በኢትዮጵያ የጠፋ መድኃኒት የሚያፈላልገው መተግበሪያ

"ጤናዎ" የሞባይል መተግበሪያ

የፎቶው ባለመብት, Tenawo

ቤዛዊት በዕድሜ የገፉ እናቷ የደም መርጋት በሽታ ያሰቃያቸዋል፡፡ በጤና እንዲቆዩ ሪቫሮክሳባን የሚባል መድኃኒት ሳያቋርጡ መውሰድ ነበረባቸው፡፡

ይህ መድኃኒት እየተገባደደ ሲመጣ ቤዛዊት እንደተለመደው ለመግዛት ወጣች፡፡ ወትሮ በቀላሉ ታገኘው የነበረው ሪቫሮክሳባን ከየት ይምጣ፡፡

ዮሐንስ-አራት መንታ-ሰባራ ባቡር አካባቢ ይገኛል አሏት፡፡ አልሆነም፡፡ ቀይ መስቀል ሞክሪ ተባለች፡፡ አልሆነም፡፡

ከነማ ተሰለፈች፡፡ አልሆነም፡፡ ወጣች ወረደች፡፡ ጠዋት ወጥታ፣ ማታ ገባች፡፡ አልሆነም፡፡

የመድኃኒት ደላሎችን ሳይቀር ተማጸነች፡፡ ከየትም ሊገኝ አልቻለም፡፡ መድኃኒቱ ግን የት ገባ?

ምንም አማራጭ አልነበራት፤ አውስትራሊያ የሚገኝ የሩቅ ዘመድ ማስቸገር የግድ ሆነ፡፡

ለካንስ መድኃኒት ከውጭም ቢሆን ለማስገባት ቀላል አልነበረም፡፡

ዲኤችኤል፣ ፌዴክስ እና ሌሎች የጥቅል ዕቃ ተላላኪ ኩባንያዎች፣ በነርሱ በኩል መድኃኒት ለማስላክ ከመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ደብዳቤ ይፈልጋሉ፡፡ ሌላ መከራ፡፡ ሌላ ስቃይ፡፡

ቀን እየገፋ ሲመጣ ቤዛዊት ተጨነቀች፡፡ ምክንያቱም መድኃኒቱ ከተገባደደ እናቷ ችግር ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ መፍጠን አለባት፡፡

በመጨረሻ በሰው በሰው፣ ከብዙ የስልክ ልውውጦች በኋላ፣ ከብዙ ተማጽኖ በኋላ፣ ከኬንያ ወደ ኢትዮጵያ እየበረረች በነበረች አንዲት በጎ ፈቃደኛ በኩል መድኃኒቱ ደረሰላት፡፡ የእናቷን ሕይወትም ታደገች፡፡

ይህ የመድኃኒት ፍለጋ እሽክርክሪት የቤዛዊት ብቻ አይደለም፡፡ በርካቶች በየቀኑ ይኖሩታል፡፡

የሚሰወሩት መድኃኒቶች

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከውጭ ምንዛሬ መመናመን ጋር ተያይዞ መድኃኒቶች ድንገት ይሰውሩ ይዘዋል፡፡

መንግሥት ለምግብና መድኃኒት የውጭ ምንዛሬን አይሰስትም፡፡ ኾኖም ግን ይህ መድኃኒቶች እንደልብ እንዲገኙ አላስቻለም፡፡

ደላሎች ደብቀው አስወድደው ይሸጧቸዋል ይባላል፡፡

የጨነቀው ቤተሰብ የትኛውንም ዋጋ ከፍሎ እንደሚገዛቸው ያውቃሉ፡፡ በሰው ችግር ያተርፋሉ፡፡

አሁን አሁን የጠፉ መድኃኒቶች ብቻ አይደሉም፣ የሚገኙትም የት እንደሚገኙ ማወቅ ጊዜና ጉልበትን ይጠይቃል፡፡

በአዲስ አበባ ሺህ ፋርማሲዎች አሉ፡፡ የሚፈልጉት መድኃኒት ወይ ቦሌ ወይም ጉለሌ አንድ ፋርማሲ መደርደሪያ ላይ ቁጭ ብሎ ሊሆን ይችላል፡፡

ነገር ግን ሁሉን ፋርማሲ አዳርሶ ይሆናል እንዴ?

