የጦር ወንጀል ምንድን ነው? ከሳሽና ለፍርድ አቅራቢስ ማነው?

'ፑቲን በጦር ወንጀል ይፈለጋሉ' የሚል መፈክር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ምዕራባውያን ፑቲን በጦር ወንጀል መጠየቅ አለባቸው ይላሉ።

የቦስኒያ ሰርብ ጦር መሪ ራትኮ ማልዲች በጦር ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር ውሎ ዘ ሄግ ወደተሰኘው የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት ሲሄድ ብዙዎች አንድ ጥያቄ ጠይቀው ነበር።

የጦር ወንጀል ማለት ምን ማለት ነው? የሚል።

ለመሆኑ የጦር ወንጀል ከሌላው በምን ይለያል? ከሳሽስ ማነው?

"አዎ፤ ጦርነትም ቢሆን ሕግ አለው" ይላል ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማሕበር።

ሰላማዊ ዜጎችን የጦርነት ሰለባ ማድረግ አንዱ የጦር ወንጀል መገለጫ ነው።

የጦር ወንጀል የቅርብ ጊዜ ፅንሰ ሐሳብ ነው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት በጦርነት ወቅት የሚፈጸሙ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የግጭት አካል ናቸው ተብሎ ነበር የሚታሰብ።

ነገር ግን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሁኔታዎችን ቀየረ።

በዚህ አስከፊ ጦርነት በርካታ ሰዎች በተለይ ደግሞ አይሁዳዊያን በናዚ ጀርመን ሲገደሉ፤ ጃፓኖች ምርኮኞችንና ንጹሐንን ሳይለዩ ሲያጠፉ ምዕራባዊያን መሰል ወንጀል የሚፈፅሙ ይቀጣሉ ሲሉ ወሰኑ።

በ1945 ይህን ሕግ ጥሰዋል የተባሉ 12 የናዚ መሪዎች በሞት ወንጀል ተቀጥተዋል።

ቶኪዮም ይህን ሕግ በ1948 መተግበር ጀመረች። ሰባት ጃፓናዊያን የጦር መሪዎች የጦር ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው በስቅላት ተቀጥተዋል።

በአሁኑ ዘመን መሰል ጉዳዮችን የሚመለከተው በኔዘርላንድስ ዘ ሄግ ከተማ ያለው ችሎት ነው።

ነገር ግን የጦር ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች ቅጣታቸውን አላገኙም ያሉ መንግሥታት የራሳቸውን እርምጃም ሲወስዱ ይስተዋላል።

አንድ ታዋቂ ምሳሌ እናንሳ።

ጊዜው በፈረንጆቹ 1960። አዶልፍ ኢኽማን የተሰኘው ነባር የናዚ ጀመርን አባል በሆሎካስ ዘመን ወንጀል ፈፅሟል ተብሎ በእስራኤል መንግሥት ይከሰሳል።

ነገር ግን ሰውዬው ከነቤተሰቡ አርጀንቲና ከትሞ ነበር።

ሰውዬው ወንጀል ፈፅሞ በሰላም መኖሩ ያልተዋጠላቸው እስራኤላዊያን ሰላዮች ለልዩ ተልዕኮ ወደ ቦነስ አየረስ ያቀናሉ።

ጉድ ይመጣብኛል ብሎ ያላሰበውን ኢኽማን አንከብክበው ፊቱን በጨርቅ አፍነው ይሰወራሉ።

ኢኽማን እስራኤል ከተወሰደ በኋላ የጦር ወንጀል ፈፅመሃል ተብሎ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በስቅላት ተቀጥቷል።

የጦር ወንጀል ማዕከል ፅንሰ ሃሳብ፣ አንድ ሃገር ለፈፀመችው አሊያም የጦር ሠራዊት ለፈፀመው ወንጀል አንድ ግለሰብ ተጠያቂ ሊሆን ይችላል የሚለው ነው።

የዘር ማጥፋት፤ ሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀል፤ በጦርነት ወቅት ሰላማዊ ዜጎች ላይ አሊያም ተዋጊዎች ላይ የሚፈፀም ወንጀል በጦር ወንጀል ውስጥ የሚከታቱ ናቸው።

የዘር ማጥፋት ትልቁ የጦር ወንጀል ተደርጎ ይወሰዳል።

ሕገ-ወጥ ግድያ

ይህ ሕግ ሕጋዊ ግድያ አለ ወይ የሚል ጥያቄ ሊያጭር ይችላል።

'ዊልፉል ኪሊንግ' አሊያም በግርድፍ ትርጉሙ ሕገ-ወጥ ግድያ ወይንም ሆነ ብሎ መግደል የሚለው ሐሳብ ከጄኔቫ ስምምነት ጋር ቁርኝነት ያለው ነው።

የአራተኛው ጄኔቫ ስምምነት አንቀፅ 147 የጦር ወንጀልን እንዲህ ሲል ይፈታዋል።

"ሕገ-ወጥ ግድያ፣ ማሰቃየት አሊያም ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ ይህም ማለት አካል ላይ አሊያም ጤና ላይ ጉዳት ማድረስ፤ ጥበቃ ያላቸውን ሰዎች ያለፍላጎታቸው ይዞ ከድንበር ድንበር ማሻገር፤ ምርኮኞች እንዲዋጉ ማድረግ፤ መብታቸውን መንፈግ አሊያም ፍትህ መንፈግ፤ ሰዎችን ማገት፤ ንብረት ማውደምና መውረስ. . ."

