ሂውማን ራይትስ ዎች የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ግፍ ፈፅመዋል አለ

የሩሲያ ወታደር

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በ2020 ምርጫ ወቅት የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ጸጥታ ሲያስከብሩ ታይተዋል

የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ሰላማዊ ሰዎች በመግደል፣ በማሰቃየትና በመደብደብ ተከሰሱ።

የዓይን ምስክሮች ለዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ሂውማን ራይትስ ዎች እንደተናገሩት ባለፈው ሐምሌ ወር ላይ በተፈጠረ አንድ ክስተት የሩሲያን ቋንቋ የሚናገሩ ተዋጊዎች ቢያንስ 12 ያልታጠቁ ወንዶችን መንገድ ላይ ተኩሰው ገድለዋል።

አብዛኞቹ ሟቾችም ከቦሳንጎዋ አቅራቢያ መንገድ ላይ ጉድጓድ ውስጥ ተጥለዋል ብለዋል የዓይን እማኞቹ።

የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ መንግሥት አማጺያንን ለመዋጋት የግል ከሆነው የሩሲያ ዋግነር ግሩፕ ወታደሮችን አልቀጠርኩም ብሏል።

ማስጠንቀቂያ- ይህ ዘገባየሚረብሽ ይዘት ይዟል

የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎችም ከዓለም ድሃ አገራት አንዷ በሆነችውና በአልማዝ ፣ በወርቅ እና በዩራኒየም በበለጸገችው ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ፣ የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች ስልታዊ የሆነና ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል ሲሉ ከሰዋል።

የሩሲያዋ ዋግነር ግሩፕ ማሊ እና ሊቢያን ጨምሮ በአፍሪካ ኃይሎቹን እንዳሰማራ በስፋት የተነገረ ሲሆን በሶሪያ እና በዩክሬን ባለው ግጭት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷልም ተብሏል።

ባለፈው ወር ሂውማን ራይትስ ዎች ባወጣው ሪፖርት በማዕከላዊ ማሊ ወደ 300 በሚጠጉ ሰዎች ግድያ ከተከሰሱት መካከል ተጠርጣሪ የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች እንደሚገኙበት ገልጿል።

ሆኖም በዚህ ሳምንት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰረጌ ላቭሮቭ፣ ዋግነር ግሩፕ ከሩሲያ መንግሥት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው የሞስኮን ባለሥልጣናት አቋም በድጋሚ አስታውቀዋል።

ሂውማን ራይትስ ዎች ባወጣው በዚህ ሪፖርቱ የሩሲያ ወታደሮች እአአ ከ2019 ጀምሮ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈፀማቸውን ማስረጃ አሰባስቤያለሁ ብሏል።

ድርጅቱ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በየካቲት 2019 እና በኅዳር 2021 መካከል ባሉት ጊዜያት አስር ተጎጂዎችን እና አስራ አምስት የዓይን እማኞችን ጨምሮ 40 ሰዎችን የሩሲያ ቋንቋ በሚናገሩ ወንዶች ስለደረሰባቸው በደል ቃለ መጠይቅ አድርጌያለሁ ብሏል።

የዓይን እማኞቹ እንደተናገሩት ግለሰቦቹ የጦር መሣሪያዎችን የያዙ ሲሆን ካኪ ልብስና ፊታቸውን የሚሸፍን ስካርፍ ለብሰዋል፤ የወታደር ጫማ እና መነጽርም አድርገዋል።

ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው መካከል አስራ ሁለቱ ሐምሌ 21፣ 2021 በአገሪቷ በስተምዕራብ በምትገኘው ቦሳንጎዋ ከተማ አቅራቢያ የተፈፀመውን ግድያ እንደተመለከቱ ድርጅቱ ገልጿል።

የተገደሉት ያልታጠቁ ወጣት ወንዶች ከቦሳንጎዋ በሞተር ሳይክል የወጡት ከቀኑ 6፡00 ሰዓት በኋላ ነበር።

ከከተማዋ በመውጣት የፍተሻ ኬላው ካለፉ በኋላ ከቦሳንጎዋ 12 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው መንገድ ላይ በሩሲያ ተዋጊዎች እንደሚጠበቁ በሚነገረው የመንገድ ባለሥልጣናት እንዲቆሙ ተደረገ።

