ፑቲን በዩክሬን ጦርነት ጣልቃ የሚገባ አገር ላይ መብረቃዊ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ዛቱ

ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ጦርነት እጁን የሚያስገባ ማንኛውም አገር ላይ መብረቃዊ ጥቃት እንደሚፈጸምበት አስጠነቀቁ፡፡

ይህን ለማድረግ ደግሞ አገራቸው ሩሲያ አቅምም ብቃትም አላት ብለዋል፡፡

‹‹ማንም አገር አለኝ የማይለው የጦር መሣሪያ አለን፡፡…አስፈላጊ ከሆነ እንጠቀመዋለን›› ሲሉ ብዙዎችን ያሳሰበ ንግግር አድርገዋል፡፡

አንዳንድ ተንታኞች ፑቲን በዚህ ንግግራቸው ለመጠቆም የሞከሩት ባለስቲክ ሚሳኤልና የኑክሊየር መሣሪያን ነው በማለት ግምት ወስደዋል፡፡

ፑቲን ወረራውን በጀመሩ ማግስት ለጦር ሹማምንቶቻቸው የኑክሊየር መሣሪያ በተጠንቀቅ እንዲዘጋጅ ትዕዛዝ መስጠታቸው አይዘነጋም፡፡

ይህ የፑቲን መራር ንግግር የተሰማው ደግሞ ምዕራባዊያን ለዩክሬን እጅግ ውስብስብና ዘመናዊ መሣሪያዎችን በመስጠት በተጠመዱበት ማግስት ነው፡፡

በተለይም ባለፉት ቀናት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ኦስቲን በኪየቭ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

በዚህ ጉብኝታቸውም ለዩክሬን ወደ 700 ሚሊዮን ዶላር የተጠጋ እርዳታን ይፋ አድርገዋል፡፡

ከትናንት በስቲያ ደግሞ የምዕራብ አገራት በጀርመን ተሰብስበው ለዩክሬን የሚደረገውን የጦር መሣሪያ እርዳታ እንዴት ከዚህም በላቀ መልኩ ማሳደግ ይቻላል በሚል ተወያይተው ነበር፡፡

በጦርነት ጣልቃ ያለመግባት ጥብቅ ፖሊሲን ትከተል የነበረችው ጀርመን ሳይቀር ያልተጠበቀ የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ ለዩክሬን 50 የአየር መቃወሚያ ታንኮችን እሰጣለሁ ብላለች፡፡

በአሁን ጊዜ ጦርነቱ ተፋፍሞ የቀጠለ ቢሆንም የምዕራብ አገር ተንታኞች ሩሲያ በምሥራቅ ዩክሬን ልታደርገው ያሰበችው መጠነ ሰፊ ጥቃት እንደተስተጓጎለባት እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡

ሩሲያ ከዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ ከበባ ወደ ኋላ እንድታፈገፍግ ከተደረገች በኋላ ትኩረቷን ወደ ደቡብ ምሥራቅ ዩክሬን በተለይም ዶንባስ በሚባለው ክልል ለማድረግ ወስና ነበር፡፡

ይሁንና በምሥራቅ ግንባር ሩሲያ ያሰበችውን ግስጋሴ አላሳካችም፡፡ ከዩክሬናዊያን ያልጠበቀችው መከላከል ገጥሟታል፡፡በርካታ ወታደሮችም ተገድለውባታል፡፡

ይህ በአንዲህ እያለ የአውሮጳ ኅብረት ሩሲያ ለፖላንድና ቡልጋሪያ ጋዝ አልሸጥም ማለቷን አውግዟል፡፡

የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሊየን እንዳሉት ይህ የሚያሳየው ሩሲያ የማታስተማምን የንግድ አቅራቢ መሆኗን ነው፡፡

ሩሲያ በበኩሏ ይህን እርምጃ የወሰድኩት ወዳጅ ያልሆኑ አገራት ለማቀርብላቸው ጋዝ ክፍያቸውን በሩብል እንዲያደርጉ ያሳለፍኩትን ውሳኔ ፖላንድና ቡልጋሪያ ስላላከበሩት ነው ብላለች፡፡