በአሜሪካ ተያይዘው የጠፉት እስረኛና የማረሚያ ቤት ፖሊስ 'ልዩ ግንኙነት' ነበራቸው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, LAUDERDALE COUNTY SHERIFF'S OFFICE
በአሜሪካ አላባማ ግዛት ያመለጠው እስረኛ እና እንዲያመልጥ ረድተዋለች ተብላ የተጠረጠረችው የማረሚያ ቤት ፖሊስ "ልዩ ግንኙነት" እንደነበራቸው መርማሪዎች ተናገሩ።
ከአላባማ ሸሪፍ ቢሮ የወጣው መግለጫ እንዳለው እስረኛውና ፖሊሷ ልዩ ግንኙነት እንደነበራቸው ከጠፋውና በግድያ ወንጀል ከሚጠረጠረው እስረኛ ኬሲ ዋይት ጋር አብረው የታሰሩ እስረኞች አረጋግጠዋል።
ፖሊስ እስካሁን በእስረኛውና በፖሊሷ መካከል አለ የተባለው 'ልዩ' ግንኙነት የፍቅር መሆን አለመሆኑን አልገለጸም።
ፖሊስ የ38 ዓመቱን ኬሲ ዋይትንና የ56 ዓመቷን የማረሚያ ቤት ፖሊስ እያደነ ነው።
ግለሰቦቹ ተያይዘው የጠፉት የማረሚያ ቤት ፖሊሷ 'በሀሰት' እስረኛውን ወደ አዕምሮ ጤና ግምገማ እየወሰድኩ ነው ካለች በኋላ ነበር።
ግለሰቦቹ የጠፉበት አርብ ዕለት ለፖሊሷ የመጨረሻ የሥራ ቀኗ ነበር።
ቪክ በቅርቡ ቤቷን የሸጠች ሲሆን አብዛኛውን ጊዜዋን በባህር ዳርቻዎች እየተዝናናች ለማሳለፍ ማቀዷን ለባልደረቦቿ ተናግራ ነበር።
ቪክ እስረኛውን ኬሲ ዋይትን የእስር ቤቱን ደንብ በመጣስ ብቻዋን በማጀብ እንዲያመልጥ እንደረዳችው ፖሊስ ያምናል።
ፖሊስ ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ "መርማሪዎች በሳምንቱ መጨረሻ በፖሊስ አባሏ እና በታራሚው ኬሲ መካከል ልዩ ግንኙነት እንዳለ ከሌሎች ታራሚዎች መረጃ አግኝተዋል" ብሏል።
ግንኙነታቸውም በገለልተኛ ምንጮች እና መንገዶች በተደረገ ምርመራ ተረጋግጧል ብሏል መግለጫው።
ማክሰኞ ዕለት የአሜሪካ ማርሻል አገልግሎት ፖሊሷ እና እስረኛው ለመጨረሻ ጊዜ አርብ ዕለት የአላባማ ታርጋ ቁጥር ያለው ፎርድ መኪና እያሽከረከሩ መታየታቸውን ገልጿል።
እስረኛ ኬሲ ዋይት "የታጠቀ እና እጅግ አደገኛ" ተብሎ ሊወሰድ እንደሚገባም ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ሰኞ ዕለት ሸሪፍ ሲንግልተን ኬሲ ዋይትን "እጅግ አደገኛ" ሲል የገለጸው ሲሆን የሕግ አስከባሪ አካላት ለእስረኛው ምንም ዓይነት እድል እንዳይሰጡ አሳስቧል።
"እስረኛው ምንም የሚያጣው ነገር የለም፤ ምንም ሊያደርግ ይችላል" ሲልም አክሏል።
ከእስረኛው ጋር አብራ የጠፋችው ቪክ ጥሬ ገንዘብ እየተጠቀመች እንደሆነ እንደሚታሰብ እና ስልኳንም እንዳጠፋች ገልጿል።
አቃቤ ሕግ ክሪስ ኮኖሊ "ቪክ በሕይወቴ የማምናት ሰው ነበረች፤ ጠንካራ ሠራተኛም ጭምር። ለዚያም ነው ሁኔታው ያስደነገጠን" ብለዋል።
ሼሪፍ ሲንግልተን እንዳሉት የእስር ቤቱ ተቆጣጣሪ ፖሊሷ ቪክ፣ በሥራ ክፍሏ ለ25 ዓመታት አገልግላለች።
የእርምት ረዳት ዳሬክተርም ስትሆን እስረኞችን ወደ ፍርድ ቤት ማመላለስ ከኃላፊነቶቿ መካከል አንዱ ነበር።
የ38 ዓመቱ ጎልማሳ እስረኛው ኬሲ እአአ በ2020 የ58 ዓመቷ ኮኒ ሪጂዌይን በስለት በመግደል በሁለት ከባድ የግድያ ወንጀሎች እንደተከሰሰ የአሜሪካ ማርሻል አገልግሎት ገልጿል።
ግለሰቡ ግድያውን መፈፀሙን አምኖ የነበረ ሲሆን በኋላ ግን በአዕምሮ ጤና ምክንያት ጥፋተኛ አይደለሁም ሲል ተከራክሮ በሎዴርዴል ካውንቲ እስር ቤት ውስጥ የፍርድ ሒደቱን እየተጠባበቀ ሳለ ነው የጠፋው።
የአሜሪካ የፌደራል ሕግ አስከባሪ ኤጀንሲ በበኩሉ ግለሰቡ እአአ በ2015 ማጭበርበርን እና የተሽከርካሪ ስርቆት ጨምሮ በተከታታይ የወንጀል ድርጊቶች በቀረበበት ክስ በእስር ላይ እንደነበር አስታውቋል።
ከዚህ ቀደም በኬሲ የመግደል ሙከራ የተደረገባት አንዲት ሴት ኬሲ ከእስር ቤት ማምለጡን ስታውቅ "ተጨንቄያለሁ" ብላለች።
ስሟ ያልተጠቀሰው ይህች ሴት እርሷ እና ቤተሰቧ ኬሲ ይከታተለናል በሚል መደበቃቸውን ተናግራለች።