ከሞተር ሳይክሉ እንዲወርዱ እና እጃቸውን ጭንቅላታቸው ላይ እንዲያደርጉና ስልካቸውን እንዲያስረክቡም ተነገራቸው።

ከዚያም ከአራት እስከ ስድስት የሚሆኑ የሩሲያ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች መሬት ላይ አስተኝተው እንደደበደቧቸው እና አንድ በአንድ እየተወሰዱ በተንበረከኩበት ጭንቅላታቸውን በጥይት ተመትተው መገደላቸውን ድርጅቱ በሪፖርቱ አትቷል።

ሁኔታውን ሲመለከቱ የነበሩት ጮክ ብለው መጸለይ እንደጀመሩና በጩኸቱና በግርግሩ መካከል ከተያዙት ወጣት ወንዶች መካከል ሁለቱ ማምለጥ እንደቻሉ ሪፖርቱ አክሏል።

"ጣቴቆረጡት"

ሂውማን ራይትስ ዎች እአአ በ2019 በባምባሪ የታሰሩ እና በሩሲያ ወታደሮች ስቃይ የደረሰባቸው ሰዎችን በተመለከተም መረጃ አደራጅቷል።

ከአማጺ ቡድኑ ጋር ግንኙነት አለህ በሚል ተጠርጥሮ የተያዘው ባለሱቅ በ2019 ጥር ላይ በያዘው የሩሲያ ተዋጊ ጣቱ እንደተቆረጠ ተናግሯል።

"በብረት ዘንግ እና ቢላዋ እግሬን ክፉኛ ደበደቡኝ ፣ ቁርጭምጭሚቴ ታስሮ ነበር፤ አንዱ በአስተርጓሚ አማካኝነት 'ጣቶችህን እንቆርጣለን' አለኝ" ይላል ማሃማት ኑር ማማዶ በእስር ቤት ስለደረሰበት በደል ሲናገር።

የማሃማት ኑር የተቆረጠ ጣት

የፎቶው ባለመብት, LEWIS MUDGE/HRW

የምስሉ መግለጫ, መሃማት ኑር ማማ የሩሲያ ሰዎች ጣቱን በቢላ እንደቆረጡት ለሂውማን ራይትስ ዎች ተናግሯል።

"ጮኽኩ ፣ በጣም ነበር የሚያመው። ከዚያም ገመድ አውጥተው አንገቴ ላይ ጠመጠሙት፤ ገመዱን አጠበቁት ። ከዚያ አልቻልኩም ወደቅኩ። ምላሴ ታጠፈ። አንድ ሩሲያዊ አፌ ውስጥ የጡብ ስባሪ አስገብቶ መታው። ጥርሴ ተነቀለ" ይላል ማሃማት።

ማሃማት ስለደረሰበት መከራ ለጋዜጠኞች የተናገረ ሲሆን ሂውማን ራይትስ ዎች መስከረም 2019 ላይ ግልጽ ባልሆነ መንገድ መገደሉን ገልጿል።

የሩሲያ እና የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ግንኙነት ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው እአአ በ2018 የቀድሞ የሩሲያ መኮንኖች ወታደራዊ ሥልጠና ለመስጠት ከአገሪቷ ጋር መስማማታቸውን ተከትሎ ነበር።

ሐምሌ 30፣ 2018 ላይ ሦስት የሩሲያ ጋዜጠኞች፣ ዋግነር ግሩፕ በአገሪቷ ስላለው ተሳትፎ የተመለከተ የምርመራ ዘገባ የሰሩ ጋዜጠኞች በጥይት ተመትተው ተገደሉ። እስካሁን ከግድያው ጀርባ ያለው አካል አልተገኘም።

ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እአአ በ1960 ነጻነቷን ካወጀች በኋላ በግጭቶች ስትታመስ ቆይታለች።

በ2013 በዋናነት ሙስሊም አማጺያን አብላጫውን የክርስትና እምነት ተከታዮች ያሉበትን አገር መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ራሳቸውን ለመከላከል ሚሊሻዎች መቋቋማቸው ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ ሰፊ እልቂትን አስከትሏል።

የአገሪቱ ፕሬዚደንት ፋውስቲን አርቸንጂ ቱዋዴራ በ2016 ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላም አገሪቱ ስልታዊ አጋርነቷን ከቀድሞ ቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ ወደ ሩሲያ አዙራለች።

ሂውማን ራይትስ ዎች በአገሪቷ ተጠያቂነት አለመኖሩ አብዛኛውን ግጭት አንዲባባስ አድርጎታል ብሏል።

በመሆኑም መንግሥት የውጭ ኃይሎችን ጨምሮ ግድያ፣ ሕገ ወጥ እስር እና ማሰቃየት የፈፀሙትን ሁሉ አጣርቶ ለሕግ እንዲያቀርብ ድርጅቱ ጠይቋል።