ከእስር እንዲለቀቁ የተፈረደላቸው ኬንያዊው ሼኽ ወህኒ ቤት ለመቆየት ጠየቁ

ሼክ ጉዮ ጎርሳ ቡሩ ያሉበት ካሚቲ እስስ ቤት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ሼክ ጉዮ ጎርሳ ቡሩ ያሉበት ካሚቲ እስስ ቤት

ኬንያዊው ሼኽ ለዓመታት ታስረው ከቀረበባቸው ክስ ፍርድ ቤት በነጻ ቢያሰናብታቸውም በእስር ቤት እንዲቆዩ እንዲፈቀድላቸው ጠየቁ።

ሼኽ ጉዮ ጎርሳ ቡሩ ከአራት ዓመት በፊት ተይዘው ከእስላማዊው ታጣቂ ቡድን አልሻባብ ጋር በመተባበርና የሽብር ቡድኑን የሚያስተዋውቁ ቁሳቁሶችን ይዘው በመገኘት ክስ ተመስርቶባቸው ነበር።

ጉዳያቸውን ሲመለከት የቆየው የኬንያ ፍርድ ቤት፣ ዐቃቤ ሕግ በግለሰቡ ላይ ያቀረበውን ክስ ማረጋገጥ ባለመቻሉ በዚህ ሳምንት ከአስር እንዲለቀቁ ወስኗል።

ነገር ግን ሼኽ ጉዮ ጎርሳ ቡሩ ከ እስር ቤቱ ውጪ ለደኅንነታቸው ስለሰጉ እጅግ አስቸጋሪ ከሚባለውና ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግለት ካሚቲ እስር ቤት አልወጣም ብለዋል።

ግለሰቡ ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ በመንግሥት ታፍነው ሊገደሉ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ለፍርድ ቤት የገለጹ ሲሆን፣ አቤቱታቸውን የሰሙት ዳኛም ሼክ ጉዮ በ እስር ቤቱ ከ30 ቀናት ላልበለጠ ጊዜ እንዲቆዩና በአስር ቤቱ ለሚቆዩበት ጊዜም ለመንግሥት አስፈላጊውን ክፍያ እንዲፈጽሙ አዘዋል።

ይህንንም ተከትሎ ሼኽ ጉዮ ከእስር ቤት ሲወጡ መንግሥት ለደኅንነታቸው ጥበቃ እንዲያደርግ ሌላ መዝገብ በኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስከፍተዋል።

ሼኽ ጉዮ ያቀረቡት ስጋት በኬንያ ውስጥ የሚያጋጥመው የሰዎች በኃይል የመሰወር ጉዳይን በድጋሚ ዋነኛ መነጋገሪያ አድርጎታል።

በቅርቡ የወጣ የአምነስቲ ኢንትርናሽናል ሪፖርት እንዲሁም ሌሎች የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ቡድኖችም ኬንያ ውስጥ እየጨመረ ለመጣው የጭካኔ ድርጊት፣ ከሕግ ውጪ ግድያና አፈና ፖሊስን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

የአገሪቱ ብሔራዊ የፖሊስ አገልግሎት ግን በመብት ተቆርቋሪዎች የሚቀርብበትን ክስ አይቀበለውም።።

ሼክ ጉዮ ጎርሳ ቡሩ በኬንያ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ከአራት ዓመት በፊት በሰሜናዊ ኬንያ ማርሳቢት ከተማ ውስጥ በሚገኝ ሃይማኖታዊ ውስጥ ነበር።

ሼክ ጉዮ ሕገ ወጥ ከሆነው የሶማሊያ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን ጋር ይተባበራሉ ተብለው የተያዙ ሲሆን፣ የቡድኑ አባል ናቸው የሚለውን ጨምሮ 11 ክሶች ቀርበውባቸው ነበር።

የግለሰቡ ጉዳይ ለአራት ዓመታት በፍርድ ቤት ሲታይ የቆየ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ ክሱን የሚያረጋግጥ በቂ ማስረጃ አላቀረበም በሚል ሼክ ጉዮ ጎርሳ ቡሩ ከአስር እንዲወጡ ተወስኖላቸዋል።