ኬኒያ የቱሪዝም ምንጭ የሆኑ የዱር እንስሳቶቿን ልትቆጥር ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP
ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኬኒያ በታሪኳ ለመጀመሪ ግዜ የዱር እንስሳት ቆጠራ ለማካሄድ ዛሬ አርብ ዘመቻ ትጀምራለች።
ቆጠራው በምስራቃዊው የአገሪቱ ክፍል በሚገኘው የሺምባ ኮረብታዎች እንደሚጀመር የኬኒያ የዱር እንስሳት አገልግሎት አስታውቋል።
ተቋሙ እንዳለው ቆጠራው አጠቃላይ የዱር አራዊቱን ቁጥር ለማወቅ ብሎም በየአካባቢው ያላቸውን አሰፋፈር ለመረዳት ያግዛል።
እንዲሁም ከአመት አመት የዱር እንስሳት አሰፋፈር እና ቁጥር ላይ ያለውን ልዩነት ለማወቅ ብሎም የዱር እንስሳት ጥበቃ አደጋዎችን ለመለየት ያስችላልም ተብሏል።
የዱር እንስሳት አገልግሎቱ ከ ዱር እንስሳት ጥናት እና ስልጠና ተቋም ጋር በጋራ ቆጠራወን ያከናውናል።
ዘ ቢግ ፋይቭ በመባል የሚታወቁት የኬንያ ዱር እንስሳት የሃገሪቱ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ናቸው።
እነዚህ አምስቱ እንስሳት በቀደመው ጊዜ በአዳኞች ዘንድ ለማደን አስቸጋሪ ተደርገው የሚቆጠሩ እንስሳት ናቸው።
ኬንያ፤ የዱር እንስሳትን በተለመከተ ጠበቅ ያለ ሕግ አላት። የዱር እንስሳትን ማደንም ሆነ ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴያቸውን ማደናቀፍ ያስቀጣል።
ዝሆን፣ አናብስት፣ ነብር፣ የኬፕ ጎሽና አውራሪስ [ሪኖ] ለማየት በየዓመቱ ሚሊዮኖች ወደ ኬንያ ይጓዛሉ።
ከእነዚህ አምስት ግዙፍ የዱር እንስሳት በተጨማሪ ከታንዛኒያ ወደ ኬንያው ማሳይ ማራ ብሔራዊ ፓርክ የሚተሙ እንስሳትን ለማየት በርካታ ጎብኚዎች ይመጣሉ።
ነገር ግን አምና የከተሰተውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ የሃገሪቱ ቱሪዝም መስክ እጅግ ተጎድቷል።
የኬንያ መዲና ናይሮቢ መሃል ከተማ ብሔራዊ ፓርክ ያላት ብቸኛዋ የዓለማችን መዲ ናት።