ዓለም አቀፍ ጠበቃዎች እንደሚሉት ይህ የጦር ወንጀል ትንታኔ ነው።

የዘር ማጥፋት ወንጀልስ ምንድነው?

ዘ ሄግ ያለው ፍርድ ቤት የዘር ማጥፋትን "ሆነ ተብሎ በጠቅላላው አሊያም የተወሰነ፤ ሃገራዊ፤ ብሔረሰባዊ፤ ዘር ወይንም ኃይማኖትን ለማጥፋት የሚፈፀም ወንጀል" ይለዋል።

የዘር ማጥፋት ወንጀልን የሚመለከተው ሕግ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለዋወጠና እያደገ መጥቷል።

በፈረንጆቹ የካቲት 2001 ዘ ሄግ ያለው ፍርድ ቤት በጦርነት ጊዜ የተፈፀመ የተቀናጀ መድፈርና ወሲባዊ ባርነትን ሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀል ነው ሲል በይኖ ነበር።

ከዚህ ብይን በኋላ በጅምላ መድፈር አሊያም መድፈር እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀም ከዘር ማጥፋት ቀጥሎ ከፍተኛ የጦር ወንጀል መሆናቸው ታወጀ።

የጦር ወንጀልን እንዴት መለየት ይቻላል?

የጦር ወንጀልን መለየት ቀላል የሚባል ሂደት አይደለም።

ሰላማዊ ነዋሪዎች በጠላት ጦር ከቤት ንብረታቸው ቢፈናቀሉ የጦር ወንጀል ተፈፅሟል ማለት ከባድ ነው።

ይህ ድርጊት የጦር ወንጀል የሚሆነው ሰላማዊ ነዋሪዎቹ ሆነ ተብሎ እንደ ዘር ማፅዳት ዘመቻ እንዲፈናቀሉ ከተደረገ ነው።

ለምሳሌ አንድ አየር ኃይል ሌላኛው ወገን ለፕሮፖጋንዳ ይጠቀምበታል ብሎ ያሰበውን የቴሌቪዥን ጣቢያ ቢያጋይ እንደ ጦር ወንጀል አይቆጠርም።

መንገድ ማውደም፣ ድልድይ ማፍረስ፣ የኃይል አቅርቦት፤ ፋብሪካ ሌሎችም መሠረት ልማቶች ቢወድሙ እንደ ጦር ወንጀል ላይቆጠር ይችላል።

ነገር ግን ይህ ውድመት ከጦርነት ስልት ጥቅሙ በላይ ሰላማዊ ዜጎችን አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ የጦር ወንጀል ሊሆን ይችላል።

ዓለም አቀፍ ችሎት

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የጦር ወንጀልና ሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀል ወጥ የሆነ አተገባበር ይኑራቸው ብለው መጠየቅ ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

በፈረንጆቹ 1993 የቀድሞዋ ሶቪዬት ሕብረትን በተመለከተ የሚመጡ ጉዳዮችን ለማየት ዓለም አቀፍ ችሎት ተቋቁሟል።

አልፎም በ1994 በሩዋንዳ የተፈፀሙ ጥሰቶችን ለማየት በታንዛኒያዋ አሩሻ ችሎት ተቋቁሟል።

ሌላኛው የጦር ወንጀልን የተመለከተው ችሎት የቀድሞው የላይቤሪ ፕሬዝደንት ቻርልስ ቴይለርን ለመዳኘት የተቋቋመው ነው።

ሐምሌ 2008 ሱሪናም ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤትን [አይሲሲ] የተቀላቀለች 107ኛው ሃገር ሆናለች።

ዩናይትድ ስቴትስ ግን ይህ ዓለም አቀፍ ስምምነት አልፈርምም ስትል እምቢኝ ብላለች። ምክንያቷ ደግሞ ፍርድ ቤቱ የፖለቲካ መጠቀሚያ ሊሆን ይችላል ነው።

እንደ ሩሲያና ቻይና ያሉ ኃያላን ሃገራትም አንቀላቀልም ብለዋል።

ይህ ፍርድ ቤት ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ነው የሚለውን ጥያቄ ብዙዎች ያነሳሉ።

ይህ ፍርድ ቤት ገለልተኛ የሚሆነው ሁሉም ሃገራት ለፈፀሙት ጥሰት እኩል ተጠያቂ ሲሆኑ ብቻ ነው ይላሉ።