“በሶማሌ ሕዝብ ላይ የተፈጸመው ወንጀል የብሔራዊ ምክክሩ አካል መሆን አለበት” የኦብነግ ሊቀመንበር

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር መስራች እና ሊቀ መንበር አብድራህማን መሀዲ
የምስሉ መግለጫ, የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር መስራች እና ሊቀ መንበር አብድራህማን መሀዲ

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር መስራች እና ሊቀ መንበር አብድራህማን መሀዲ በሶማሌ ሕዝብ ላይ የተፈጸመው ወንጀል የብሔራዊ ምክክሩ አጀንዳ አካል መሆን አለበት ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ከኦብነግ ሊቀ መንበር ከአቶ አብድራህማን መሀዲ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ቆይታ አድርጓል። ሊቀ መንበሩ በሶማሌ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ ስለ ቀድሞ የክልሉ ፕሬዝደንት እና በብሔራዊ ምክክሩ ጉዳይ ዙሪያ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከቢቢሲ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሚከተለውን ምላሸ ሰጥተዋል።

line

ቢቢሲ፡ አቶ አብድራህማን በኬንያ መዲና ናይሮቢ ረዘም ያለ ቆይታ ያለው ጉብኝት አድርገዋል። በርካቶች የዚህ ጉብኝት ዓላማ የኢትዮጵያ መንግሥትን ለመቃወም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለመቀላቀል ነው ይላሉ። የጉዞዎት ዋና ዓላማ ምንድን ነው?

አቶ አብድራህማን፡ ኬንያ በአፍሪካ ቀንድ ቁልፍ አገር እንዲሁም ትልቅ የሶማሌ ሕብረተሰብ መገኛ መሆኗ ይታወቃል። ትልቅ ቁጥር ያለው የሶማሊ ስደተኞች በኬንያ ይገኛሉ። በርግጥ ከዚህ ቀደምም እዚህ አገር እንቅስቃሴዎች አሉን።

ኬንያ በተለይም ከዚህ ቀደም በኦብነግ እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል እርቅ እንዲመጣ ድርድሮችን በማስተናገድ ያደረገችው አስተዋጽኦም አይዘነጋም። የኢትዮጵያን መጻኢ እድል በሚወስኑ ሂደቶች ሁሉ የሶማሌ ሕዝብን ወክለን በእያንዳንዱ የውሳኔ ሂደት ውስጥ መሳተፍ እንፈልጋለን።

ሌላው ግን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ እንደመሆናችን ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተገናኝንም እንወያያለን። ይህ ማለት ግን የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የመሪዎቹ ጠላት ነን ማለት አይደለም። ነገር ግን አገሪቷ እየተመራችበት ስላለችበት መንገድ ሀሳባችንን እንሰጣለን።

ኢትዮጵያ ሕብረ-ብሔራዊ አገር ናት። መጪዋ ኢትዮጵያ ሁሉም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች መብቶቻቸው የሚከበሩባት እንድትሆን ነው የምንሰራው። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ቁስል አለ። እኛ እሱን ለማባባስ ሳይሆን እሱን ለማከም የድርሻችንን ለመወጣት ነው የምንሰራው።

line

ለበርካታ ዓመታት በምሥራቃዊው የአገሪቱ አካባቢ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ የነበረው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ ወደ አገር ቤት ተመልሶ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ለመሳተፍ መወሰኑ ይታወሳል።

ይሁን ፓርቲው ከመራጮች ምዝገባ እና ከምርጫ ሂደት ጋር የተያያዙ የተከሰቱ ችግሮ አልተቀረፉም በማለት በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ሳይሳተፍ መቅረቱ ይታወሳል።

line

ቢቢሲ፡ አገር አቀፉን ምርጫ ጥላችሁ በመውጣታችሁ ትቆጫላችሁ? ሌሎች ፓርቲዎች አንድም ሁለትም መቀመጫ ይዘው ድምጻቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።

