ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ መላክን የሚተቹት የተሻለ መፍትሄ የላቸውም: የዩኬ ሚኒስትር

የዩናይትድ ኪንግደም የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሪቲ ፓቴል እና የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪንሴንት ቢሩታ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የዩናይትድ ኪንግደም የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሪቲ ፓቴል እና የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪንሴንት ቢሩታ

የዩናይትድ ኪንግደም የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሪቲ ፓቴል መንግሥት ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ያቀረበውን እቅድ የሚቃመሙ ሰዎች የተሻለ መፍትሄ ማቅረብ አልቻሉም ሲሉ ወቅሰዋል።

ሚኒስትሯ ከሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በጋራ ታይምስ መጽህሄት ላይ ባወጡት ጽሁፍ የሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ ያለውን ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ለመግታት አዲስ መፍትሄ ነው ያመጣነው ብለዋል።

ያመከራ እንዲቀጥል የትኛውም ሰብዓዊነት የሚሰማው ሀገር ሊፈቅድ አይችልም ብለዋል ሁለቱ ሚኒስትሮች በጽሑፋቸው።

ይህ የሚኒስትሮቹ አስተያየት የተሰማው የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ ሰድተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመላክን እቅድ ክፉኛ ከተቹ በኋላ ነው።

ፓቴል እና የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪንሴንት ቢሩታ በሰብዓዊ ቀውሶች እና በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ምክንያት ጥገኞችን የመቀበያው ዓለም አቀፉ ስርዓት እየተዳከመ ነው ብለዋል።

በህገ ወጥ መንገድ ወደ ዩኬ የሚገቡ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለማጓጓዝ የተያዘው እቅድ የስደተኞችን ደህንነት ለመጠበቅ ያግዛል ብለዋል።

ሚኒስትሮቹ በጽሑፋቸው ዩናይትድ ኪንግደም በሩዋንዳ 120 ሚሊዮን ፓውንድ መነሻ በጀት በትምህርታዊ ፕሮጀክቶች ላይ የምታደርገው ኢንቨስትመንት በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት የሚሰደዱ ሰዎችን ችግር ለመቅረፍ ያግዛል ብለዋል።

"ጠንካራ እና አዳዲስ እርምጃዎችን እየወሰድን ነው። እቅዶቹን የሚተቹ ተቋማት ግን መፍትሄ የሚሉትን ነገር አለማቅረባቸው አስገራሚ ነው። . . . ይህ ስቃይ እንዲቀጥል መፍቀድ ለማንኛውም ሰብአዊ ሀገር አማራጭ መሆኑ አክተሞለታል "ሲሉም ጽፈዋል።

ሁለቱ ሀገራት በደረሱበት ስምምነት መሰረት በሩዋንዳ የሚገኙ አንዳንድ ስደተኞች ወደ ዩኬ እንደሚላኩም ታውቋል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት ምንጭ ለቢቢሲ እንደገለፀው ሩዋንዳ "በጣም ተጋላጭ የሆኑ የተወሰኑ ስደተኞችን" ለማቋቋም በምትታደርገው ጥረት ዩኬ ድጋፍ ታደርጋለች።

ትላንት በተከበረው የፈረንጆቹ ትንሳኤ ላይ የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ እቅዱን በመተቸት መንግሥትን "ሀላፊነታችንን በተቋራጭ" ለሌላ አካል ሰጥቷል ብለው የተቹ ሲሆን ውሳኔው የፈጣሪን ፍቃድ የሚጻረር ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

የዮርክ ሊቀ ጳጳስ እስጢፋኖስ ኮትሬል ሃሳብ የተጋሩት ጳጳሱ ፖሊሲው አስጨናቂ ነው ያሉ ሲሆን ከዚህ የተሻለ ነገር ማድረግ እንችላለን ብለዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲ እና አንዳንድ የወግ አጥባቂ ፓርላማ አባላት እቅዱን ተችተውታል። በሌላ በኩል ከ160 በላይ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ዘመቻ የሚያደርጉ ቡድኖች "አሳፋሪ ጨካኔ" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ፓቴል ዕቅዱን እንዲሰርዙ አሳስበዋል።

ተቺዎቹ ያሳስበናል ከሚሉት ጉዳዮች መካከል የሩዋንዳ የሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳይ አንዱ ሲሆን ዩኬ ባለፈው ዓመት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሀገሪቱ ውስጥ አለ ያለችውን ያለፍርድ መግደል፣ የሰዎች መጥፋት እና ማሰቃየትን ማንሳቷን ያነሳሉ።

ሆኖም ፓቴል እና ቢሩታ ይህንን ወቀሳ አይቀበሉትም። በታይምስ ፅሁፋቸው ላይ ሩዋንዳ "በዓለም ደህንነታቸው ከተጠበቁ ሀገራት መካከል አንዷ ነች" ያሉ ሲሆን ቀድሞውንም 130 ሺህ በላይ ከበርካታ ሀገራት የመጡ ስደተኞችን ተቀብላለች ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ሚኒስትሯ እና የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዕቅዱ አደገኛ ጉዞዎችን በማድረግ ስደተኞች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ እንዳይጥሉ ያደርጋቸዋል ቢሉም የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣን የላኩት ደብዳቤ ግን የዕቅዱ ውጤታማነት ግን እጅግ ያጠራጥራል።

ቋሚ ጸሃፊ ማቲው ራይክሮፍት በደብዳቤያቸው ፖሊሲው ከፍተኛ ወጪ እንደሚያስወጣ ጠቁመዋል።