ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና አጋሩ የልጃቸው ህይወት ማለፉን አስታወቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የማንቸስተር ዩናይትዱ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና አጋሩ ጆርጂና ሮድሪጌዝ የልጃቸው ህይወት ማለፉን "ወላጆች ሊሰማቸው የሚችለው ትልቁ ህመም" ሲሉ ገልጸውታል።
የ37 ዓመቱ ፖርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና የ28 ዓመቷ ሮድሪጌዝ መንታ ልጆችን እየጠበቁ ነበር።
ሴቷ ልጃቸው በሕይወት መትረፏን "ይህንን ጊዜ በተወሰነ ተስፋ እና ደስታ ለመኖር የሚያስችል ጥንካሬ ይሰጠናል" ሲሉ ገልጸውታል።
"ልጃችን፣ አንተ የእኛ መልዓክ ነህ። ሁልጊዜም እንወድሃለን" ሲሉ ሃሳባቸውን አካፍለዋል።
ጥንዶቹ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት "የልጃችንን ህይወት ማለፍ ስንገልጽ በጥልቅ ሃዘን ነው" ብለዋል።
"በክስተቱ ሁላችንም አዝነናል" ሲሉም አክለዋል።
ጥንዶቹ መንታ ልጅ እየጠበቁ መሆኑን ባለፈው ጥቅምት ነው ያሳወቁት።
'ህመምህ ህመማችን ነው። የምንመኝላችሁ ፍቅር እና ጥንካሬን ለአንተ እና ለቤተሰብህ ይድረስ" ሲል ክለቡ ማንቸስተር ዩናይትድ በትዊተር ገጹ አስፍሯል።
የቡድን አጋሩ ማርከስ ራሽፎርድ በትዊተር ገፁ ላይ "ወንድሜ በሃሳብ ከአንተ እና ከጆርጂና ጋር ነኝ። በጣም አዝኛለሁ" ብሏል።
የሮናልዶ የቀድሞ ክለብ ሪያል ማድሪድ በበኩሉ ክለቡ፣ ፕሬዝዳንቱ እና የዳይሬክተሮች ቦርድ "ከልብ አዝነዋል" ብሏል።
"ማድሪድ የቤተሰቡን ህመም ይጋራል። ሁላችሁምን መፅናናቱ ይድረሳችሁ" ሲሉ አክለዋል።
ማንቸስተር ሲቲ፣ ሊድስ ዩናይትድ እና ፕሪምየር ሊጉም የሐዘን መግለጫዎችን በትዊተር ገፃቸው አስተላልፈዋል።
ሮናልዶ እአአ በ2010 የተወለደ ክርስቲያኖ ጁኒየር የተባለ ወንድ ልጅ አለው።
መንትያዎቹ ኢቫ እና ማቲዮ በ2017 የተወለዱ ሲሆን ከሮድሪጌዝ ደግሞ አላና ማርቲና የተባለችና በ2017 የተወለደች ሴት ልጅ አላቸው።