በዚህ ሕዝብ ጤፍ በሆነበት ከተማ ከጦር ኃይሎች-ሲኤምሲ፣ ከቦሌ-ሸጎሌ ለመድረስ ግማሽ ቀን አይበቃም፡፡

ይህን ችግር መነሻ አድርጎ ታዲያ አንድ የጤና ድርጅት መፍትሄ ፍለጋ ተነሳ፡፡

መድኃኒቶችን የሚያፈላልግ ድረ ገጽ ፀነሰ፡፡ ድረ ገጹ የስልክ መተግበሪያን ወለደ፡፡ የስልክ መተግበሪያው የጥሪ ማዕከልን ፈጠረ፡፡

ለምን ሁሉንም መድኃኒቶች ወደ አንድ ቋት አስገብተን የሕዝብን እንግልት አንታደግም ያለው ይህ ድርጅት ማን ነው?

ከግራ ወደ ቀኝ፣ ከመሥራቾቹ መካከል ዋና ሥራ አስኪያጁ ዶ/ር ሲሳይ አበበ፣ የምጣኔ ሀብትና የጤና ፍትሕ ባለሙያ መሠረት ኃይለኢየሱስ እና ክሊኒካል ፋርማሲስት ዶ/ር ኢስሃቅ መሐመድ አደም

የፎቶው ባለመብት, Tenawo

የምስሉ መግለጫ, ከግራ ወደ ቀኝ፣ ከመሥራቾቹ መካከል ዋና ሥራ አስኪያጁ ዶ/ር ሲሳይ አበበ፣ የምጣኔ ሀብትና የጤና ፍትሕ ባለሞያ መሠረት ኃይለኢየሱስ እና ክሊኒካል ፋርማሲስት ዶ/ር ኢስሃቅ መሐመድ አደም

የመድኃኒት ዝርዝሮችን በስልክ

‹‹ጤናዎ›› የሞባይል መተግበሪያ የጤና ጥበቃ ከፍተኛ ተጠሪ በተገኙበት በሸራተን አዲስ የተመረቀው ከወራት በፊት ነበር፡፡

ኬ.ኤም.ኤስ ሄልዝ ትሬዲንግ ይባላል ድርጅቱ፡፡ ባለአክሲዮኖቹ በኢትዮጵያ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝና አሜሪካ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮያዊያን ናቸው፡፡

ገሚሶቹ የድርጅቱ መሥራቾች ታዲያ አገር ቤት በዚሁ የጤና ዘርፍ የተሠማሩ ባለሙያዎች መሆናቸው ለዚህ ትርምስምሱ ለወጣ የጤና ሥርዓት መፍትሄ እንዲሹ ሳይገፋፋቸው አልቀረም፡፡

ይህም ካለፉበትና በየቀኑ ከሚያስተውሉት ችግር ተነስተው ለማኅበረሰብ መፍትሄ ለመስጠት አግዟቸዋል፡፡

የዚህ ሐሳብ አፍላቂና የድርጅቱ መሥራች ዶ/ር ሲሳይ አበበ፣ በሠሩባቸው ሐኪም ቤቶች ሁሉ በተደጋጋሚ አንድ ነገር አስተዋሉ፡፡

‹‹ታማሚዎች ተመልሰው መጥተው ያዘዝኩላቸውን መድኃኒት ማግኘት እንዳልቻሉ ይነግሩኝ ነበር›› ይላሉ፡፡

ይህ ሁኔታ መደጋገሙ ታዲያ ዶ/ር ሲሳይ የመተግበሪያውን ሐሳብ እንዲያብሰለስሉ ምክንያት ሆናቸው፡፡

ለመሆኑ የጤናዎ መተግበሪያ ተግባር ምንድነው?

በአጭሩ ለማስቀመጥ ደንበኛው የሚፈልገው መድኃኒት የት እንዳለ ይጠቁመዋል፡፡

ይህን የሚያደርገው በስልክ መተግበሪያ በመጠቀም ነው፡፡

መተግበሪያው አሠራሩ ከነ ኡበር፣ ራይድ ወዘተ የታክሲ ማሰሻ መተግበሪያዎች ጋር ተመሳሳይ ይመስላል፡፡

መጀመርያ ለደንበኛው፣ ካለበት በ500 ሜትር ራዲየስ ያሉ መድኃኒት ቤቶችን ያሳየዋል፡፡

ወይም ደግሞ መድኃኒት ፈላጊዋ ካለችበት ሆና በከተማው ያሉ መድኃኒት ቤቶቹን እያማረጠች በመተግበሪያው በምናብ ፋርማሲዎች ውስጥ ትዘልቃለች፡፡

