ሩሲያ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው 'ልዩ ወታደራዊ ኦፕሬሽን' ነው በሚለው አቋሟ ጸናች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሩሲያ በዩክሬን እየተካሄደ ያለውን 'ጦርነት' ብዬ አልጠራም አለች።
ይህ የተባለው የሞስኮው መንግሥት በዩክሬን እየካሄደ ያለውን በይፋ 'ጦርነት' ሲል ይገልጸዋል የሚል መረጃ በስፋት ከተሰራጨ በኋላ ነው።
ሩሲያ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው 'ጦርነት' ሳይሆን 'ልዩ ወታደራዊ ኦፕሬሽን' ነው ብላ ትገልጻለች።
ምዕራባውያን የናዚ ጀርመን ሽንፈት እና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃትን በተመለከተ በሞስኮ በሚካሄድ ወታደራዊ ትዕይነት ላይ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን እየተካሄደ ያለው 'ልዩ ወታደራዊ ኦፕሬሽን' ወደ 'ጦርነት' ደረጃ ከፍ ብሏል ብለው ይናገራሉ ብለው ነበር።
ይሁን እንጂ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮ ይህ የምዕራባውያን መላ ምት ምንም ዓይነት እውነት የለበትም ብለዋል።
የሩሲያ ባለሥልጣናት በዩክሬን ላይ የፈጸሙትን ወረራ፤ የዩክሬንን 'ወታደራዊ አቅምን ለማዳከም' እና 'የናዚ ስሜትን ለማጥፋት' የሚካሄድ 'ልዩ ወታደራዊ ኦፕሬሽን' ሲሉ ይገልጹታል።
ሞስኮ የፊታችን ሰኞ ግንቦት 1/2014 ዓ.ም. በሞስኮ ብቻ ሳይሆን ከከፍተኛ ውጊያ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ በቁጥጥሯ ስር ባስገባቻቸው የዩክሬኗ ማሪዮፖል ከተማ ጭምር ነው።
የዩክሬን ባለሥልጣናት ለዚህ ሥነ ሥርዓት ሲባል የሩሲያ ወታደሮች የማሪዮፖል ዋና ጎዳናዎችን እያጸዱ ነው።
እንደ ባለሥልጣናቱ ከሆነ መሃል ከተማ ከሚገኙ ጎዳናዎች ፍርስራሾች እየጸዱ ነው። አስክኖች እና ያልፈነዱ ቦምቦች እየተነሱ ነው።
ዩክሬናዊቷ ፖለቲከኛ አልዮና ሸክሩም ሩሲያ የድል ቀኗን በምታከብርባቸው ቀናት ነገሮች የበለጠ ፈታኝ ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ለፑቲን እና መመሥረት ለሚፈልገው ግዛት ይህ ቀን ልዩ ትርጉም ይኖረዋል" ይላሉ ፖለቲከኛዋ።
ፑቲን የድል በዓሉ በሚከበርበት ቀናት በኪዬቭ፣ ኦዴሳ እና ማሪዮፖል ከተሞች እና ዙሪያ ጠንካራ ውጊያ በመክፈት አስቸጋሪ የሚባሉ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።












