በስዊድን የተካሄደው ቅዱስ ቁርዓንን የማቃጠል መርሐ-ግብር ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በስዊድን ቅዱስ ቁርዓንን የማቃጠል መርሐ ግብር መካሄዱን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ቁጣ 4ኛ ቀኑን ይዟል፡፡
በበርካታ የስዊድን ከተሞች ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰዎች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል፡፡
ቅዱስ ቁርዓንን የማቃጠል መርሐ ግብር ያካሄደው ቀኝ ዘመም አክራሪ፣ ጥቁርና መጤ ጠል የሆነ ቡድን ነው፡፡
የአገሬው መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ ተቋሞውን ተከትሎ ሦስት ሰዎች ክፉኛ ቆስለዋል፡፡
በርካታ ንብረቶች ወድመዋል፡፡ የሕዝብና የግል ተሸከርካሪዎች ተቃጥለዋል፡፡
እስከ አሁን 17 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ፣ በደቡባዊቷ የስዊድን ከተማ፣ ማልመ፣ አውቶቡሶችን ጨምሮ በርካታ ተሸከርካሪዎች ተቃጥለዋል፡፡
ይህም የሆነው ሙስሊምና ስደተኛ ጠል የኾነው አክራሪ ቀኝ ዘመም ቡድን በከተማዋ ትዕይንተ ሕዝብ ማድረጉን ተከትሎ ነው፡፡
ድርጊቱ ያስቆጣቸው የኢራንና የኢራቅ መንግሥታት በየአገሮቻቸው የስዊድን ኤምባሲ ወኪሎችን ጠርተው አነጋግረዋል፡፡
በስዊድን በርካታ የኢራንና የኢራቅ ስደተኞች ይኖራሉ፡፡
ይህን ሙስሊምና ስደተኛ ጠል የሆነውን ቡድን የሚመራው የዴንማርክና ስዊድን ጥምር ዜግነት ያለው ራስመስ ፓሉዳን የሚባል ግለሰብ ነው፡፡
የቡድኑ ስም ስትራም ኩርስ ይባላል፡፡
ራስመስ የቀኝ አክራሪ ሲሆን ጥቁሮች፣ ሙስሊሞችና በአጠቃላይ ስደተኞች ከአካባቢው አገራት ጠቅልለው እንዲወጡ የሚታገል ነው፡፡
ራስመስ ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገረው ቅዱስ ቁርዓንን የማቃጠሉን ተግባር በድጋሚ እንደሚፈጽመው ለደጋፊዎቹ ቃል ገብቷል፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የራስመስን ድርጊት ተከትሎ የተነሳውን ቁጣ ለማብረድ ከተሰማሩ የጸጥታ አስከባሪዎች መካከል 16ቱ ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡
ባለፈው ሐሙስ፣ ዓርብና ቅዳሜ ይህ ቀኝ አክራሪ ቡድን ስቶክሆልም አቅራቢያ ጨምሮ ሊንኮፒንግና ኖርኮፒንግ ላይ ተመሳሳይ ቅዱስ ቁርዓንን የማቃጠል መርሐ ግብር አድርጓል፡፡
ራስመስ ፓሉዳን ድርጊቱን በሌሎች ከተሞችም አስፋፍቶ ለመቀጠልም ዝቷል፡
የስዊድን ብሔራዊ ፖሊስ አለቃ አንደርስ ቶርንበርግ ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት ግጭቶችን የማብረድ ድርጊት ውስጥ ማለፋቸውን ገልጠው ይህ የዘንድሮው ቁጣ ግን ከዚህ ቀደም ከገጠሟቸው ሁሉ ኃያሉ ነው ሲሉ ተናግሯል፡፡
ይህ ስትራም ኩርስ የተሰኘው ቀኝ ዘመም አክራሪ ቡድን ከ2 ዓመታት በፊት በዚያው በስዊድን ቅዱስ ቁርዓንን የማቃጠል መርሐግብር ለማድረግ ማቀዱን ተከትሎ ተመሳሳይ ቁጣ ተቀስቅሶ ነበር፡፡
ይህም የኾነው እንደ አውሮጳዊያኑ በ2020 በስዊድን ሦስተኛዋ ከተማ ማልመ ነበር፡፡
ራስመስ ፓሉዳን በስካንዲኒቪያን የቀኝ አክራሪዎች ዘንድ ስሙ የገነነ ሰው ሲኾን ሙስሊምና ጥቁር ጠል በመሆኑ ይታወቃል፡፡
ዴንማርክ ውስጥ ዘረኛና አስነዋሪ ድርጊት ፈጽመኻል በሚል ለአንድ ወር በእስር አሳልፏል፡፡
ራስመስ ፓሉዳን ይህን ቁርዓን የማቃጠሉን መርሐግብር ፈረንሳይና ቤልጂየምን ጨምሮ በሌሎች የአውሮጳ ከተሞችም ለመድገም ዝቷል፡፡