የመድኃኒት ዝርዝራቸውን መመልከት ትችላለች፡፡ የምትፈልገው መድኃኒት መኖሩን ስታረጋግጥ ደግሞ ዋጋቸውን ማመሳከር ይቻላታል፡፡

ይህ ነው ‹‹የጤናዎ የስልክ መተግበሪያ›› ተግባር፡፡

ይህ መተግበሪያ በከፊል ሥራ ጀምሯል፡፡ የመረጃ ቋቱን ብዛትና ጥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ ነው፡፡

‹‹የተገልጋዩን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ ከብክነት መታደግ ነው ቀዳሚው ፍላጎታችን›› ይላሉ ዶ/ር ሲሳይ አበበ፡፡

ዶ/ር ሲሳይ የኬ.ኤም.ሲ ሄልዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡

ጤናዎ መተግበሪያ ታዲያ በስልክ ብቻ የሚገኝ አገልግሎት አይደለም፡፡

ዘመናዊ ስልክ ላልታደሉና ከቴክኖሎጂ ላልተዋወቁ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሌላ አማራጭ አለው፡፡

24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥ 9456 የጥሪ ማዕከል፡፡

ሐኪምና ታካሚን ማገናኘት

የጤናዎ መተግበሪያ ዋናው ተግባሩ የትኞቹ መድኃኒቶች በየትኛው ፋርማሲ ውስጥ ይገኛሉ የሚለውን መጠቆም ይሁን እንጂ ሌሎች ተጓዳኝ አገልግሎቶችም አሉት፡፡

ለምሳሌ በግል ጤና ጣቢያ ለመታከም የሚፈልግ ተገልጋይ የት ሆስፒታል ማን የሚባል ስፔሻሊስት መቼ እንደሚገኝ ማወቅ ቢፈልግ ይህን መረጃ ከዚሁ ማግኘት ይችላል፡፡

በዚህ መተግበሪያ ውስጥ 80 የሚሆኑ ሐኪሞች፣ በተለያየ ስፔሻላይዜሽን ያሉ፣ ማንነታቸውና የሥራ ልምዳቸው ተካቷል፡፡ በቀጣይ ዓመታትም በርካታ ሐኪሞች የዚሁ መተግበሪያ አባል ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ይህ ማለት አንድ ታካሚ ሐኪሙን ከተገቢ ምክር ጋር የመምረጥ፣ ካለበት ሆኖ ቀጠሮ የማስያዝ ዕድልን ይሰጠዋል፡፡

ዶ/ር ሲሳይ እንደሚሉት በአሁኑ ጊዜ ድርጅታቸው በየትኛውም የግል ሆስፒታል የታካሚና የሐኪም ቀጠሮን የማስያዝ ተጨማሪ ሥራን ይሠራል፡፡

‹‹ታካሚዎች የትኛውን ሐኪም፣ መቼ፣ የት ክሊኒክ ማግኘት እንደሚችሉ ማማከር ብቻ ሳይሆን ቀጠሮም እንይዝላቸዋለን፡፡ በሆስፒታል እየሄዱ ወረፋ መያዝ፣ መንገላታትን ለማስቀረት ነው እየሞከርን ያለነው›› ይላሉ፡፡

"ጤናዎ" የሞባይል መተግበሪያ

የፎቶው ባለመብት, Tenawo

አገር ውስጥ የሌሉ መድኃኒቶችን ፍለጋ

በቀድሞ ጊዜ የምሽት ተረኛ መድኃኒት ቤቶች በየቀኑ በብሔራዊ ራዲዮ ይነገሩ ነበር፡፡

ልክ ዛሬ የአየር ትንበያና ስፖርት ዘገባዎች ከዜና በኋላ እንደሚታወጁት ሁሉ፡፡

ዛሬ ይህ ነገር መኖሩን እንጃ፡፡

ዜጎች አጣዳፊ የመድኃኒት ጥያቄ ቢገጥማቸው እንግልታቸውን ለማስቀረት ያለመ ነበር ነገሩ፡፡

ያን ጊዜ ጥቂት ፋርማሲዎች ነበር በከተማው የነበሩት፡፡

አሁን መድኃኒት ቤቶች እንደ አሸን በፈሉበት ዘመን፣ ኮንዶሚንየም ግቢ ድረስ ዘልቀው የነዋሪዎች ጎረቤት መሆን በቻሉበት ዘመን ነገሩ ያን ያህልም አልተቃለለም፡፡ ለምን?

