"ሩሲያ የዩክሬንን ከተሞች ለማውደም ቆርጣ ተነስታለች"

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሩሲያ የዩክሬንን አበይት ከተሞች እንዳልነበሩ ለማድረግ እያፈራረሰች ነው ሲሉ የዩክሬን ባለሥልጣናት ተናገሩ።
የማሪዮፖል ከተማ ከንቲባ አማካሪ እንደሚሉት የሩሲያ ወታደሮች በከተማዋ የሚዘዋወሩ ሰዎችን የይለፍ ወረቀት እየጠየቁ ነው።
አማካሪው ፔትሮ አንድሪዮሼንኮ ቴሌግራም በተሰኘው መልዕክት መላላኪያ ሰዎች ተሰልፈው የይለፍ ወረቀት ሲጠየቁ የሚያሳይ ፎቶ አጋርተዋል።
ሰውዬው አክለው ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ይህ ወረቀት የሌለው ሰው በከተማዋ ለመዘዋወርም ይሁን ወጥቶ ለመሄድ አሊያም መንገድ ላይ መንቀሳቀስ አይቻለውም።
አማካሪው የሩሲያ ወታደሮች ይህን የሚያደርጉት በከተማዋ ማን እንደቀረ ለማወቅ ነው ይላሉ።
ሩሲያ አብዛኛውን የማሪዮፖል ክፍል ተቆጣጥሪያለሁ ትላለች፤ ዩክሬናዊያን ወታደሮች ደግሞ አዞቭስታል የሚባል የኢንዱስትሪ መንደር አቅራቢያ እንደተሸሸጉ ይታመናል። በሌላ በኩል የሉሃንስክ ነዋሪዎች ከተማዋን በፍጥነት ለቀው እንዲወጡ ታዘዋል።
ምስራቅ ዩክሬን የምትገኘው የዚች ከተማ ነዋሪዎች በፍጥነት ለቀው እንዲወጡ ታዘዋል ሲል የፃፈው የዩክሬኑ ዜና ወኪል ዩኒያን ነው።
የሉሃንስክ አስተዳዳሪ ሰርጌ ጋይዳይ "ምናልባት ይህ የመጨረሻ ዕድላችሁ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በኋላ ልናድናችሁ አንችልም» ሲሉ ለከተማዋ ነዋሪዎች መልዕክት ልከዋል።
የሩሲያ ወታደሮች አሁን ፊታቸውን ወደ ሉሃንስክና ዶኔስክ ያዞሩ ይመስላል።
ሁለቱ ከሰልና ብረት አምራች ከተሞች በምስራቃዊ የሃገሪቱ ክፍል የምትገኘው ዶንባስ ግዛት አካል ናቸው። ዶንባስ የሚገኙ የዩክሬን ወታደሮች ከሩሲያ ሊቃጣ የሚችለውን ከባድ እርምጃ ለመግታት ዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በተያያዘ ዘገባ የዩክሬኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ሩሲያ የዩክሬን ከተሞች ለማውደም ቆርጣ ተነስታለች ብለዋል።
በተለይ ደግሞ የወደብ ከተማዋ ማሪዮፖልን "በየትኛውም መንገድ ዶግ አመድ ለማድረግ ወስናለች" ሲሉ ተደምጠዋል።
ከሰዓታት በፊት የዩክሬኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴኒስ ሺምሃል ማሪዮፖል "በጠላት እጅ አትወድቅም" ብለው ነበር።
ሩሲያ በከተማዋ ያሉ የዩክሬን ተዋጊዎች እጃቸውን እንዲሰጡ ቀነ ገደብ አስቀምጣለች።
ዋና ከተማዋ ኪይቭ አቅራቢ ብዙ ሽንፈቶች ያስተናገደችው ሩሲያ አሁን ትኩረቷን ወደ ምስራቁ የዩክሬን ክፍል ያደረገች ይመስላል።
የሩሲያ ወታደሮችና የዩክሬን ተዋጊዎች በዶንባስ ግዛት ከባድ የሆነ ግጭት ውስጥ እንደሚገቡ ተተንብይዋል። በሌላ በኩል ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ወደ ፖላንድ ተሰደው የነበሩ ዩክሬናዊያን ወደ ሃገራቸው መመለስ ጀምረዋል።
ባለፈው ቅዳሜ 22 ሺህ ገደማ ዩክሬናዊያን ስደተኞች ወደ ሃገራቸው የተመለሱ ሲሆን አሁን ፖላንድ ድንበር ላይ የሚገኙ ስደተኞች ቁጥር ከ19 ሺህ በላይ ነው።