አቶ አብድራህማን፡ ላለፉት 30 አመት የታገልነው እኮ ራስን በራስ ለማስተዳደር እና ለዴሞክራሲ ነው። ያ ነው አሁን የተጣሰው። እናም በአጸፋው ያሳለፍነውን ውሳኔ አንጸጸትበትም። መጀመሪያ እጩዎቻችንን እንዳናስመዘግብ ከለከሉን። ከዛ በምርጫ ቦርድ ጥረት ነው 140 ዕጩዎች አዲስ አበባ ሄደው እንዲመዘገቡ የተደረገው።

ቀጥሎ የምርጫ ካርድ መስረቅ ጀመሩ። አባላቶቻችን እንዳይመርጡ ተደረጉ። ታዲያ ማን ነበር የሚመርጠው? የመራጮች ምዝገባ ካርዶችን ወደየቤታቸው ወሰዱ። ይህንን በማስረጃ ነው ለምርጫ ቦርድ ያረጋገጥነው።

በሚያሳዝን ሁኔታ ቦርዱ ትኩረት አልሰጠውም። ይህም በሰሜኑ ጦርነት እና በሌሎች ምክንያቶች ነው። ውጤቱ ምን እንደሆነ እያወቅን እንዲሁም በተጭበረበረ ምርጫ ለምን እንወዳደራለን? ለቦርዱ ሰብሳቢ ክብር አለን። ለዴሞክራሲ በመቆማቸው ዋጋ ከፍለዋል። ነገር ግን ምርጫ ቦርድ አንድ ሰው አይደለም። በዚህ ምርጫ ቦርዱ የሶማሌ ሕዝብን በተመለከተ ኃላፊነቱን አልተወጣም ብለን እናምናለን።

ስለዚህ እኛ እየታገልን ያለነው ለመርህ እንጂ ለስልጣን መንበር አይደለም። ስለዚህ ይህ መርህ ተጥሷል ብለን ስላመንን ለመርሃችን መቆም አለብን።

ድርቅ

የፎቶው ባለመብት, ERIC LAFFORGUE/ART IN ALL OF US

የምስሉ መግለጫ, በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች በ40 ዓመታት ውስጥ የከፋ ነው የተባለ ድርቅ እንዳጋጠመ የአሜሪካ መንግሥት የልማት ድርጅት-ዩኤስኤይድ አስታውቆ ነበር።

ቢቢሲ፡ የሶማሌ ክልልን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ድርቅ ተከስቷል። የእርስዎ ፓርቲ ከተቃውሞ ባለፈ የድርቁን ጫና ለመቀነስ ምን የሚጨበጥ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል?

አቶ አብድራህማን፡ ለክልሉ፣ ለፌደራል መንግሥት እና ለዓለም-አቀፉ ሕብረተሰብ የመጀመሪያውን የአደጋ ደወል ያሰማነው እኛ ነን። ነገሮች ሳይባባሱ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ ስናቀርብ ነበር።

ጥሪያችንን ወደ ጎን በማለት እርምጃ መውሰድ የጀመሩት ዘግይተው ነው። አሁን ቀውሱ ተባብሷል። ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብ አደጋ ላይ ወድቋል። ነገሩ ከኢትዮጵያ መንግሥት አቅም በላይ የሆነ ይመስለኛል። ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ደግሞ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ተጠምዷል። እስካሁን 60 በመቶው የእንስሳ ሃብት ረግፏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ፕሬዘዳንቷ ወደ ክልሉ መጥተው ጎብኝተዋል። ነገር ግን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ማወጅ አለባቸው። ልክ እንደ ሰሜኑ ሁሉም ምስራቁም ትኩረት ይፈልጋል። ለሰሜን ኢትዮጵያ ከተመደበው በጀት ጋር ለሶማሌ ክልል የአደጋ ምላሽ የተመደበው ገንዘብ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

