳት ባይኖራቸውም ከኢትዮጵያ በተሻለ መልኩ ግን ጥቅም እያገኙበት እንደሆነ አቶ ኩመራ ያስረዳሉ።

''ሌሎች የአፍሪካ አገራት ከእኛ የሚበልጡት ባሏቸው የዱር እንስሳት ብዛትና ስርጭት ነው። በርካታ ብርቅዬ እንስሳት ባይኖራቸውም ያሉት የተለመዱ የዱር እንስሳት ግን በብዛት በተለያዩ ቦታዎች ይገኛሉ። ለምሳሌ ዝሆን፣ ጎሽ፣ ዜብራና ቀጭኔ በምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አገራት በበርካታ ቦታዎች በብዛት ይታያሉ'' ብለዋል።

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሰዎች በእንስሳቱ ላይ የሚያደርሱትን አሉታዊ ተጽዕኖን መቀነስ በመቻላቸው እንዲሁም ዘመናዊ የጥበቃና ክትትል ስራዎችን ስለሚሰሩ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ይናገራሉ።

የስዋይን ቆርኬ (የኢትዮጵያ ቆርኬ)

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Wild Life Authority

የምስሉ መግለጫ, የስዋይን ቆርኬ

በትኩረት የሚሰራባቸው የዱር እንስሳት

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኩመራ እንደሚሉት በአሁኑ ሰአት ከፍተኛ ትኩረት ተደርጎባቸው ክትትል የሚደረግባቸው የዱር እንስሳት አሉ።

''በሻሸመኔ አቅራቢያ በሰንቅሌ የእንስሳት መጠለያ ውስጥ ብቻ የሚገኙት የስዌይን ቆርኬዎች ወደ 800 አካባቢ እንደሆኑ መረጃው አለን።''

ይህ እንስሳ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኝ የዱር እንስሳ ነው። ቀደም ሲል በአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ፣ ያቤሎ የዱር እንስሳት መጠለያ፣ ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ይገኝ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ሰአት ግን ሙሉ በሙሉ ከነዚህ አካባቢዎች ጠፍቷል።

ዋልያ ደግሞ በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የሚገኝ ሲሆን ብዛቱም ወደ 900 መድረሱን ዳይሬክተሩ ነግረውናል። ''ይህ ብርቅዬ እንስሳ ከ1983 ዓ.ም. በፊት እስከ አለመታየት ደርሶ የነበረ ሲሆን ቁጥሩም ቢሆን ከ100 በታች ነበር።''

ከዚህ በተጨማሪ በባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የሚገኘው የደጋ አጋዘን እስከ 2 ሺ አካባቢ እንደሚሆን ይገመታል። ቀይ ቀበሮ ደግሞ በአጠቃላይ እንደ አገር ከ400 በላይ ነው ይላሉ አቶ ኩመራ።

ቀይ ቀበሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኝ ሲሆን በዓለም ደረጃ ለመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው ሥጋ በል የዱር እንስሳት መካከል አንዱ ነው።

ቀይ ቀበሮ በኢትዮጵያ ሰባት ስፍራዎች ላይ ይገኝ የነበረ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየተመናመነ መጥቶ፣ በአሁኑ ሰዓት ከ450 የማይበልጥ ብቻ እንደሚገኝ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ።

ቀይ ቀበሮዎች አኗኗራቸው በሕብረት ነው። አንዱ ቀበሮ በበሽታ ከተያዘ የቡድኑ አባላት መታመማቸው እና ለሞት መጋለጣቸው የተለመደ ነው።

ሰዎች ወደ ተከለሉ ፓርኮች ጥሰው በመግባት ኑሮ በመመስረታቸው የተነሳ የእብድ ውሻ በሽታ ከአካባቢው ውሾች በቀላሉ ወደ እንስሳቱ እየተላለፈ ለሞት እንደሚዳረጉ አክለው ይናገራሉ።