መድኃኒት ቤቶችን እንጂ መድኃኒቶችን ማግኘት አልተቻለም፡፡

ይህ ሀቅ የጤናዎ መተግበሪያ ፈጣሪዎችም የሚክዱት አይደለም፡፡

በቂ መድኃኒቶች በሌሉበት ፋርማሲ መጠቆም ምን ይፈይዳል?

በገበያ የሚገኙት መድኃኒት ቤቶችማ ወትሮም የትም የሚገኙ ናቸው፡፡ የማይገኙት ደግሞ የትም አይገኙም፡፡

ዶ/ር ሲሳይ ይህን ሁኔታ ድርጅታቸው እንደሚረዳ ለቢቢሲ አስረድተው ለዚህም ሲባል መድኃኒት ከውጭ የማስመጣት ፍቃድ መውሰዳቸውን አብራርተዋል፡፡

ለጊዜው ሰዎች ከገበያ ያጧቸውን መድኃኒቶች በተናጥል ጥያቄ ሲያቀርቡልን ከውጭ ለማስመጣት ዝግጅት ጨርሰናል ይላሉ፡፡

ዶ/ር ሲሳይ እንደሚሉት ታዲያ የጤና ድርጅቱ ሥራ በመድኃኒት አድራሻና ዋጋ ጥቆማ የሚቆም አይደለም፡፡

ለምሳሌ ኤምአርአይ ወይም ሌላ የኢሜጂንግ ወይም የላቦራቶሪ አገልግሎት የሚፈልግ ደንበኛ በአቅራቢያው ይህን አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ስለመኖር አለመኖሩ፣ የዋጋ ዝርዝሩን እና ለአገልግሎቱ የሚጠየቀውን ተያያዥ መረጃ ሁሉ አቀናጅቶ አስቀድሞ መረጃ የማቀበል ተግባርም በመስጠት ላይ ናቸው፡፡

በጤና ሚኒስቴር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገመቺስ መልካሙ ይህ አዲስ የጤና መተግበሪያ የተገልጋይ እንግልትን፣ ጊዜና ጉልበትን በመቆጠብ ሁነኛ ሚና እንደሚጫወት መተግበሪያው በተመረቀበት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው አድናቆታቸውን ገልጠው ነበር፡፡

ይህ መተግበሪያ፣ የጥሪ ማዕከልና የጤና ድረ ገጽ ኅብረተሰብን በማገዝ ረገድ ሁነኛ ሚና ስላለው መሥሪያ ቤታቸው አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ብቅ ጥልቅ እያሉም ቢሆን የጤና ዘርፉን ለማዘመን የተሞከሩ ሙከራዎች እንደነበሩ የጠቀሱት ዶ/ር ሲሳይ በበኩላቸው ጤናዎ መተግበሪያ አስተማማኝና ዘላቂ አገልግሎት ለመስጠት ከሐኪሞችና ከጤና ተቋማት ጋር መጠነ ሰፊ ግንኙነት መፍጠሩንና፣ በእስካሁኑ አጭር ተሞክሮም ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች እንዳዩም ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡

የዚህ አገልግሎት ልዩ ባህሪም የግል ዘርፉን የጤና አገልግሎት በአንድ ጥላ ጠቅልሎ መያዙ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

ይህም ማለት ሐኪም ቀጠሮ ከማስያዝ ጀምሮ እስከ መድኃኒት ዋጋ ድረስ ዲጂታል በሆነ አሠራር ቀላል ማድረግን፣ በዚህም የጤና ሥርዓቱን ማዘመንን ያካተተ ነው፡፡

የዲጂታል ነገር፣ እስኪዘልቅና ዘላቂነቱ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዳዲስ ይበል የሚያሰኙ ሐሳቦች ይመነጫሉ፡፡ ወዲያው ይከስማሉ፡፡

አንዱ ምክንያት የኅብረተሰቡ ለውጡን ለመቀበል ዳተኛ መሆን ነው፡፡ ወደ ሕዝብ አይዘልቁም፡፡ ቢዘልቁም ዘላቂነት አይኖራቸውም፡፡

በዚህ ረገድ ጤናዎ መተግበሪያ የት ርቀት ይሄድ ይሆን?

