በኦሮሚያ ክልል ወረ ጃርሶ ወረዳ በርካታ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Warra Jarso Communication
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረ ጃርሶ ወረዳ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች በርካታ ሰዎችን መግደላቸውን እና ቤተሰቦች አስክሬን ተከልክለው ቀብር መፈጸም አለመቻላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሟች ቤተሰቦች እና ነዋሪዎች ማክሰኞ ሚያዚያ 25/2014 ዓ.ም. 18 ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
የወረዳው አስተዳዳሪ በበኩላቸው የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ18 ያነሰ እና "ከጠላት ጋር የነበሩ ናቸው" ብለዋል። የክልሉ አስተዳደር እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ ስለ ክስተቱ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የክልሉ መንግሥት 'ኦነግ ሸኔን የማጽዳት ዘመቻ ጀምሪያለሁ' ካለ በኋላ ባለፉት ሳምንታት ሰላማዊ ሰዎች በተለያዩ ቦታዎች መገደላቸው በስፋት እየተነገረ ነው።
የሆነው ምንድነው?
ነዋሪዎች እንደሚሉት ማክሰኞ ሚያዚያ 25/2014 ዓ.ም. በወረ ጃርሶ ወረዳ አዋሮ ጎልጄ ቀበሌ በዳዳ ገብርኤል ተብሎ በሚጠራ ስፍራ 18 ሰዎች ተገድለዋል።
ሰዎቹ ከመገደላቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ማለትም ሰኞ ሚያዚያ 24/2014 ዓ.ም. ጠዋት ላይ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ወደ ወረዳዋ መምጣታቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ልጃቸው በፀጥታ ኃይሎች እንደተገደለባቸው የሚናገሩት ስማቸውን የማንጠቅሰው አባት፤ "[ሰኞ] ጠዋት በግምት 12፡15 ላይ ከብቶች አውጥተን ቆመን ነበር። 'ኑ' ብለው ጠሩን [የፀጥታ ኃይሎች] ከዚያ 'ትክክለኛ ሸኔ አሁን አገኘን' ብለው ልጄን ያዙት። ወዲያው ኮቱን አስወልቀው እጁን ወደ ኋላ አሰሩት" ይላሉ።
በቀጣይ ቀን ማክሰኞች ሚያዚያ 25 በመንግሥት ኃይሎች የተያዘባቸውን ልጃቸውን ለመጠየቅ ልብስ እና ምግብ ይዘው የመንግሥት ኃይሎች ወዳሉበት ካምፕ መሄዳቸውን እኚህ አባት ይናገራሉ። ". . . ሕግ ነው ያሰረው ብዬ ማክሰኞ ምግብ እና ልብስ ይዤ ልጄን ልጠይቀው ወደ ካምፕ ሄድኩ" ይላሉ።
ይሁን እንጂ ልጃቸውን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ማክሰኞ ንጋት 11 ሰዓት ላይ መገደላቸውን ዋሻ ሚካኤል ጸበል ለመጠመቅ ከሚሄዱ ሰዎች መስማታቸውን ይናገራሉ።
"መንግሥት የማያውቃቸውን ልጆቻችንን ጨረሰብን" በማለት ልጃቸው ከሕግ ፊት ሳይቀርብ መገደሉን ይናገራሉ።
ልጃቸው የታጣቂ ቡድኑ አባል ወይም ከታጣቂ ቡድኑ ጋር አንዳች ግንኙነት እንዳለው የተጠየቁት አባት፤ "በጭረሽ" ሲሉ መልሰዋል።
"ከእነሱ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ከአጠገቤ ተለይቶ አያውቅም። ከሰው ጋር ተጣልቼ እጄ ተሰብሮ ከ10ኛ ክፍል አቋርጦ እኔ ለመርዳት ወደ እርሻ ተመልሶ ነበር" በማለት ይናገራሉ።
'ሦስት ዘመዶቼ ናቸው የተገሉብኝ'
ሌላኛው ቢቢሲ ያነጋገረው ነዋሪ ደግሞ ወንድሙ እና ሁለት የአጎቱ ልጆች በዕለቱ መገደላቸውን ይናገራል። ሁለቱ በ20ዎቹ የእድሜ ክልሎች ውስጥ ሲገኙ ሦስተኛው ደግሞ ዕድሜው 20 መሆኑን ያስረዳል።
ይህ ነዋሪ ከተገደሉት ሦስቱ መካከል ሁለቱ የቤተክርስቲያን አገልጋይ ዲያቆኖች መሆናቸውን አንዱ ደግሞ ለፋሲካ በዓል ከአዲስ አበባ ወደ ከተማ የሄደ መሆኑን በመናገር ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የላቸውም ይላል።
ሦስቱ ወጣቶች ሰኞ ተይዘው ማክሰኞ መገዳላቸውንም ይናገራል።
ቢቢሲ ያነጋገረው ሌላኛው ነዋሪ ደግሞ በዕለቱ ከተገደሉት 18 ሰዎች መካከል 14ቱ ከእነርሱ ጎጥ መሆናቸውን ጠቅሰው "ከእኛው አካባቢ ነው ይዘዋቸው የሄዱት። እስር ቤት ያስገቧቸዋል ብለን ስንጠብቅ ገደሏቸው። እስካሁን አልተቀበሩም" ይላሉ ነዋሪው።
