የምዕራባውያንን ማዕቀብ ለሚሸሹት ሩሲያውያን መሸሸጊያ የሆነችው ዱባይ

ዱባይ ማሪና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ ከቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ የሩሲያ ባለጸጎች ከምዕራባውያን ማዕቀበ ለማምለጥ ዱባይን መዳረሻቸው እያደረጉ ነው።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቢሊየነር ሩሲያዊያን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትሷ ዱባይ እየገቡ ነው።

አንድ ሪፖርት በመጀመሪያዎቹ የ2022 ሦስት ወራት ዱባይ ውስጥ በሩሲያ ባለሀብቶች የተገዙ ንብረቶች መጠን በ67 በመቶ ጨምሯል ብሏል።

ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ እስካሁን ድረስ የዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ በሩሲያ ላይ ማዕቀብ አልጣለችም። ሩሲያ 'ልዩ ወታደራዊ ኦፕሬሽን' የምትለውን ወረራንም አላወገዘችም።

ማዕቀብ ላልተጣለባቸው ሩሲያዊወያንም ቪዛ እየሰጠች ነው።

የሞስኮ ወረራን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ወራት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሩሲያውያን አገራቸውን ጥለው ሳይወጡ አይቀርብም ይባላል።

አንድ የሩሲያ ዜግነት ያለው የምጣሄ ሀብት ባለሙያ ጦርነቱ በተጀመረ በመጀመርያዎቹ 10 ቀናት ከ200ሺህ ያላነሱ ሩሲያውያን አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል ብሎ ነበር።

አዳዲስ ኩባንያዎች በዱባይ ሲቋቋሙ ድጋፍ የሚያደርገው ቨርቱዞን በቅርብ ወራት ገበያው እንደደራላት ይገልጻል።

"ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ከሩሲያውያን የሚቀርብልን የአግልግሎት ፍላጎት በአምስት እጥፍ ጨምሯል" ብለዋል የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ጆርጅ ሆጄኢግ።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደሚሉት ከሆነ ሩሲያውያኑ ከአገራቸው እየሸሹ ያሉት ጦርነቱን ተከትሎ በሩሲያ ሊያጋጥም የሚችለው የምጣሄ ሀብት ድቀት ስለሚያሳስባቸው ነው።

"ለአንጡራ ሀብታቸው ማረጋገጫ ስለሚፈልጉ ነው ወደዚህ የሚዘዋወሩት" ብለዋል።

የሩሲያውያን ባለሀብቶች ወደ ዱባይ መትመም በከተማዋ የቅንጡ ቪላ እና አፓርትመንት ቤቶች ፍላጎትን ጣራ አድርሶታል። የቤት አሻሻጮችም የዋጋ ጭማሪ ሪፖርት እያደረጉ ነው።

ሞደርን ሊቪንግ የተባለ ቤት አሻሻጭ ኩባንያ የሩሲያውያንን የቤት ፍላጎት ለማርካት የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪ የሽያጭ ባለሙያዎችን መቅጠሩን ለቢቢሲ ገልጿል።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቲያጎ ካለዳስ ወደ ዱባይ በአስቸኳይ መዘዋወር የሚፈልጉ ሩሲያውያን የሰልክ ጥሪ እንደሚደርሳቸው ይገልጻሉ።

"ወደዚህ የሚመጡት ሩሲያውያን ግዢ የሚፈጽሙት ለኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን ዱባይን ሁለተኛ ቤታቸው ለማድረግ ነው" ብለዋል።

ዱባይ ማሪና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በግለሰብ ደረጃ ያሉ ባለሀብቶች ብቻ አይደሉም ወደ ዱባይ እያቀኑ ያሉት፤ ኩባንያዎች ከነሠራተኞቻቸው ወደ ዱባይ እየተመሙ ነው።

ፉአድ ፋቱሌቭ ከዊዌይ ኩባንያ መሥራቾች መካከል አንዱ ነው።

ፉአድ የብሎክቼይን ኩባንያው በሩሲያ እና ዩክሬን ቅርንጫፎች እንዳሉት ይናገራል። ከጦርነቱ በኋላ ግን እርሱ እና አጋሮቹን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞቹን ወደ ዱባይ ማዘዋወራቸውን ይገልጻል።

"ጦርነቱ በሥራችን ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል።"

ፉአድ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ የጣሏቸው ማዕቀቦች ሥራቸውን ለመሥራት ስላላስቻላቸው አገር ለመቀየር መገደዳቸውን ያስረዳል።

እንደ ጄፒ ሞርጋን እና ጉግል ያሉ ዓለም አቀፍ ስም ያላቸው ኩባንያዎችም በሩሲያ ያላቸውን ቢሮ በመዝጋት ሠራተኞቻቸውን ወደ ዱባይ እያዘዋወሩ ነው።

የባህረ ሰላጤው አገራት ዩኤኢ እና ሳዑዲ አረቢያ፣ ምዕራባውያኑ በሩሲያ ላይ ማዕቀብ እንዲጥሉ ያቀረቡላቸውን ተደጋጋሚ ጥሪ ለመስማት ፍቃደኛ አልሆኑም።

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ከወራት በፊት የሩሲያን ወረራ ለማውገዝ ድምጽ በሰጠበት ወቅት ጉዳዩን በድምጸ ታዕቅቦ ካለፉት አገራት መካከል ዩኤኢ አንዷ ነበረች።

ከዚህ በተጨማሪም ሩሲያን ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለማገድ የወጣው ውሳኔ ላይ አቡ ዳቢ በድምጸ ታዕቅቦ አልፋለች።