እንግሊዝ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ማቀዷን "ርካሽና ሥነ ምግባር የጎደለው" ስትል ኤርትራ ነቀፈች

የፎቶው ባለመብት, MINISTRY OF INFORMATION
ኤርትራ እንግሊዝ ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞችን ጉዳያቸውን ለማስፈፀም ወደ ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ሩዋንዳ ለመላክ ማቀዷን "ርካሽና ሥነ ምግባር የጎደለው" ስትል ተቃወመች።
የአገሪቷ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ትናንት ሚያዝያ 10፣ 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ "ሕገ ወጥ" ያለው ስምምነቱ በርካታ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ነው ብሏል።
በመሆኑም በገንዘብ ማበረታቻ የአፍሪካን አገር ተባባሪነት የሚጠይቅ "ርካሽ እና ሥነ ምግባር የጎደለው" ዕቅድ ሊወገዝ እንደሚገባው መግለጫው በአፅንኦት ገልጿል።
ባለፈው ሳምንት የዩኬ መንግሥት ኢንግሊሽ ቻናል ተብሎ በሚጠራው የውሃ አካል በኩል ወደ ዩኬ የሚገቡ አብዛኞቹን ጥገኝነት ጠያቂዎች በነጠላ አውሮፕላን ትኬት ወደ ሩዋንዳ እንደሚልክ ማስታወቁ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንስን ይህ የ120 ሚሊዮን ፓዎንድ ፖሊሲ፤ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ከሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ያድናል ብለዋል።
ይሁን እንጂ የስደተኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶችን ጨምሮ በርካቶች የዩኬ መንግሥትን ዕቅድ አጥብቀው ተችተዋል።
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴርም በመግለጫው በአጠቃላይ ዕቅዱን የነቀፈው ሲሆን የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ዋና መንስዔዎች፣ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች እና ሰቆቃ ለመሸፋፈን ያለመ ነው ብሏል።
መግለጫው አክሎም በውጫዊ አጀንዳዎች ከተቀሰቀሱ እና ከተባባሱ አስከፊ ግጭቶችና ጦርነቶች በተጨማሪ አንዳንድ አገራት በስውር የፖለቲካ ዓላማ በአንዳንድ አገራት ላይ "ስልታዊ የሕዝብ ቅነሳ እያደረጉ ነው" ሲልም ወቅሷል።
እነዚህም ዓለም አቀፋዊና ብዙ መልክ ያለው ወንጀል ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያሻው ወሳኝ ማሳያዎች ናቸው ብሏል።
ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላኩን ዕቅድ እነማን ተቃወሙ?
- በዩኬ ተቃዋሚው የሌበር ፓርቲ መሪ ሰር ኪዬር ስታርመር "ሊተገበር የማይችል" እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮቪድ ክልከላዎችን ተላልፈው ተገኝተው የቀረበባቸውን ትችት ለማስቀየር ያመጡት ሃሳብ ነው ሲሉ ኮንነዋል።
- የስደተኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶችም ይህ ፕሮግራም ዩኬን ሊያስወጣ የሚችለውን ከፍተኛ ወጪ እና የሩዋንዳ የሰብዓዊ መብት አያያዝን ጥያቄ ውስጥ ከትተዋል።
- ከ160 በላይ የሚሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና ዘመቻ የሚያካሂዱ ቡድኖች ዕቅዱን "ጭካኔ የተሞላበት ነው" ሲሉ ሚኒስትሮች ሃሳባቸውን እንዲሰርዙ አሳስበዋል።
- የእንግሊዙ ጳጳስ ዕቅዱ " ከአምላክ ሥራ ጋር የሚቃረን ነው" ሲሉ ተቃውመውታል። ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ ባደረጉት ስብከት የክርስቶስ ትንሳኤ ኃላፊነታችንን የምንቀንስበት አይደለም" ብለዋል።
- የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ ሩዋንዳ መላክ ዓለም አቀፍ ሕግን እንደሚጻረር የገለጸ ሲሆን "የጥገኝነት ጠያቂዎችን ጉዳይ የመመልከት ኃላፊነትን ወደ ሌላ አገር ማዘዋወር ተቀባይነት የለውም" ብሏል።
ስምምነቱ ምን ይላል?
የስደተኞች ቅበላን በተመለከተ በዩኬ እና ሩዋንዳ መንግሥታት መካከል የተደረሰው ስምምነት ዝርዝር እስካሁን ይፋ አልሆነም።
ይሁን እንጂ ከዩኬ ወደ ሩዋንዳ እንዲሸጋገሩ የሚደረጉት ስደተኞች አብዛኛዎቹ ነጠላ ወንዶች እንደሚሆኑ ተገልጿል።
በስምምነቱ መሠረት ሩዋንዳ ከዩኬ የምትቀበላቸውን ስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄ ትመረምራለች።
የስደተኛው የጥገኝነት ጥያቄ ምላሸ የሚያገኝ ከሆነ በሩዋንዳ እንዲኖር ይፈቀድለታል። በሩዋንዳ የመኖር ፍላጎት የሌለው ስደተኛ ወደ ትውልድ አገሩ ወይም ሊቀበለው ወደሚችለው ሦስተኛ አገር ሊዘዋወር ይችላል።
የሩዋንዳ መንግሥት "ስደተኞች በአገሪቱ ሕግ ሙሉ ጥበቃ ይደረግላቸዋል፤ እኩል የሥራ ቅጥር መብት፣ የጤና እና የማሕበራዊ አገልግሎቶችንም ያገኛሉ" ብሏል።