ለጦርነቱ መልሶ ግንባታ 120 ቢሊዮን ብር ሲመደብ ለሶማሌ ክልል የድርቅ ምላሽ 500 ሚሊዮን ነው የተመደበው። ስለዚህ በቂ ትኩረት አልተሰጠውም ማለት እችላለሁ። እኛ ጥሪ ከማቅረብ ውጪ ምንም ማድረግ አንችልም።

በጀቱም ሆነ የፖለቲካ አቅም የለንም። አሁን ማንንም እየወቀስን ሳይሆን በርካታ ተጨማሪ ስራዎች መሰራት አለባቸው ብለን እናምናለን።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ድንበር መክፈት ይገባታል። ማንኛውም ሰው ከሶማሊያ እንዲመጣ መፍቀድ ያስፈልጋል። ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብም ከሶማሊያ፥ ጂቡቲም ሆነ ከኬንያ ጋር በመተባባር በጋር መስራት አለበት። አሁን ያለው ሁኔታ የአደጋ ግዜ ምላሽ ነው የሚያስፈልገው።

line

በደቡብ እና በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ በተለይ በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳትን አስከትሏል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይህ ድርቅ በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልል ያሉ 8 ሚሊዮን ሕዝብ ጎድቷል ይላል።

የተመድ የሰብዓዊ እርዳታዎች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ዞኖችን ከጎበኘ በኋላ መጋቢት 28/2014 ዓ.ም. ባወጠው ሪፖርት ላይ አጋር ድርጅቶች ለድርቁ ምላሸ መስጠት ዋና ትኩረታቸው እንዲሆን ጠይቋል።

ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው መጋቢት 29/2014 ላይ የሶማሌ ክልል ፕሬዝደንትን በክልሉ ያጋጠመው ድርቅ በቅርብ ጊዜ እንደሚጠናቀቅ እና የመንግሥት ምላሸ እንደሚቀጥል ተናግረዋል ሲል ዘግቧል።

line

ቢቢሲ፡ መንግሥት ድርቁ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን እየገለጸ ነው። እናንተ በርግጥ መደረግ እየተቻለ ሳይደረግ የቀረ ነገር ብላችሁ የምትጠቅሱት ምንድን ነው?

አቶ አብድራህማን፡ ከሶስት ወራት በፊት የሶማሌ ክልል ፕሬዘዳንትን አግኝቼ አነጋግሬው ነበር። ሁሉም ነገር በቁጥጥር ስር ነው አለኝ። ነገር ግን ይህ ትክክል አልነበረም።

እነርሱ ችግሩን አቅልለው እያዩት ነበር። አሁን እንደተረዳነው ለዚህ ድርቅ የተመደበ በጀት እንደነበረ እና እሱን ለምርጫ እንዳዋሉት ነው። ስለዚህ ይህ ድርቅ እንደሚመጣ ይታወቅ ነበር። ዘግይተው ነው መንቀሳቀስ የጀመሩት፤ እያደረጉት ያለውም ጥቂት ነው።

ገንዘብ እየሰጡ እንዳለ ተረድቻለሁ ነገር ግን በገንዘቡ የሚገዙት ምግብ እንኳን የለም።

የዚህ ችግር መሰረቱ ነገሮችን የመሸፋፈን ባሕል ነው። ረሃቡን እኮ እነሱ (መንግሥት) አላመጡትም፤ ተፈጥሯዊ ችግር ነው።

የእነሱ ችግር ነገሩን የያዙበት መንገድ ነው። ተጨማሪ እርዳታ በወቅቱ በማሰባሰብ የመንግሥት ሃብትን ቢያስተባብሩ የተሸለ ነገር ማድረግ ይችሉ ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ነገሮችን የመሸፋፈን አካሄድ ትክክል አይደለም።

