አሜሪካ እርዳታ ትግራይ መድረሱን እና የትግራይ ኃይሎች ከኤሬብቲ መውጣታቸውን አሞገሰች

የፎቶው ባለመብት, AFP
አሜሪካ ወደ ትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ መድረሱን በበጎ እንደምትቀበለው አስታወቀች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ፣ ከ1,700 ሜትሪክ ቶን በላይ ነፍስ አድን ሰብአዊ እርዳታ ትግራይ መግባቱ መልካም ዜና ነው ብሏል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከንን ባጣቀሰው በዚሁ መግለጫ፣ የትግራይ ኃይሎች ከአፋር ክልል ኤሬብቲ መውጣታቸውን አሜሪካ እንደምትደግፍ ተገልጿል።
በተያያዥም "ከሌሎችም የአፋር አካባቢዎች የትግራይ ኃይሎች ቢወጡ ጠቀሜታው የጎላ ነው" ብሏል መግለጫው።
ህወሓት ሚያዚያ 5/2014 ዓ. ም. በትግራይ የቴሌቭዥን ጣቢያ ባስተላለፈው መግለጫ ሠራዊቱን ከኤሬብቲ ማስወጣቱን መግለጹ ይታወሳል።
ህወሓት ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲደርስ ለማስቻል፣ ተቆጣጥሮት ከነበረው ኤሬብቲ መውጣቱን ነው የገለጸው።
ባሳለፍነው ሳምንት በዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር አማካይነት ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ትግራይ መድረሳቸው ይታወሳል።
የአሜሪካ መንግሥት ትላንት ሚያዝያ 8/2014 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫም "ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ትግራይ መግባታቸውን እንደግፋለን። የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የትግራይ ክልል አስተዳዳሪዎች እና የአፋር ክልል አስተዳዳሪዎች እርዳታው እንዲደርስ ያደረጉትን ትብብርም እናደንቃለን" ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት፣ ሌሎችም ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት አጋሮች "እርዳታ ለሚያሻቸው ሁሉ እንዲያቀርቡ እንጠይቃለን" ብሏል የአሜሪካ መንግሥት።
ለትግራይ፣ ለአፋር እንዲሁም በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች ባጠቃላይ መጠነ ብዙ፣ ቀጣይነት ያለው እንዲሁም ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መኖር እንዳለበት መግለጫው አጽንኦት ይሰጣል።
የኤሌክትሪክ እና የስልክ አቅርቦትን ጨምሮ ባንክና ሌሎችም መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱም በመግለጫው ተጠይቋል።
የኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥት እና ህወሓት ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መስማማታቸው "ለሰላም እና እርቅ መንገድ ይጠርጋል" ሲል መግለጫው ያክላል።
የኢትዮጵያ መንግሥት መጋቢት 15/2014 ዓ. ም. ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑ ይታወሳል። የፌደራል መንግሥቱን ውሳኔ ተከትሎ ህወሓትም በተመሳሳይ ሰብአዊ እርዳታ በተመቻቸ ሁኔታ እንዲደርስ ግጭት የማቆም ውሳኔ ላይ መድረሱ አይዘነጋም።
ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የወጣው መግለጫም "ሁለቱ ወገኖች አሁን በታየው ለውጥ ቀጥለው ግጭቱን በድርድር፣ በዘላቂነት መፍታት የሚችሉበት መንገድ ማግኘት አለባቸው" ይላል።
ይህ እንዲሆንም በትግራይ መሠረታዊ አገልግሎቶች መመለስ እንዳለባቸው እና አካታች ፖለቲካዊ አካሄድ መተግበር እንዳለበት መግለጫው አስምሮበታል።
ሰብአዊ እርዳታ በተመቻቸ ሁኔታ እንዲተላለፍ በሚል በሁለቱ ወገኖች ስምምንት መደረጉት ተከትሎ ባለፈው ሳምንት የዓለም ምግብ ፕሮግራም 47 ምግብ እና ነዳጅን ጨምሮ የተለያየ ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ትግራይ ማድረሱን አስታውቋል።
ይህም ለሰብአዊነት ሲባል ተኩስ አቁም ከተደረገ ወዲህ በዓለም ምግብ ፕሮግራም ወደ ትግራይ የተላከ ሁለተኛ ዙር እርዳታ ነው።
በተመሳሳይ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ምግብና የሕክምና ቁሳቁስን ጨምሮ እርዳታ የጫኑ መኪኖቹ ባለፈው ሳምንት የትግራይ መዲና መቀለ መድረሳቸውን አስታውቋል።
ይህም ለሰብአዊነት ሲባል ተኩስ አቁም ከተደረገ ወዲህ በዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ለትግራይ የተደረገ ሁለተኛ ዙር እርዳታ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት፣ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በሰሜን ኢትዮጵያ ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸውና ከእነዚህ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ ገልጿል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተስፋፋው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ቀውስ አድርሷል።
በኢትዮጵያ መንግሥት እንዲሁም በህወሓት በኩል ለሰብአዊነት በሚል ግጭት ለማቆም መወሰኑን ተከትሎ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች እንዲሁም የተለያዩ አገራት ለሰብአዊ እርዳታ የተሻለ ሁኔታ እንደሚፈጠር ተስፋ እንዳለቸው ገልጸዋል።












