ጸያፍ ቃል የሚያወጡት በቀቀኖች

የፎቶው ባለመብት, LINCOLNSHIRE WILDLIFE PARK
በዱር እንስሳት ፓርክ ውስጥ ለዕይታ ይቀርቡ የነበሩት አምስት በቀቀኖች ጎብኚዎች ላይ ጸያፍ ቃል ማውጣት በመጀመራቸው ለዕይታ እንዳይቀርቡ መደረጉ ተነገረ።
ዝርያቸው ከአፍሪካ የሆኑት ግራጫዎቹ በቀቀን ወፎች በዩናይትድ ኪንገደም በሚገኘው የዱር እንስሳት ፓርክ ውስጥ ለዕይታ ይቀርቡ ነበር።
ይሁን እንጂ ወፎቹ ጎብኚዎቹ ባሉበት ላባቸውን እያማቱ ጸያፍ ቃል ማውጣት በመጀመራቸው ለዕይታ ወደሚጋረዱበት የፓርክ ክፍል እንዲዘዋወሩ ተደርጓል ተብሏል።
የፓርኩ ሠራተኞች ወፎቹ ወደ ፓርኩ በመጡ ወቅት አስደሳች ስሜት ተፈጥሮባቸው እንደነበር ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ጸያፍ ቃላቶችን ማውጣት መቀጠላቸው ያልተጠበቀ ነው ይላሉ።
የፓርኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስቲቭ ኒኮላስ እንደሚሉት ከሆነ ወፎቹ ይህን መሰል ጸያፍ ቃል የሚያወጡት የሰዎች ትኩረት እና ምላሽ ለማግኘት ነው።
በቀቀኖቹ ጸያፍ ቃሉን ሲያወጡ ሰዎች ከሳቁ ወይም በአግራሞት ከተመለከቷቸው ቃሉን ደጋግመው እንዲያወጡት ያበረታታቸዋል።
"አንዳንድ ጎብኚዎች ይህንን የበበቀኖቹን ያልተገባ ተግባር አስቂኝ ሆኖ ያገኙታል። ቅዳሜ እና እሑድ ላይ ግን ሕጻናት ጎብኚዎቹ ስለሚኖሩ ወፎቹን ወደ ሌላ የፓርኩ ክፍል ለማዘዋወር ወስነናል" ብለዋል ኃላፊው።
ኃላፊው ጨምረው፣ "ወደ ሌላኛው የፓርክ ክፍል ሲዘዋወሩ ሌሎች ቃሎችን ይማራሉ ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ። ግን በሌላ የፓርኩ ክፍል ውስጥ የሚገኙ 250 በቀቀኖችን ጸያፍ ቃል የሚያስተምሩ ከሆነ ምን ማድረግ እንደምንችል እርግጠኛ አይደለንም" ብለዋል።
በዚህ ፓርክ ውስጥ በቀቀኖች አግራሞትን የሚጭር ነገር ሲፈጥሩ ይህ የመጀመሪያ አይደለም።
በ2020 መጀመሪያ ላይ ቺኮ የተባለው በቀቀን የቢዮንሴን 'ኢፍ አይ ዌር ኤ ቦይ' የተሰኘውን ዘፈን በመዝፈን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ቺኮ በአሁኑ ወቅት የራሱ ኢንስታግራም ገጽ ተከፍቶለታል።