በጥሩ እና መጥፎ መንግሥት መካከል ያለው ልዩነት የራሱ ጥፋት ያልሆነ እና የተፈጥሮ ችግር የሆነ ነገርን ለመደበቅ መሞከር እና ግልጽ በመሆን መካከል ነው።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ ሙሐመድ ኡመር
የምስሉ መግለጫ, የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ ሙሐመድ ኡመር

ቢቢሲ፡ ከሶማሌ ክልል ባለስልጣኖች በተለይም ከፕሬዘዳንት ሙስጠፌ ጋር ያላችሁ ግጭት በስልጣን ይገባኛል ነው የመጣው የሚሉ ትችቶች ይነሳባችኋል። በተለይም ከምርጫው በኋላ በነበረው የስልጣን ክፍፍል።

አቶ አብድራህማን፡ ስልጣንን ለማረቅ የተሻለው መንገድ ሕዝብ የሚፈልገውን እንዲመርጥ ማድረግ ነው። ይህ ካልሆነ ነው ግጭት የሚመጣው። እኛ በስልጣን መጋራት ወንበር ለመውሰድ ፍለጎት የለንም።

የምንፈልገው ሕዝባችን የሚፈልገውን እንዲመርጥ እድሉ እንዲሰጠው ነው። ለምሳሌ በምርጫ 30 ወይ 60 በመቶ ብናገኝ ቁጭ ብለን ተደራድረን ስልጣን እንጋራለን። ነገር ግን ሁሉንም ነገር ከተዘረፈ በኋላ ሁለት ሶስት መቀመጫ ሰጥቼ የስልጣን መጋራት ነው ቢባል እኛ አይሆንም ነው የምንለው።

ከምርጫው በኋላ ሁለት የክልል ቢሮ ኃላፊነት ለመስጠት ጠይቀውን አንፈልግም ብለን ትተናል። ምክንያቱም ተጭበርብሯል ባልነው ስርዓት ውስጥ እንዴት መልሰን አካል መሆን እንችላለን?

ቢቢሲ፡ አዲስ በተዋቀረው የሶማሌ ክልል መንግሥት ውስጥ ግን የእናንተ አባላት ተካትተዋል አይደለም?

አቶ አብድራህማን፡ በፍጹም፤ እነሱ ከፓርቲው የተባረሩ ሰዎች ናቸው። የክልሉ መንግሥት በፓርቲያችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የተወሰኑ አባላቶቻችን አስኮብልሏል። ሁለት ለክልል ቢሮ አንድ ለፌደራል ሚኒስትር መስሪያ ቤት ተሹመዋል። ስለዚህ እኛ እነሱን እንደ ብልጽግና ነው የምንቆጥራቸው።

ቢቢሲ፡ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን መዋቅር እና የተቋቋመበት ሂደት ፓርቲያችሁ እንዴት ይመለከተዋል?

አቶ አብድራህማን፡ መንግሥት አደርጋለሁ ብሎ ያሰበው ምክክር ልክ እንደምርጫው ሁሉ ችግር ያለበት ነው። መንግሥት ምርጫውን ለማራዘም በሚሞክረበት ወቅት እአአ በ2019 ላይ ነበር ብሔራዊ ምክክር ይደረግ የሚለውን ሃሳብ ያቀረብነው።

ያኔ መንግሥት አሻፈረኝ አለ። ምርጫውም ተደረገ። መንግሥት አሁን የብሔራዊ ምክክር ሃሳብን ተቀብሏል፤ ነገር ግን እርስ በእርሳቸው ለመነጋጋር ካልሆነ በቀረ ይሄ ብሔራዊ ምክክር አይደለም።

ከአንድ ፓርቲ የመጡ ሰዎች ናቸው የኮሚሽኑ አባል ሆነው የተቀመጡት። ሕዝብ መርጧቸዋል ቢባልም እኛ ግን እናውቃቸዋለን። ከሶማሌ ክልል እኮ ማን እንደሚላክ ምርጫው ከማለቁ ከአንድ ወር በፊት እናውቅ ነበር።