ዶ/ር ሲሳይ አንዱ ፈተና ይኸው መሆኑን አውስተዋል፡፡

ወደ ዲጂታል ሄልዝ ለመሸጋገር ለብዙ ሰዎች ቀላል እንዳልሆነ በዚህ አጭር ቆይታ ራሱ የተረዱት ዶ/ር ሲሳይ፣ ድርጅታቸው ታዲያ ሕዝቡን ከአግልግሎቱ ጋር በቀላሉ ለማስተዋወቅ በማሰብ ለጊዜው ማንኛውንም ክፍያ አየጠየቁ አለመሆኑን አብራርተዋል፡፡

‹‹ለጊዜው ከመቶ በላይ መድኃኒት ቤቶች ከኛ ጋር ለመሥራት ተመዝግበዋል፡፡ እነዚህ መድኃኒት ቤቶች አዲስ መድኃኒት ሲያስገቡም ሆነ ነባር መድኃኒቶችን ሽጠው ሲጨርሱ በኛ ሲስተም እየገቡ አሁናዊ መረጃን ለኅብረተሰቡ ያቀብላሉ፡፡ ሌሎችንም ለማሳመን እየሞከርን ነው›› ይላሉ ዶ/ር ሲሳይ፡፡

በኢትዮጵያ ከ60 ሚሊዮን የሚልቅ ሞባይል ተጠቃሚ ቢኖርም፣ የኢንተርኔት ተደራሽነቱና ዘመናዊ ስልክ ተጠቃሚው ቁጥር የዚህ ሲሶውን እንኳ አይሞላም፡፡

እርግጥ በአሁን ዘመን ብዙ አገልግሎቶች ወደ ሞባይል እየገቡ ነው፡፡ ገንዘብ ዝውውርም ከወረቀት ወደ ሞባይል እየተሸጋገረ ነው፡፡ ይሁንና የሕዝብን እምነት ማግኘት በቀላል የሚገኝ እሴት አይደለም፡፡

ዶ/ር ሲሳይም ይህን አይክዱም፤ ‹‹ወደ ዲጂታል ሽግግር ጉዞው ቀላል እንደማይሆን አውቀን ነው የተነሳነው፤ በኛ አገር ዲጂታል ቴክኖሎጂ ገና እያደገ ነው፡፡ ሰዎች እምነት ገና አላዳበሩም፡፡ ይህ ነገር ጊዜ ሊወስድ ይችላል›› ብለዋል፡፡

ይህን ለማገዝም ነው የሚመሩት ድርጅት ለሁሉም አገልግሎቶቻቸው ለጊዜው ክፍያን ላለመጠየቅ የወሰነው፡፡

ፈውስን ፍለጋ ወጥቶ በሽታን መሸመት

ወደ ዲጂታል ዓለም ለመግባት እዚያ እዚህም የሚታዩት ሙከራዎች ከብዙ በጥቂቱ ይሁንታን ያገኛሉ፡፡

በኢትዮጵያ ካየነው ሁሉ ለጊዜው በትራንስፖርት ዘርፍ የሰመረ ይመስላል፡፡ በፋይናንስ ዘርፍም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች ታይተዋል፡፡

በጤና ዘርፍ ግን እምብዛም አይደለም፡፡ እርግጥ የሰዎች የጤና ሰነድ ከገንዘብም በላይ ከለላን ይሻል፡፡ ደኅንነቱ የተጠበቀ የመረጃ አያያዝን መከተል ይፈልጋል፡፡

በዚህ ረገድ ብዙ ከተሠራ ከብዙ ትዕግስት ጋር ወደፊት መንፏቀቅ ይቻል ይሆናል፡፡

በተለይ የኅብረተሰብን ችግር ለመፍታት ያለሙ፣ መፍትሄ ላይ መሠረት ያደረጉ መተግበሪያዎች ሲሳኩም የዛኑ ያህል ሕይወት ዘዋሪ ናቸው፡፡

የኬ.ኤም.ኤስ ሄልዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ሲሳይ አበበ ደጋግመው እንደሚሉት፣ ሰዎች ፈውስ ፍለጋ ወጥተው፣ በሽታን ሸምተው መመለስ የለባቸውም፡፡

‹‹ጤናዎ ሁለገብ መተግበሪያ›› የጤናው ዘርፍ ዲጂታል ሽግግር ረዥሙ ጉዞ አንድ እርምጃ ይሆን?