ፑቲን ምዕራባውያን ዩክሬንን ማስታጠቅ እንዲያቆሙ ለማክሮን ነገሩ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ምዕራባውያኑ ዩክሬንን ማስታጠቅ እንዲያቆም ለፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ነገሩ።
ፑቲን ምዕራባውያን ዩክሬንን ማስታጠቅ አቁመው በምትኩ በፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ላይ ጫና ቢያሳድሩ ጦርነቱን ማቆም ይቻላል ሲሉ ለማክሮን ተናግረዋል።
ፑቲን ይህን ያሉትን ከወር በኋላ ከፕሬዝደንት ማክሮን ጋር በስልክ በተገናኙበት ወቅት ነው።
ማክሮን በበኩላቸው ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ እና ሩሲያም ወረራውን እንድትገታ ጠይቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ካስተናገዱት የዩክሬን ከተሞች መካከል አንዷ በመሆነችው ማሪዮፖል የሚገኙ ንጹሃሃን ዜጎች እንዲወጡ ማክሮን ጠይቀዋል።
ምዕራባውያን ከኃያሉ የሩሲያ ጦር ጋር እየተፋለመች ላለችው ዩክሬን ከፍተኛ መጠን ያለው ወታደራዊ ድጋፎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ለዩክሬን ከፍተኛ ድጋፍ ካደረጉ አገራት መካከል አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግድም ይጠቀሳሉ።
ዩኬ ትናንት 300 ሚሊዮን ፓውንድ ግምት ያላቸው ወታደራዊ የራዳር ሥርዓቶች እና አቅጣጫ ጠቋሚ ሥርዓቶችን የሚያፍኑ መሣሪያዎችን ጨምሮ ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብታችለ።
በዚህ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎች እና ሲቪሎች የሞቱ ሲሆን ጦርነቱን ተከትሎ ከ5.5 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናውያን ቀያቸውን ጥለው ወደ ጎረቤት አገራት ተሰደዋል።
ሁለቱ መሪዎች በነበራቸው የስልክ ንግግር ወቅት ቭላድሚር ፑቲን አስተዳደራቸው ከዩክሬን ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን አመላክተዋል።
የፈረንሳይ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ላይ የዩክሬንን ሉዓላዊነት ያከበረ ድርድር እንዲካሄድ ማክሮን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ለፑቲን ተናግረዋል ብሏል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ያሸነፉት ማክሮን፤ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ከፑቲን ጋር በርካታ ጊዜ ተገናኝተው ተነጋግረዋል።