ይህ የአገሪቱ ብቸኛ እድል ነው ብለን እናምናለን። አዲስ ማሕበራዊ ውል ማሰር አለብን።

line

ኢትዮጵያ በአገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ተደርጎ ብሔራዊ መግባባት እንዲመጠ ሂደቱን የሚመራ ኮሚሽን አቋቁማለች።

ምንም እንኳ ገለልተኛ የሆኑ የኮሚሽኑ አባላት ከሕዝብ፣ ከፖለቲካ ድርጅቶችና ከሲቪል ማኅበራት ጥቆማ መሠረት የተመረጡ ናቸው ቢባልም በአባላቱ ላይ በርካታ አስተያየቶችና ትችቶችን ሲያስተናግድ ቆይቷል።

line

አቶ አብድራህማን፡አሁን ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ማወቅ ያለባቸው ነገር ቢኖር አገሩ የእነርሱ ብቻ እንዳልሆነ ነው። ይሄ አገር የሁሉም ነው። ሁሉም ሕዝብ የአገሩ ባለቤት ነው።

የተሻለ መጻኢ እድል እንዲሁም ሰላም እንዲኖር ካስፈለገ የተለየ አቋም ያላቸው ሰዎች ድምጽ መሰማት አለበት። ትልቅ ናቸው፣ ብዙ ናቸው ወይም ትንሽ ናቸው ሳይባል የሁሉም ድምጽ መሰማት አለበት።

ስለዚህ እያልን ያለነው የዚህ አገር ባለቤትነት የጋራችን ነው። አንድ ቡድን ወይም ፓርቲ ሁሉን ነገር በበላይነት ሊይዝ አይችልም ነው። እንደዛ ያለ የአስተዳደር መንገድ ጠቃሚ ስላልሆነ በመላው አለም እየተቀየረ ነው።

እኛም ለላፈው 100 አመት ሞክረነዋል። ምኒሊክ፣ ኃይለስላሴ፣ መንግሥቱ እና መለስ ሲገዙ አይተናል። አሁን አዲስ እድል አለን። ኢትዮጵያ በየ10 እና 20 ዓመቱ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት አዲስ እድል ታገኛለች። አሁን እንደዛ አይነት መሰረታዊ ለውጥ ነው የምንፈልገው።

ነገር ግን አሁን ወደ ኋላ እየተመለሰች ነው። ስለዚህ የሕዝቡ፣ የመሪዎች (የተቃዋሚዎችን ጨምሮ) እንዲሁም የዓለም አቀፉ ማሕብረሰብ ቆም ብሎ አሁን ስለቆምንበት ቁልፍ መንገድ ማሰብ ይጠበቅብናል።

አሁን የእዚህ አገር መሪ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድ ናቸው። ሌጋሲያቸውንውን ሊያስቀምጡ ይገባቸዋል። ባለፈው ሶስት አመት የተፈጠሩትን ችግሮች ማስተካከል ይቻላል።

ጦርነቱ መቆም ይገባዋል። ጦርነቱ ቆሞ እውነተኛ ንግግር መጀመር ይገባዋል። እየተገዳደልን ኩራት ምን ጥቅም አለነው? 'እኛ ኢትዮጵያዊያን ነን፤ የውጪ ጣልቃ ገብነት አንፈልግም' እንላለን።

ከውጭ ባለሙያዎችን ማምጣት አለብን። በዚህ ሂደት ውስጥ ካለፉ እንደ የመን፣ ደቡብ አፍሪካ እና የመን ሰዎችን ማምጣት አለብን። ምን ተሳካ ምን ሳይሳካ ቀረ የሚለውን ለማወቅ።

ቢቢሲ፡ ስለዚህ በሂደቱ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ናችሁ?

