በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ ሚኒስትር አቶ በረከት ስምዖን በረሃብ አድማው መቀጠላቸውን ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ

በረከት ስምኦን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አቶ በረከት ስምኦን በረሃብ አድማው መቀጠላቸውን እና የጤንነታቸውም ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ ገለፁ።

የአቶ በረከት ስምኦን ባለቤት፣ ወ/ሮ አሲ ፈንቴ፤ ዛሬ ሰኞ ባህር ዳር ማረሚያ ቤት ሄደው ባለቤታቸውን መመልከታቸውን ገልፀው በረሃብ አድማው መቀጠላቸውን መረዳታቸውን ለቢቢሲ ተናገረዋል።

የማስታወቂያ ሚኒስትርነትን ጨምሮ በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ የቆዩት እና በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙት አቶ በረከት ስምዖን የረሃብ አድማ ላይ መሆናቸው የተሰማው ቅዳሜ ዕለት ነበር።

ባለፉት ሶስት ዓመታት በአማራ ክልል መዲና ባህር ዳር በእስር ላይ የሚገኙት አቶ በረከት ስምዖን ሚያዚያ 7/2014 ዓ.ም. ጀምሮ የረሃብ አድማ ማድረግ የጀመሩት ለወራት ወደ አዲስ አበባ ለመዘዋወር ለማረሚያ ቤቱ ሲያቀርቡት የቆየው ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ እንደሆነም ምንጮቹ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ባለቤታቸው ለቢቢሲ በረሃብ አድማው የተነሳ አቶ በረከት መዳከማቸውን፣ ሁኔታቸው 'አሳሳቢ' መሆኑን ተናግረው አባዛኛውን ጊዜ በእንቅልፍ እንደሚያሳልፉ መረዳታቸውን ገልፀዋል።

የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች እሁድ እለት አቶ በረከትን በስፍራው ተገኝተው እንዳናገሯቸው መረዳታቸውን ባለቤታቸው ገልፀው፤ አቶ በረከት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አለማግኘቱ "የሰብዓዊ መብት ጥሰት፤ የፍትህ መጓደል ነው" ብለው ለኃላፊዎቹ እንዳስረዷቸው እንደነገሯቸው እና እነርሱም ጥያቄያቸውን ሰምተው መልስ ይዘው እንደሚመጡ ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አቶ በረከት ያሉበት ድረስ ባለሙያ መላካቸውን እና ቅሬታቸውን ማዳመጣቸውን ተናግረዋል።

ቤተሰቡ የአቶ በረከት ያሉበት 'የጤና ሁኔታ፣ እድሜ እንዲሁም ሞራል መነካቱ' እና ተያያዝነት ጉዳዩች እንዳሉ ሆነው ምግብ አልመገብም ማለታቸው ተጨማሪ የጤና ቀውስ ያስከትልባቸዋል በሚል እንዳሳሰባቸው ይናገራሉ።

አቶ በረከት ላቀረቡት ጥያቄ አይሆንም ወይንም ይሆናል የሚል አፋጣኝ ምላሽ ማግኘት የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ነው ያሉት ባለቤታቸው፤ ይህ ጉዳይ እጅጉን እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል።

አቶ በረከት ከተፈረደባቸው የስድስት ዓመት እስር ውስጥ አንድ ሶስተኛውን አገባደው በአመክሮ ከእስር ለመውጣት ጥያቄ አቅርበው ነበር።

ወ/ሮ አሲ የልብ ህመም እንዳለባቸው እና በረሃቡ ምክንያት የከፋ አደጋ እንዳይደርስ ቤተሰባቸው ስጋት ውስጥ መውደቁን ጨምረው ለቢቢሲ አስረድተዋል።

"መጀመሪያም የእርሱን ጉዳይ ማየት የነበረበት አዲስ አበባ ያለ ፍርድ ቤት ነበር። አሁን ደግሞ ፍርደኛ ስለሆነ አዲስ አበባ ተዘዋውሮ ለመታሰር ጥያቄ ሲያቀርብ ነበር። እኔም ሆንኩ ልጆቻችን ባህርዳር ተመላልሰን ለመጠየቅ አቅማችን የማይፈቅድበት ደረጃ ደርሰናል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአማራ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ብአዴን ውስጥ በነበራቸው ቁልፍ ሚና የሚታወቁት አቶ በረከት፤ በ2010 ዓ.ም. ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው እስከሚለቁ ድረስ ቢያንስ በስድስት የተለያዩ ዋና ዋና የመንግሥት ኃላፊነቶች አገልግለዋል።

በተለይም በ1997 በተካሄደው ምርጫ በሚደረጉ ክርክሮች ወቅት እና ከምርጫው በኋላ በነበሩ ቀውሶች ወቅት የማዕከላዊ መንግሥቱ ፊት ነበሩ።

ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላም ብአዴን አቶ በረከትን ከፓርቲ አባልነታቸው ያገዳቸው ሲሆን በሙስና ወንጀል ተጠርጥረውም ከሚኖሩበት አዲስ አበባ ተይዘው ወደ አማራ ክልል መወሰዳቸው ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎም አቶ በረከት በአመክሮ ለመፈታት ያቀረቡት ጥያቄ መልስ ያለማግኘቱን ባለቤታቸው ተናግረዋል።

ይህ የአመክሮ መብት የማይሰጠው የዲሲፕሊን ግድፈት ላለበት እስረኛ ብቻ ነው የሚሉት ወ/ሮ አሲ፤ ባለቤታቸው ምንም የዲሲፕሊን ግድፈት ሳይኖርባቸው ሌሎች ዜጎች ያላቸውን መብቶች መከልከላቸው አሳዝኖናል ብለዋል።

ከአቶ በረከት ጋር አብረው ታስረው የቆዩት አቶ ታደሰ ካሳ በከፍተኛ ህመም ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ከመጡ አምስት ወራት መቆጠራቸውን እና አቶ በረከትም አንድ ክፍል ውስጥ ለብቻቸው ታሰረው መቆየታቸው አንዱ ለረሃብ አድማው ምክንያት መሆኑን ባለቤታቸው ተናግረዋል።

"እስካሁን ድረስ ይህ ችግር በክልሉ መንግሥት ይፈታል በሚል፤ አገሪቷም ያለችበት ሁኔታ ስለሚታወቅ በትዕግስት ጠብቀናል። የተለያዩ ደብዳቤዎችን እንዲሁም የቃል ውይይቶችን ብናደርግም ምንም መልስ ስላጣን አሁን መልዕክቱ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እንዲደርስ አድርገናል" ሲሉም የአቶ በረከት ባለቤት አክለዋል።

የአማራ ክልል የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት ኮማንደር አባይነህ በላይ ስለጉዳዩ መረጃ እንደሌላቸው እና አጣርተው መልስ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

አቶ በረከትን በተመለከተ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እንጂ የረሃብ አድማ ማደረጋቸውን ጨምሮ የተለየ መረጃ እንደሌላቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ በጉዳዩ ላይ ቅሬታ እንደደረሳቸው እና ጉዳዩን እንደሚመለከቱት ለቢቢሲ ተናግረዋል።