በአንዴ ዘጠኝ ሆኖ በመወለድ የመጀመሪያ የሆኑት ልጆች አንደኛ ዓመታቸውን አከበሩ

በዓለም ብቸኛ የሆኑት ዘጠኝ በአንዴ የተወለዱት ልጆች

የፎቶው ባለመብት, SALOUM ARBY

የምስሉ መግለጫ, በዓለም ብቸኛ የሆኑት በአንዴ የተወለዱ ዘጠኝ ልጆች

በአንዴ በመወለድ በዓለም ብቸኛ የሆኑት ዘጠኝ ልጆች አንደኛ ዓመታቸውን እንዳከበሩና መልካም ጤና ላይ እንደሚገኙ አባታቸው ለቢቢሲ ገለጸ።

በአንድ ጊዜ የተወለዱት ዘጠኝ ልጆች መዳህ እንደጀመሩ በማሊ መከላከያ ውስጥ የሚሠራው አባታቸው አቡበከር አርቢ ተናግሯል።

ከልጆቹ መካከል አንዳንዶቹ መቀመጥ እንደጀመሩና የተወሰኑት ደግሞ በድጋፍ እንደሚራመዱም ገልጿል።

ልጆቹ በተወለዱበት የሞሮኮ ሆስፒታል ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል።

የ26 ዓመቷ እናታቸው ሐሊማ ሲሴ በጥሩ ጤንነት ላይ ናት ሲልም አባትየው ተናግሯል።

"ቀላል አይደለም። አድካሚ ቢሆንም ልጆቻችን ተደርድረው ስናይ ልፋቱን እንረሳዋለን" ብሏል አቡበከር።

ጥንዶቹ ሳዑዳ የተባለች የሦስት ዓመት ልጅ አለቻቸው።

የልጆቹን ልደት ጥቂት ሰዎች እና ነርሶች በተገኙበት እንደሚያከብሩ ገልጸዋል።

"አንደኛ ዓመት ልደት ልዩ ነው። ይህንን ጊዜ አንረሳውም" ብሏል አባትየው።

ልጆቹ በአንድ ጊዜ የተወለዱና በሕይወት የቆዩ ብዙ ሕፃናት ተብለው በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ጊነስ ተመዝግበዋል።

እናትየዋ ልጆቹን ከመውለዷ በፊት ለተሻለ ሕክምና በማሊ መንግሥት ወደ ሞሮኮ እንድትሄድ ተወስኗል።

ከአራት በላይ ልጆችን በአንዴ መውለድ ከወሊድ ጋር ለተያያዘ እክል ሊያጋልጥ ይችላል።

ጽንስ ማቋረት በሚፈቀድባቸው አንዳንድ አገራት ከአራት በላይ ልጆች ሲጸነሱ እንዲቋረጥ ይመከራል።

ቤተሰቡ በአሁኑ ወቅት ልጆቹ በተወለዱበት ሆስፒታል ውስጥ ለመኖሪያነት በተዘጋጀ አፓርትመንት ውስጥ ይኖራሉ።

ነርሶቹ ልጆቹን በመንከባከብ እናታቸውን እንደሚያግዙም ተናግረዋል።

ልጆቹ ቀንና ሌሊት ምን መመገብ እንዳለባቸው በሐኪሞች መርህ ወጥቷል።

ልጆቹ አምስት ሴቶች እና አራት ወንዶች ሲሆኑ በ30ኛ ሳምንታቸው ነው የተወለዱት።

የአይን ቦርጃ ክሊኒክ ሜዲካል ዳይሬክተር ፕ/ር ዩሱፍ አልአይ እንደተናገሩት፣ ክብደታቸውም ከ500 ግራም እስከ 1 ኪሎ ግራም ነበር።

እናትና አባት ከመጀመሪያ ልጃቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, SALOUM ARBY

የምስሉ መግለጫ, እናትና አባት ከመጀመሪያ ልጃቸው ጋር

ወንዶቹ ልጆች ሞሐመድ፣ ኦማር፣ ኤልሐጂ፣ ባሕ ይባላሉ። ሴቶቹ ደግሞ ካዲዳ፣ ፋጡማ፣ ሐዋ፣ አዳማ እና ኦሞው።

አባታቸው እንዳለው ሁሉም የተለያየ ባህሪ አላቸው።

"አንዳንዶቹ ዝምተኛ ናቸው። ሌሎቹ በጣም ያለቅሳሉ። ሁሌ መታቀፍ የሚፈልጉም አሉ።"

የማሊ መንግሥት ዘጠኙ ልጆችና እናታቸው ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ በመደገፉ አባትየው አመስግኗል።

ልጆቹ ገና ወደ አገራቸው ማሊ አልተወሰዱም። ዝናቸው ግን ናኝቷል።

"ቤተሰቦቻችን፣ ጓደኞቻችን፣ ጎረቤቶቻችን እንዲሁም መላው ማሊ ልጆቹን ለማየት ጓጉቷል" ሲል አባትየው ለቢቢሲ ገልጿል።

ልጅ ለመውለድ እየሞከሩ ላሉ ጥንዶችም መልካም ምኞቱን እንዲህ አስተላልፏል።

"ልጅ የሌላቸው ልጅ እንዲያገኙ ፈጣሪ እንዲረዳቸው እመኛለሁ። ሌሎችም ሰዎች እኛ ያለን እንዲኖራቸው እሻለሁ። ልጀች ሀብት ናቸው፣ ጸጋ ናቸው።"