አቶ አብድራህማን፡ለመሳተፍ ፈቃደኛ ነን፤ ነገር ግን ቅድመ ሁኔታዎች አሉን። አሁን እየተሄደበት ያለው መንገድ አሳታፊ አይደለም። ሂደቱ በአንድ ፓርቲ ተጠልፎ ተወስዷል። ነገሩ በብልጽግና እጅ ነው ያለው።

ቢቢሲ፡ አንዳንድ የፓርቲያችሁ አባላት የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) ከእስር እንዲፈቱ እየጠየቁ ይገኛሉ። በዚህ ላይ የፓርቲያቸሁ አቋም ምንድነው?

አቶ አብድራህማን፡ አብዲ ኢሌ የራሱ ሕዝብ ላይ ወንጀል ፈጽሟል። ከእርሱ ጋር ጉዳይ አለን። ይሄ አንድ ነገር ነው። ለእኛ ይህ የሚያም ጉዳይ ነው።

በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር
የምስሉ መግለጫ, በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር

ቢቢሲ፡ በርግጥ አቶ አብዲ መሃመድ በስልጣን ላይ ሳሉ የእርስዎን ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች ዒላማ ሲያደርጉ ነበር።

አቶ አብድራህማን፡ አዎ፤ ነገር ግን እርሱ የስርአቱ አካል ነው እንጂ ለብቻው አላደረገውም። ጥያቄው የሶማሊ ሕዝብ ላይ ለሆነው ነገር ሁሉ ተጠያቂው አንድ ሰው አይደለም ነው። ይህንን ያደረገው አገሩ ነው። የኢትዮጵያ አገር።

ይሄ ኃላፊነት ሊወሰድ እና ሊመረመር የሚገባው ነው። ከገዢው ፓርቲ፣ እስከ መከላከያ ሠራዊቱ፣ በወቅቱ ስልጣን ላይ እስከነበሩት ሰዎች። እኛም እንደ ኦብነግ መመርመር ካለብን መመርመር አለብን። ነገር ግን የፖለቲካ እስረኞች በእስር መቀመጥ የለባቸውም።

አብዲ ኢሌም ወደ ፍርድ ቤት መወሰድ እና ጉዳዩም እንደ ወንጀል ነው መታየት ያለበት። ይልቁንም አሁን አንድ እስር ቤት ውስጥ ተዘግቶበት ነው ያለው።

ቢቢሲ፡ እዚህ ጋር አንድ ከባድ ቃል እየጠሩ ነው። የፖለቲካ እስረኛ የሚል። አብዲ ኢሌ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ነው እስር ላይ ያሉት ብላችሁ ታምናላችሁ ማለት ነው? እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የፖለቲካ እስረኛ ማለት በፖለቲካ አመለካከቱ ወይም አቋሙ ምክንያት ለእስር የተዳረገ ማለት ነው። ችሎት እየቀረቡም ነው። አብዲ መሐመድ በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት ነው የታሰሩት?

አቶ አብድራህማን፡ አብዲ ኢሌ የፖለቲካ ስርዓት አካል ነው። የእርሱ የወንጀል አጋር የነበሩ የመከላከያ አዛዦቹ እኮ አሁንም አዲስ አበባ ናቸው። ልክ እንደርሱ የፖለቲካ አመራር የነበሩም አሉ። ለምንድነው ታዲያ እሱ ብቻ የታሰረው?

