የዓለም ባንክ በጦርነትና በግጭት ለተጎዱ ኢትዮጵያውያን የ300 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማጽደቁን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, World bank
የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ውስጥ በጦርነትና በግጭት ለተጎዱ ከአምስት ሚሊዮን ህዝብ በላይ መርጃና መልሶ ማቋቋሚያ የሚሆን የ300 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መመደቡን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰቱ ጦርነቶች እና ግጭቶች በርካቶችን ቀጥፈዋል፣ ሰብዓዊ ቀውሶችን፣ እንዲሁም የግል እና የህዝብ ተቋሟትን እንዲወድሙ አድርጓል ያለው የዓለም ባንክ ይህ ሁኔታ በርካቶችን ከፍተኛ ድጋፍ እንዲሹ አድርጓቸዋል ብሏል በድረገፁ ባወጣው መግለጫ።
በተጨማሪም በመላው አገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች እንዲፈናቀሉና ወሲባዊ ጥቃቶች እንዲባባሱ ምክንያት እንደሆነም ጠቅሶ በጦርነቱ ምከንያት በሴቶች እና ታዳጊዎች ላይ አካላዊና ወሲባዊ ጥቃቶች መፈጸማቸው በስፋት ሪፖርት መደረጉን አስታውሷል።
ይህ ድጋፍ የዓለም አቀፍ ልማት ማህበር (International Development Association) በሚል ማዕቀፍ ሲሆን በግጭት ለተጎዱ ማህበረሰቦች ድጋፍና መልሶ መቋቋሚያ የሚውል ፕሮጀክት ነው።
ፕሮጀክቱ የማህበረሰቡን አፋጣኝ ፍላጎቶች መቅረፍ፣ በግጭት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ማቋቋምና ማህበረሰቡ በጦርነቱ እንዳይጎዳ በዘላቂነት ለማቋቋም የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚደግፍም ከዓለም ባንክ ድረ-ገፅ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
በተለይም ፕሮጀክቱ በማህበረሰቡ ቅድሚያ የሚያስፈልጋቸውን መሰረታዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግና የአየር ንብረት ለውጥን ተጽዕኖ መቋቋም የሚችሉ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ይገነባል ብሏል።
በጦርነቱ የተጎዱ ማህበረሰቦችን ፍላጎት በአስቸኳይ ለሟሟላት በትምህርት፣ በጤና፣ በውሃ እና በንጽህና ዙሪያ ያሉ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማቅረብ ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ሰጪ ግንባታ እንደሚከናወንም ጠቁሟል።
ዓለም ባንክ በተጨማሪም እንዳለው በጦርነቱ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው አካላት ከደረሰባቸው አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳቶች እንዲያገግሙ የተሻለ አገልግሎት እና አጠቃላይ እንክብካቤ እንዲያገኙ ይደረጋል።
"ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት የደረሰባቸው ግለሰቦች በአካላዊ እና በአእምሯዊ ጤንነታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ይደርስባቸዋል። ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከደረሰባቸው ጉዳት ለማገገም የሚያስችላቸውን ድጋፍ ማግኘት አልቻሉም። ይህ ፕሮጀክት ግጭት በተከሰተባቸው ክልሎች ወሲባዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ነዋሪዎች የጤና፣ የስነ-ልቦና-ማህበራዊ ድጋፍ እና የህግ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል" ሲሉ የኤርትራ፣ የኢትዮጵያ፣ የደቡብ ሱዳን እና የሱዳን የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ኦስማን ዳዮኔ ተናግረዋል። .
ፕሮጀክቱ ብሄራዊ ቢሆንም በመጀመሪያ ቅድሚያ የሚሰጠው በቅርቡ በተከሰተው ግጭት ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸውና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮችን ላስተናገዱት የአፋር፣ የአማራ፣ የቤኒሻንጉል-ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች ይሆናል።
ከአካባቢያዊ ሁኔታዎች ጋር የተጣጣመ ፈጣን እና ቀልጣፋ ድጋፍን ለማረጋገጥ ፕሮጀክቱ በፌዴራል፣ በክልል እና በማህበረሰብ አቀፍ ድርጅቶች እንደሚተገበር የተጠቀሰ ሲሆን በተጨማሪም ጦርነት እየተካሄደ ባለባቸው አካባቢዎች በገለልተኛ የሶስተኛ ወገን ተግባራዊ ይሆናል።
በአውሮፓውያኑ 1960 የተቋቋመው የአለም ባንክ አለም አቀፍ ልማት ማህበር (አይዲኤ) ድሃ በሆኑ ሃገራት ኢኮኖሚያቸውን የሚያሻሽል፣ ድህነትን የሚቀንስና የማህበረሰቡን ህይወት ለሚያሻሽሉ ፕሮጀክቶች በአነስተኛ ወለድ ድጋፍ የሚያደርግ ነው ሲል የዓለም ባንክ በድረገፁ አስቀምጧል።
የልማት ማህበሩ በአለም ላይ ላሉ ለ74 ድሃ ሃገራት ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን ከነዚህም 39ኙ በአፍሪካ እንደሚገኙ ከዓለም ባንክ ድረ-ገፅ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።