ምንም እንኳን አጠቃላይ ቁጥራቸው አሁንም አነስተኛ ቢሆንም የእነዚህ ብርቅዬ እንስሳት ቁጥር ቀስ በቀስ መጨመር ማሳየት የቻለው ባለፉት 20 ዓመታት በተሰሩ የጥበቃ ስራዎች እንደሆነ አቶ ኩመራ ያስረዳሉ።

ከእነዚህ ብርቅዬ የዱር እንስሳት በተጨማሪ ትልቁ የሜዳ አህያ (ግሬቪ ዜብራ)፣ ጥቁር አውራሪስ እና ዝሆን በከፍተኛ ደረጃ ቁጥራቸው የተመናመነ የዱር እንስሳት ሲሆኑ የመጥፋት አደጋም ተጋርጦባቸዋል።

እየተሰሩ ያሉ ራዎች

የዱር እንስሳት ቁጥር መመናመን በሁሉም አገራት የሚከሰት ሲሆን በዚህም የተነሳ በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ሀብት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ይገኛል።

ለዚህ ደግሞ የተለያየ ምክንያቶች ያሉት ሲሆን ዋነኛው ግን የሕዝብ ብዛት መጨመርና ፓርኮችና ጥብቅ ስፍራዎች ለመኖሪያነት ግልጋሎት መዋላቸው ነው።

ሕገወጥ አደን ያለባቸው አካባቢዎችም ለዱር እንስሳቱ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መመናመን እና መጥፋት ተጠቃሽ ምክንያት ሆኖ ይገኛል።

ብሔራዊ ፓርኮችና ሌሎች ጥብቅ ስፍራዎች ህጋዊ ሰውነት ኖሯቸው ዓለም አቀፍ መርሆዎችንና ደረጃዎችን ጠብቀው እንዲተዳደሩ ማድረግ በዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ስር አንዱ አላማ መሆኑን አቶ ኩመራ ነግረውናል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ባለስልጣኑ በመጀመሪያ ጥብቅ ስፍራዎችን ማቋቋምና ሕጋዊ ማድረግ፣ ለጥብቅ ሥፍራዎች ማኔጅመንት ፕላን ማዘጋጀትና ተግባራዊ ማድረግ፣ በዱር እንስሳት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ የልማት እንቅስቃሴዎችን መቀነስ እንዲሁም የአስተዳደሩንና ማኔጅመንት ፕላኑን ተግባራዊ ለማድረግ አዋጅ፣ደንብና መመሪያ ማዘጋጀት ትኩረት ሰጥተን በመስራት ላይ ነን ይላሉ።

በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙና የመጥፋት ስጋት ያለባቸው የዱር እንስሳት ልዩ ጥበቃ ማድረግ፣ እንስሳቱ እንዲጠኑና ባሉበት ቦታ እንዲጠበቁ ማድረግና ስጋት ላይ ያሉ እንስሳትን ወደ ምቹ ቦታዎች እንዲዛወሩ እስከማድረግ ጭምር የሚሰሩ ስራዎች መኖራቸውን ይገልጻሉ።

በተጨማሪም የግል ባለሃብት፣ ማህበረሰብ፣ መንግሥት ሁሉም ኃላፊነት እንዳለበት አቶ ኩመራ አሳስበዋል። በዘርፉም የባለሀብቶች ጥያቄም እየጨመረ መምጣቱን ይናገራሉ።

''ባለሀብቶች በጥብቅ ቦታዎች በሎጅ ኢንቨስትመንት ለመሰማራት እንዲሁም ከመንግሥት ጋር በጥምረትና በቅንጅት የተወሰኑ ብሄራዊ ፓርከችን ለማስተዳደር የተወሰኑ ጥያቄዎች እየመጡ ነው። ይህ ደግሞ አቅማችንን እየጨመረው እንደሚመጣ ይታሰባል። በዚህም የጥበቃና ቆጠራ ስራው በአግባቡ መከናወን ይችላል ማለት ነው''