እኛ ወንጀል አልሰራም አላልንም። ነገር ግን ያኔ ትዕዛዝ ሲሰጡት የነበሩት የፌደራል ሰዎች የታሉ? ለዛ ነው ክሱ የፖለቲካ አላማ ያለው ነው የምንለው። አሁን የሚሰበሰብበት ማስረጃ በስልጣኑ መጨረሻ ወራት በጅግጅጋ ከተማ የተፈጸመውን ወንጀል የተመለከተ ነው።

በኦጋዴን ላይ የተፈጸሙት ወንጀሎችስ? አንድም ግዜ በችሎት ሲጠቀሱ አንሰማም።

line

የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሃመድ ኡመር በቁጥጥር ሥር በዋሉ ወቅት በሶማሌ ክልል ውስጥ በሚገኙ ነዋሪዎች መካከል ግጭት በመቀስቀስና በግጭቱ የሚሳተፍ ቡድን የማደራጀት ሕገ ወጥ ድርጊት ፈጽመዋል የሚል ክስ በጠቅላይ አቃቤ ሕግ ተመስርቶባቸው ነበር።

አብዲ መሐመድ ሐምሌ 2010 ዓ.ም. ሀይማኖትና ብሔርን ለይቶ ግድያዎችን እና ጥቃቶችን ሰንዝሯል የተባለውን "ሄጎ" የተሰኘ ቡደን አሰልጥነውን በማሰማራት በፌደራል መንግሥቱ ክስ ቀርቦባቸው ነበር።

line

ቢቢሲ፡ ያኔ ከእርሳቸው ጋር ያበሩት ፍርድ ቤት ፊት ይቅረቡልን ማለት እና እርሱ ይለቀቅ ብሎ መጠየቅ የተለያዩ አይደሉም?

አቶ አብድራህማን፡ በፍጹም! ኦብነግ እሱ እንዲፈታ ጠይቆ አያውቅም። የት እና መቼ ነው ይለቀቅ ብለን የጠየቅነው?

ቢቢሲ፡ ፓርቲው መግለጫ አውጥቷል አላልኩም። ነገር ግን የፓርቲው አባል የሆኑ ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ ይህንን ሲያንጸባርቁ ነበር።

አቶ አብድራህማን፡ ይህ ትክክል አይደለም። ይህንን የጠየቀ የኦብነግ አባል የለም። አንድም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ወይም የስራ አስፈጻሚ ይህንን አልጠየቀም።

ይህንን እየጠየቀ ያለው የሶማሌ ሕዝብ ነው። እኛ ግን እንደ ፓርቲ በመደበኛ መልኩ ይህንን ጥያቄ አላቀረብንም። እያልን ያነው የ2007ቱ የጅምላ መቃብሮች በመላው ኦጋዴን (ሶማሌ ክልል) ይገኛሉ ነው።

በዛ ውስጥ የተሳተፉ የመከላከያ ጀነራሎች፣ የኢሕአዴግ የፌደራል ኃላፊዎች እንዲሁም የስር አባላት ተሳትፈውበታል ነው። የታሉ? ለምን አልተከሰሱም? አቃቤ ሕግ ለምን አብዲ ኢሌን ብቻ ከሰሰ? ሶማሌ ስለሆነ ነው? ይህንን ጥያቄ መጠየቅ አለብን።

በኦጋዴን(ሶማሌ ክልል) የተደረገው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ነው። ይህ በክልልም በፌደራልም የተፈጸመ ነው።

ቢቢሲ፡ እነሲህ ነጥቦች በብሔራዊ ምክክሩ ላይ ይነሱ የሚል አቋም አላችሁ?

አቶ አብድራህማን፡ አዎን ይህ የብሔራዊ ምክክሩ አካል መሆን አለበት። ሕዝባችን ካሳ ይፈልጋል። ኢትዮጵያ በሃገር ስም የሶማሌ ሕዝብ ላይ ወንጀል ፈጽሟል። ይህ ደግሞ በማስረጃ የተደገፈ ነው። በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት የተሰነደ ነው።

ስለዚህ አገሩ ለዚህ ምላሽ መስጠት ይገባዋል። ለዚህ ደግሞ የብሔራዊ ምክክሩ አካል መሆን የሚገባው አጀንዳ ነው። ከሶማሌ ክልል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የት እንደደረሱ አይታወቅም። ሃምሳ ሺ የሚሆኑ ሴቶች ተደፍረዋል። ወላጅ የሌላቸው ልጆች በየቦታው አሉ። ተርበው እና ታርዘው። ኢትዮጵያ ውስጥ ይሄ እኮ ተነስቶ አያውቅም። ስለዚህ ነው ውይይቱ ላይ ይቅረብ የምንለው።