ይህ ነዋሪ ከሟቾች መካከል የቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑ ዲያቆኖች፣ በጉልበት ሥራ የሚተዳደሩ እና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደሚገኙበት ይናገራሉ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸውን የሟች ቤተሰቦችና ዘመዶች ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸውን አይጠቅስም።

የፎቶው ባለመብት, ወረ ጃርሶ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ
ከላይ ያለው ምስልን ያጋረው 'የወረ ጃርሶ ወረዳ ብልጽግና' የፌስቡክ ገጽ ሲሆን፣ ከተለየ አቅጣጫ የተነሳ ተመሳሳይ ምስልም በወረዳው ኮሚኒኬሽን አማካይነት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተጋርቷል።
ቢቢሲ ከሟች ቤተሰቦች እንደተረዳው በዚህ ምስል ላይ ከሚታዩት ሰዎች መካከል ቢያንስ ሁለቱ በፀጥታ ኃይሎች በተወሰደባቸው እርምጃ ከተገደሉት ውስጥ ናቸው።
ቢቢሲ ዛሬ አርብ ሚያዚያ 28/2014 ዓ.ም. ረፋድ ላይ የቤተሰብ አባላትን መልሶ ያነጋገረ ሲሆን፤ ማክሰኞ ሚያዚያ 25/2014 ዓ.ም. ንጋት ላይ የተገደሉት ሰዎች አስክሬን እስካሁን አልተነሳም።
"አስክሬን ስጡን ስንላቸው 'እናተም መጨመር ፈላጋችሁ' አሉን። . . . አውሬ እና አእዋፍ እየበላው ነው (አስክሬኑን)። ምን እናደርግ? አስክሬን ሰጥተውን ከመቅበር ውጪ ሌላ ምን እንፈልጋለን?" ሲሉ ልጃቸው የተገደለባቸው አባት ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Warra Jarso Communication/ screen shot
የመንግሥት ምላሽ
ከግድያው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሰኞ ሚያዚያ 24/2014 ዓ.ም. የወረ ጃርሶ ወረዳ ኮሚኒኬሽን በፌስቡክ ገጹ "የኦነግ-ሸኔ አባላት" ናቸው ያላቸው 18 ሰዎች መያዛቸውን ገልጾ ከዚህ በላይ ያለውን ምስል አጋርቷል።
የወረ ጃርሶ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አየለ መንግሥቱ ትናንት ሐሙስ እንደተናገሩት የተገደሉት "ከጠላት ጋር የነበሩ ናቸው" ብለዋል። "አብዛኛዎቹ የተያዙት ከጠላት ጋር የነበሩት ናቸው። ከዚያ ውጭ ደግሞ ማን አለበት የሚለውን እያጣራን ነው። ከአገር መከላከያ ጋር እያጣራን ነው" ሲሉ መልሰዋል።
የሕዝብ ጥያቄን ተከትሎ የመንግሥት ፀጥታ ኃይል በወረዳው ተሰማርቶ "የማጽዳት ሥራ እየሰራ ነውም" ብለዋል።
"የፀጥታ ችግር ባለበት አካባቢ ንጹሃን ሰዎች ሊጎዱ ስለሚችሉ" ከተገደሉት ሰዎች መካከል ንጹሃን ሰዎች ስለመኖራቸው እየተመረመረ ነው ብለዋል።
አቶ አየለ፤ "18 አይደርሱም [የተገደሉት ሰዎች ቁጥር] ግን የተገደሉ ሰዎች አሉ" በማለት ተናግረዋል።
ቢቢሲ ተጨማሪም ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ክልሉ የአስተዳደር እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ ስልክ ደውሎ ነበር። ኮሎኔል አበበ ስለጉዳዩ "አላውቀም" ሲሉ አጭር ምላሸ ሰጥተዋል። መሰል ድርጊት ከእርሳቸው እውቅና ውጪ ሊፈጸም እንደሚችል ቢቢሲ ላቀረበላቸው ጥያቄ፤ "እኔ እንደዚህ አይነት ትዕዛዝ አልሰጠሁም፤ አላውቀም" ሲሉ መልሰዋል።
"ሸኔን የማጽዳት ዘመቻ"
ከሰሞኑ መንግሥት 'ሸኔ' ብሎ የሚጠራውን ታጣቂ ቡድን "የማጽዳት ዘመቻ" ጀምሬያለሁ ካለ በኋላ በሁለቱ አካላት መካከል የሚደረገው ግጭት ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ይህን ተከትሎ ባለፉት ሳምንታት በተለይ በምዕራብ ሸዋ ዞን በሚገኙ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች ስለመገደላቸው በስፋት ተዘግቧል።
ከእነዚህ መካከል አርብ ሚያዚያ 21/2014 ዓ.ም. ምዕራብ ሸዋ ዞን አደአ በርጋ ወረዳ የተገደሉት ሰዎች ይገኙበታል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በዕለቱ ከ20 የማያንሱ ነዋሪዎች በወረዳው ጂማታ ተብላ በምትጠራ ቦታ በኦሮሚያ ልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት መገደላቸውን ተናግረው ነበር።
ይህ ግድያ የተከሰተው በክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ላይ በአካባቢው የነበሩ ታጠቂዎች ጥቃት ሰንዝረው ግድያ ከፈጸሙ በኋላ መሆኑንም ነዋሪዎች ገልጸዋል።












