በኦሮሚያ ክልል አደአ በርጋ ወረዳ በርካታ ሰዎች በኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላት መገደላቸው ተነገረ

ሆለታ ከተማ ከአደአ በርጋ ወረዳ በቅርብ ርቀት ይገኛል።
የምስሉ መግለጫ, ሆለታ ከተማ ከአደአ በርጋ ወረዳ በቅርብ ርቀት ይገኛል።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን አደአ በርጋ ወረዳ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት በርካታ ንጹሃን ሰዎችን መግደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ዛሬ ከሰዓት ቢቢሲ ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ክልል ፀጥታ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ በበኩላቸው፣ "ይህ ውሸት ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

እንደ ነዋሪዎች ከሆነ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ አባላት ትናንት አርብ ሚያዚያ 21/2014 ዓ.ም. በነዋሪዎች ላይ ግድያ የፈጸሙት ከአንድ ቀን በፊት ታጣቂዎች የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላትን ከገደሉ በኋላ ነው።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የአካባቢው ነዋሪዎች ትናንት አርብ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ቢያንስ 21 ይሆናሉ ሲሉ ሌላኛው ነዋሪ ደግሞ የሟቾች ቁጥር ወደ 40 ይጠጋል ብለዋል።

በአካባቢው በስፋት የሚንቀሳቀሰው እና ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ጦርነት ውስጥ የሚገኘው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን ትናንት በመንግሥት ኃይሎች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 46 መሆኑን ጠቅሶ ከተገደሉት መካከል የ15 ሰዎችን ስም ዝርዝር አውጥቷል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በበኩሉ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በአደአ በርጋ ወረዳ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች 15 ንጹሃን ዜጎችን ገድለዋል ብሏል።

ከተገደሉት ንጹሃን ዜጎች መካከል የ70 ዓመት አዛውንት እንደሚገኙበት መግለጫው ጠቁሞ "የታጠቁት ኃይሎች ገንዘብ፣ ጌጣጌጥ እና ሌላም ቁሳቁስ እየዘረፉ እንዲሁም የሰዎችን መኖሪያ እያቃጠሉም ነው" ሲል አክሏል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በአሁን ወቅት ሕይወታቸውን ለማዳን ወደ ጫካ እየሸሹ እንደሆነም የኦነግ መግለጫ ያመለክታል።

ሐሙስ እና አርብ ያጋጠመው ምንድነው?

ሐሙስ ሚያዚያ 20/2014 ዓ.ም. የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላት በወረዳው በሚገኝ ገጠራማ ስፍራ በፒክ አፕ መኪና ተጭነው ሲጓዙ ድንገተኛ ጥቃት በታጣቂዎች ተፈጽሞባቸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በዚህ ጥቃት ከ10 የማያንሱ የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት መገደላቸውን እና ቢያንስ 3 ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

በልዩ ኃይል አባላቱ ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት ተከትሎ በቀጣይ ቀን ማለትም አርብ ሚያዚያ 21/2014 ዓ.ም. በወረዳው በሚገኙ ኢንጪኒ፣ ሙገር፣ ሬጂ እና ጂማታ ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች ከፍተኛ ውጥረት ነግሶ ነበር ይላሉ ነዋሪዎች።

"በጂማታ ቤት ለቤት እየዞሩ ፍተሻ እያደረጉ ሰዎችን መግደል ጀመሩ" ሲሉ አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ሬሳ በቤት ውስጥ፣ በየጓሮ፣ ከዋናው መንገድ ዳር ሁሉ ይታይ ነበር" ሲሉ በጂማታ ከተማ የነበሩ እና አሁን በሆለታ ከተማ የሚገኙ ነዋሪ ነግረውናል።

የፖሊስ አባላቱ በነዋሪዎች ቤት ላይ ብርበራ ሲፈጽሙ እና ሲገድሉ፤ 'ሸኔን የምትደብቁት እናንተ ናችሁ' ሲሉ እንደነበረ በቦታው ካለ ነዋሪ እንደሰሙ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪ ይናገራሉ።

የኢንጪኒ ከተማ ነዋሪ ደግሞ ከሰዎች መኖሪያ ቤት የወጡ ታጣቂዎች በልዩ ኃይል አባላቱ ላይ ጥቃት ካደረሱ በኋላ የፖሊስ አባላቱ በቀጣይ ቀን በነዋሪዎች ላይ ግድያ መፈጸማቸውን ተናግረዋል።

ነዋሪው ትናንት አርብ ምሽት በከተማዋ በሚገኝ ሆስፒታል "ብዙ ግርግር ነበር" ብለዋል። "ሁሉም ስለሚፈራ ወደዛ ሄደን ምን እየተካሄደ እንደሆነ አልጠየቅንም" ሲሉ ተናግረዋል።

ከግድያው በተጨማሪ በጂማታ በርካታ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ከነዋሪዎች መረዳት ተችሏል።

የኦሮሚያ ክልል ፀጥታ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ፣ "ይህ ውሸት ነው። እንደዚህ ዓይነት ሪፖርት አልደረሰንም" ሲሉ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።

ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ሌሎች ጥያቄዎች ብናቀርብም "ሐሰት ነው" ከሚለው በዘለለ የገለጹልን ነገር የለም።

ስለ ጉዳዮ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ መንግሥት ኮምንኬሸን አገልግሎት ዶ/ር ለገሰ ቱሉ እንዲሁም ሰላማዊት ካሳ ብንደውልም ስልክ ስላልተነሳ ምላሽ ማካተት አልቻልንም።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ስለተፈጠረው ነገር መረጃ እንዳለው ለመጠየቅ ወደ ሕዝብ ግንኙት ባልደረባዎች ብንደውልም አልተሳካም።

line

ከሰሞኑ መንግሥት 'ሸኔ' ብሎ የሚጠራውን ታጣቂ ቡድን "የማጽዳት ዘመቻ" ጀምሬያለሁ ካለ በኋላ በሁለቱ አካላት መካከል የሚደረገው ውጊያ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው እና የፌደራሉ መንግሥት አሸባሪ ሲል የፈረጀውን 'ሸኔ' ቡድን ለማጥፋት ለአንድ ወር የሚዘልቅ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሩን የክልሉ መንግሥት ከጥቂት ሳምንታት በፊት አስታውቆ ነበር።

ይህን ተከትሎ ባለፉት ሳምንታት በተለይ በምዕራብ ሸዋ ዞን የፌደራሉ መንግሥት በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) የታዘገ ጥቃት ሲያካሂድ መቆየቱ ተዘግቧል።

ክልሉ ከቀናት በፊት "ሸኔን የማጽዳት" ዘመቻው ተጠናክሮ መቀጠሉን እና ይህ ወታደራዊ ዘመቻ የተፈለገለትን ዒላማ እያሳካ እንደሆነ በመግለጫ አውጥቶ ነበር።

ይሁን እንጂ የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ፤ "ወታደሮቻችን እየተዋጉ ነው። ድል እንጂ ሽንፈት አልገጠመንም። . . . ከ400 በላይ ወታደር ማርከናል። የተለያዩ ጦር መሣሪያዎችን ማርከናል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።