ዩክሬን ግዙፏን የሩሲያ መርከብ ያሰጠመችው አሜሪካ የደኅንነት መረጃ አቀብላት ነው ተባለ

ሞስኮቫ ከመስመጧ በፊት

የፎቶው ባለመብት, MAX DELANY/AFP

የምስሉ መግለጫ, ሞስኮቫ ከመስመጧ በፊት

ዩክሬን የሩሲያ ብሔራዊ ኩራት ነበረች የተባለችውን ግዙፏን ሞስኮቫ መርከብ በሚሳኤል መትታ ያሰጠመችው የመርከቧን ትክክለኛ መገኛ ከአሜሪካ ጥቆማ ካገኘች በኋላ ነው ተባለ።

በርካታ መገናኛ ብዙኃን ዩክሬን ወደ ኦዴሳ ወደብ እየቀዘፈች ያለችው የትኛዋ መርከብ እንደሆነች እና መገኛ ስፍራዋን አሜሪካ እንድታሳውቃት ጠይቃለች ሲሉ ዘግበዋል።

አሜሪካ የመርከቧን መገኛ ለዩክሬን ካሳወቀች በኋላ ዩክሬን ሞስኮቫን በሁለት ሚሳኤሎች መትታ አስጥማታለች ሲሉ ስማቸው ያልተጠቀ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ከታላቋ ሶቭየት ኅብረት ጀምሮ ለሩሲያ በርካታ ግልጋሎት የሰጠችው ሞስኮቫ፤ በሩሲያውያን ዘንድ እንደ ብሔራዊ ኩራት ተደርጋ ትታይ ነበር።

መርከቧ የሰመጠችበት ሁኔታ ብዙዎችን ሲያወዛግብ ቆይቷል። የዩክሬን ባለሥልጣናት ራሳችን ባመረትነው ናፕቹን በሚባል ሚሳኤል መትተን አስምጠናል ሲሉ፤ ሞስኮ በበኩሏ በወጀብ ምክንያት በተቀሰቀሰ እሳት ሳቢያ የታጠቀችው መሳሪያ ፍንድቶ ለመስጠሟ ሰበብ ሆኗል ትላለች።

በሞስኮቫ መስመጥ ጉዳይ እስካሁን ድረስ የአሜሪካ ድርሻ ምን እንደሆነ ፔንታጎን ያለው ነገር የለም። ይሁን እንጂ የባይደን አስተዳደር ቃል አቀባይ ዩክሬን እራሷን መከላከል እንድትችል ዋሽንግተን ለኪዬቭ የደኅንነት መረጃ ትሰጣለች ብለዋል።

በስም ያልተጠቀሱ የአሜሪካ ባለሥልጣናት አሜሪካ የመርከቧን መገኛ መረጃ ለዩክሬን ስታሳውቅ ዩክሬናውያኑ ሞስኮቫን ዒላማ እንደሚያደርጓት ዋሽንግተን አላወቀችም ነበር ብለዋል።

የሩስያ የጦር መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Mike Right/Twitter

የምስሉ መግለጫ, የሞስኮቫ መስመጥ ለሩሲያ ጦር ትልቅ ኪሳራ ሆኖ ተመዝግቧል።

ሚሳኤል ተሸካሚዋ መርከብ ላይ የነበሩት 510 የባሕር ኃይል አባላት ሩሲያ ዩክሬን ላይ ስታደርግ የነበረውን የባሕር ላይ ጥቃት ሲመሩ ነበር።

ፀረ ሚሳኤል፣ የአየር መቃወሚያ፣ ፀረ ሰርጓጅ መርከብ እና ሌሎች እጅግ ውስብስብና ግዙፍ መሣሪያዎች ታጥቃ የነበረችው ሞስኮቫ፤ መስጠም ለሩሲያ ጦር ትልቅ ኪሳራ ሆኖ ተመዝግቧል።

አሜሪካ የሞስኮቫ መርከብን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ትሰጣለች ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢይ አሜሪካ የሩሲያ ጦር አዛዦች መገኛ ቦታን ለዩክሬን እያሳወቀች የዩክሬን ሠራዊት እንዲገድላቸው እያደረገች ነው የሚለውን የሚዲያ ሪፖርት አጣጥለዋል።

"በጦር ሜዳ ያሉ ዋና የጦር መሪዎች መገኛ መረጃን አንሰጥም፣ እንዲሁም የዩክሬን ጦር የዒላማ ውሳኔን በተመለከ ተሳትፎ አናደርግም" ብለዋል ቃል አቀባዩ።

ከፔንታጎን በተጨማሪ የዋይት ሐውስ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት፣ ዩክሬን የሩሲያ ጦር ጀነራሎችን ዒላማ እንድታደርግ አሜሪካ ረድታለች የሚለውን የሚዲያ ዘገባዎች አጣጥሏል።

ምንም እንኳ አሜሪካ የደኅንነት መረጃዎችን ለዩክሬን አላቀብልም ብትልም የባይደን አስተዳደር የዩክሬንን ጦርን እና ምጣሄ ሃብት ለመደገፍ እንዲሁም ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ኮንግረሱ 33 ቢሊዮን ዶላር እንዲፈቅድላቸው ጠይቋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ ምዕራባውያኑ ሩሲያ ላይ በርካታ ማዕቀቦችን ከመጣል አልፈው፤ ከአሜሪካ በተጨማሪ ዩናይትድ ኪንግደም እና በርካታ የአውሮፓ አገራት ለዩክሬን ጦር ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ከዚህ ቀደም የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምዕራባውያኑ የዩክሬን ጦርን መደገፋቸው ለአውሮፓ አህጉር አደጋ ነው ብሎ ነበር።