በርግጥ ከዚህም በፊት ተፈጽሟል። በ1974፣ በ1964፣ በ1961 የአይሻ ጭፍጨፋ፣ የደገሃቡር ጭፍጨፋ፣ የሽላባ ጭፍጨፋ፣ የቀላቦ ጭፍጨፋ ምሳሌ ናቸው። ይህ የቀጠለ ስለሆነ መነጋገር አለብን። አሁን የሶማሌ ሕዝብ ገንዘብ ይፈልጋል ማለት አይደለም።

ነገር ግን ለዚህ ነገር መዝጊያ ማበጀት አለብን። ይህ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ያሉ ኢትዮጵያዊያንም የሚያነሱት ጥያቄ ነው። ኢትዮጵያ ሕዝቧ ላይ በተለያየ ግዜ ወንጀል ፈጽማለች። ኦሮሞም አማራም ጋር ብንሄድ ተመሳሳይ ችግር ተፈጥሯል። ስለዚህ ይህ ለውይይት መቅረብ አለበት።

line

ጥቂት ስለ ኦብነግ

ኦብነግ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1984 ነበር የተመሰረተው። ቡድኑ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ መንግሥት ሽብርተኛ ተብለው ከተሰየሙ ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ሦስት የፖለቲካ ቡድኖች ከሽብር ቡድን ዝርዝር ውስጥ በፓርላማው ውሳኔ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ በውጭ የሚገኙ የታጠቁ ተቃዋሚዎች ወደ አገር ቤት መመለሳቸው ይታወቃል።

አብነግ የኦጋዴን ሕዝብ ብሎ የሚጠራውን በምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚገኘው የሶማሌ ሕዝብ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ለማስከበር በፖለቲካዊና ወታደራዊ መስኮች ትግል ሲያደርግ ቆይቷል።

line

ቢቢሲ፡ አሁንም ድረስ 'ነጻነት ግንባር' የሚለው የፓርቲያችሁ መጠሪያን በተመለከተ ብዙ ጥያቄ እንደሚቀርብ አስባለሁ። የፓርቲዎት ቀዳሚ ዓላማ ከኢትዮጵያ ነጻ መውጣት ነው?

አቶ አብድራህማን፡ መገንጠል ወንጀል አይደለም። የሶማሌ ክልል ሕዝብ መገንጠል ከፈለገ በሕገ-መንግስቱ መሰረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ መጠየቅ ይችላል።

የሶማሌ ሕዝብ ከኢትዮጵያ አገረ መንግስት መብቱን ካላገኘ እና ጥሎ መሄድ ወይም ደግሞ የኢትዮጵያ አካል ሆኖ መቆየት ከፈለገ መብት አለው።

እኛ መገንጠልን አንቀሰቀስም ግን የሶማሌ ሕዝብ ይህን የመምረጥ መብት በእጁ ተጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ ነው ቀዳሚ አላማችን።

አንቀጽ 39ን እንጠብቀዋለን። ይህ የሕዝቡ ማሕበራዊ ዋስትና እንዲሁም ለተጠያቂነት የሚረዳ መብት ነው።

ሕዝባችን ሙሉ መብቱ እና ክብሩ ካልተሰጠው ጥሎ የመሄድ መብቱ የሚጠበቅበት ነው። ይህ የሶማሊ ብቻ አይደለም። የአማራው፣ የትግሬው፣ የአገው፣ የኦሮሞው፣ የሞጃው የሁሉም ነው። ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ይህ መብት እንዲጠበቅላቸው ይፈልጋሉ። በጋራ የምንጠብቀው መብት ነው።