ሂዩማን ራይትስ ዋች በትግራይ የተፈጸመው የአየር ጥቃት የጦር ወንጀል ሊሆን ይችላል አለ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS/STRINGER
ሂዩማን ራይትስ ዋች ከወራት በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ተፈናቃዮች ተጠልለውበት በነበረ ትምህርት ቤት ላይ የተፈጸመው የአየር ጥቃት የጦር ወንጀል ሊሆን ይችላል አለ።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ታኅሣሥ 29/2014 ዓ.ም. ተፈናቃዮች ተጠልለው የነበሩበት ትምህርት ቤት ላይ የአየር ጥቃት ከተሰነዘረበት በኋላ ቢያንስ 57 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን እና 42 ሰዎች መቆሰላቸውን አስታውቋል።
በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ደደቢት ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ሰው አልባ አውሮፕላን ተፈናቃዮች ተጠልለው በነበሩትበት ትምህርት ቤት ላይ ሦስት ቦምቦችን ጥለዋል ብሏል ሂዩም ራይትስ ዋች።
የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ጥቃት ዙሪያ ጥልቅ እና ገለልተኛ ምርመራ አድርጎ ተጠያቂዎችን ለፍርድ ማቅረብ አለበት ሲልም የሰብአዊ መብት ድርጅቱ ጠይቋል።
የድርጅቱ የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር የሆኑት ላቲሻ ባደር፤ በደደቢት ትምህር ቤት ላይ በተሰነዘረው የድሮን ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው አዛውንቶች፣ ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸውን ገልጸው፤ "ወታደራዊ ዒላማ መኖሩ ሳይረጋገጥ ስልታዊ ቦምቦችን መጠቀም ገልጽ የጦር ወንጀል ነው" ብለዋል።
ዳይሬክተሯ የትግራይ ኃይሎች ተቆጣጥረዋቸው ከነበሩት የአማራ እና የአፋር ቦታዎች ለቀው ከወጡ በኋላ በኢትዮጵያ አየር ኃይል የሚፈጸሙ የአየር ጥቃቶች ተበርካተው ነበር ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ከኅዳር 13/2013 እስከ የካቲት 21/2014 በተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች 304 ሰዎች መገደላቸውን እና 373 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን መግለጹ ይታወሳል።
ከ15 ወራት በፊት በትግራይ የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተሸጋግሮ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ቀውስን አስከትሏል።
በዚህ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑት የፌደራሉ መንግሥት ጦር፣ የአማራ ክልል ኃይሎች፣ የኤርትራ ሠራዊት እና የህወሓት ኃይሎች በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ ስለመሆናቸው በተለያዩ ወገኖች በተደጋጋሚ ሲከሰሱ ቆይተዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የትግራይ ኃይሎች ወደ አማራ ክልል ገብተው በቆዩባቸው ጊዜያት ከጦር ወንጀል ጋር የሚስተካከሉ በሲቪሎች ላይ ግድያ እና የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶችን መፈጸማቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ሂዩማን ራይትስ ዋች በደደቢት ትምህር ቤት ላይ በተፈጸመው የአየር ጥቃት የደረሰውን የጉዳት መጠን ዝርዝር ለማወቅ ከጉዳቱ የተረፉ፣ በጥቃቱ ሕይወታቸውን ያጡ ቤተሰብ አባላት፣ የሰብዓዊ እርዳታ ተቋማት ሠራተኞችን እና ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ያከሙ የጤና ባለሙያዎችን አነጋግሪያለሁ ብሏል።
በጥቃቱ ማግስት ትምህርት ቤቱን የጎበኙ አንድ የጤና ባለሙያ ድግሞ፤ ሰዎች ክፉኛ ስለተቃጠሉ ምን ያክል ሰዎች እንደሞቱ ማወቅ ከባድ ነበር ሲሉ ተናግረዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ በጥቃቱ የሞቱ ሰዎች ዝርዝር ከተፈናቃዮቹ ማግኘቱን በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል። በጥቃቱ ከተገደሉት 53 ሰዎች መካከል 32 ሴቶች ሲሆኑ 21 ደግሞ ወንዶች ናቸው ብሏል።
ከተፈናቃዮች አገኘሁት ባለው መረጃ መሠረት በጥቃቱ የተገደሉት ሁሉም ሰዎች ከሁመራ ከተማ የተፈናቀሉ ሰዎች ናቸው ይላል።
በሺር ከተማ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ደግሞ በደረሰው የአየር ጥቃት ቢያንስ 46 ሰዎች የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት እንደደረሰባቸው ነግረውኛብ ብሏል ሂዩማን ራይትስ ዋች።
የሰብዓዊ መብት ቡድኑ ጨምሮም ይህ ጥቃት የተፈጸመው በቱርክ ሠራሹ ባይራክታረ ቲቢ-2 ሰው አልባ አውሮፕላን መሆኑን ከስፍራው ከተገኙ መረጃዎች አረጋግጫለሁ ብሏል።
ሂዩማን ራይትስ ዋች ሰዎች ተጠልለው በሚገኙበት ደደቢት ትምህር ቤት ወታደራዊ ዒላማ ስለመኖሩ ምንም አይነት ማስረጃ እንዳላገኘ አመልክቷል።
ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል እተካሄደ ያለው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋብ ያለ ቢመስልም የአፋር እና የአማራ ክልሎች ከትግራይ ጋር በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ውጥረት እና አልፎ አልፎም ግጭቶች እንዳሉ ሲዘገብ ቆይቷል።












