በሩሲያ የጦርነት ተጎጂዎች መታሰቢያ ውስጥ 'የደነሰችው' ዛምቢያዊት የአምስት ዓመት እስር ሊጠብቃት ይችላል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, hmao.sledcom.ru
በሩሲያ ካንቲማንሲስክ ከተማ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች በሚዘከሩበት ማዕከል ውስጥ 'የተወዛወዘችው' የ21 ዓመቷ ዛቢያዊት ተማሪ ለእስር ተዳረጋ እንደነበር የዛምቢያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አረጋገጠ።
ካንቲማንሲስክ ከተማ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ የአንደኛ ዓመት ተማሪ የሆነችው ቲዎንግ ዚባ ለሰዓታት ታስራ የተለቀቀች ቢሆንም ጉዳዩ ወደ ከተማው አቃቤ ሕግ መመራቱንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ተማሪዋ በአንድ የጦር ተጎጂዎች መታሰቢያ ማዕከል ውስጥ ስትደንስ የሚያሳየው ቪዲዮ የተቀረጸው ከሳምንታት በፊት ነበር ተብሏል።
ታዲያ ይህንን ቪዲዮ ዚባ በኢንስታግራም ገጿ ላይ "ለሙታኑ መደነስ፣ በእርግጠኝነት ዛሬ በጥሩ ሁኔታ ይተኛሉ" ከሚል ጽሑፍ ጋር ከሁለት ቀናት በኋላ አጋርታዋለች።
ይህንንም ተከትሎ ሞስኮ ለሚገኘው የዛምቢያ ኤምባሲ በተሰጠ ማብራሪያ የተማሪዋ ድርጊት በናዚ ጉዳተኞች ላይ ለመቀለድ የተደረገ አጸያፊ ጽሑፍ ነው ሲል ያብራራል።
ፖሊስ የተማሪዋን ዜግነት እና ስም ሳይጠቅስ ዚባ ለድርጊቷ ይቅርታ ስትጠይቅ የሚያሳይ ቪዲዮን በማህበራዊ ሚዲያ አጋርቶም ነበር።
ዚባ የዳንሱን ቪዲዮ ካጋራች በኋላ በፖሊስ በተለቀቀው ቪዲዮ በእንግሊዝኛ "ባለፈው ለለቀቅኩት ቪዲዮ ይቅርታ እጠይቃለው" ብላለች።
"ያኔ ቪዲዮውን ሳጋራ የሞቱት ላይ ለመሳለቅ ወይም ንቀት ለማሳየት እንደልሆነ ተረዱኝ። ሁላችሁንም በጣም በጣም ይቅርታ። እንደተረዳችሁን እና ይቅር እንዳላችሁኝ ተስፋ አደርጋለሁ" ስል አክላለች።
ፖሊስ ጉዳዩን በቀጣዮቹ ሦስት ወራት እንደሚመረምር እንዲሁም ሰብአዊ በሆነ መንገድ እና የዚባን የትምህርት ጊዜ በማይሻማ ሁኔታ እንደሚያየው ለዛምቢያ ኤምባሲ መነገሩን የውጪ ጉዳይ ሚኔስቴር ገልጿል።
አንድ የግል ጋዜጣ እንደ ዘገበው ከሆነ ተማሪዋ ለድርጊቷ ከ25 እስከ 65 ሺህ ዶላር ወይም ከአንድ እስከ አምስት ዓመት የሚዘልቅ እስር ወይም የጉልበት ስራ ይጠብቃታል።












