የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን 737 ማክስ አውሮፕላኖች ላይ ጥሎት የነበረውን የበረራ እገዳ አነሳ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኢትዮጵያ ሲቪል ኦቪዬሽን ባለስልጣን በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች በኢትዮጵያ የአየር ክልል እንዳይበሩ ጥሎት የነበረውን እግድ ማንሳቱን አስታወቀ።
ሲቪል አቪዬሽኑ በትላንትናው እለት ባወጣው መግለጫ ከሦስት አመት በፊት በደረሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ምከንያት ለረጅም ጊዜ እገዳ ተጥሎባቸው የቆዩት ቦይንግ ሰራሹ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከሚያዝያ 3፣ 2014 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ አየር ክልል መብረር ይችላሉ ብሏል።
ሲቪል አቪዬሽኑ ይህንን ይበል እንጂ በያዝነው ዓመት ጥር ወር መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አግዶት የነበረውን ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ወደ አገልግሎት መመለሱን አስታውቆ ነበር።
የወቅቱ የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም አየር መንገዱ አውሮፕላኑን ወደ በረራ አገልግሎት ለመመለስ ከውሳኔ ላይ የደረሰው በዓለም ዙሪያ ባሉ የበረራ ደኅንነት ተቆጣጣሪ አካላት የአውሮፕላኖቹን ስሪትና የማሻሻያ ስራዎች ከ20 ወራት በላይ በሚሆን ጊዜ ተፈትሾ በተደጋጋመ ክትትልና ቁጥጥር ማረጋገጫ ማግኘቱን ተከትሎ ነው ብለው ነበር።
በተጨማሪም አስተማማኝነቱና ደህንነቱ በአብራሪዎቻችን፣ በኢንጂነሮችና በበረራ ቴክኒሻኖቻችን በሙሉ ተረጋግጧል ብለዋል።
በወቅቱም ከበራራ መስመሮች ታግዶ የቆየው አውሮፕላን በአፍሪካ ትልቁ ተራራ ወደሆነው የከሊማንጃሮ ተራራ አድርጎ በመብረር ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ የናሙና በራራም ማቀዱ ተገልጾ ነበር።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር ኢቲ-302 ቦይንግ 737 ማክስ ይጓዙ የነበሩ 157 መንገደኞችና የበረራ ሰራተኞች ህልፈት ምክንያት በመሆኑ ነበር አውሮፕላኑ እገዳ የተጣለበት።
መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም የደረሰውን አደጋ ተከትሎም የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ስሪቶች ተለዋጭ መመሪያ እስካልወጣ ድረስ በኢትዮጵያ አየር ክልል እንዳይበር ባለስልጣኑ እገዳ ጥሎ ነበር።
ሆኖም በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ ፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር ለአደጋው መንስኤ የሆኑ ችግሮችን በመለየት አደጋውን ሊቀርፍ የሚያስችል አስገዳጅ መመሪያ በማውጣት መመሪያዎቹ ተግባራዊ እንደሆኑ ወደ በረራ መመለስ እንደሚችሉ መግለጹን ተከትሎ እገዳው ተነስቷል ብሏል ባለስልጣኑ።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በአውሮፕላኖቹ ላይ የተደረገውን የዲዛይን ማሻሻያ እና የአየር መንገዱን የበረራ መመሪያዎች እና ስልጠናዎች በተገቢው ሁኔታ መፈተሹን አስታውቋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድም መመሪያዎቹን ተግባራዊ ማድረጉንም ካረጋገጠ በኋላ እገዳውን ማንሳቱን አክሎ ገልጿል።
ቦይንግ በያዝነው ዓመት ኅዳር ወር ላይ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ተጎጂ ቤተሰቦች ጋር ስምምነት ላይ መድረሱ ተገልጿል።
በዚህም ስምምነት መሰረት የአሜሪካው አውሮፕላን አምራች ቦይንግ በአደጋው ለሞቱት ሰዎች ኃላፊነቱን እንደሚወስድና ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ የሚሆን ሲሆን በምላሹም የተጎጂ ቤተሰቦች ኩባንያው ላደረሰው ጉዳት በፍርድ ቤት ቅጣት እንዲጣልበት አይጠይቁም።
ስምምነቱ ከአሜሪካ ውጪ ያሉ እንደ ኢትዮጵያ እና ኬንያ ባሉ አገራት ያሉ የተጎጂ ቤተሰቦች በአገራቸው ሳይሆን በአሜሪካ ፍርድ ቤቶች ካሳ እንዲከፈላቸው መንገድ መክፈቱም ተገልጿል።
ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በኢንዶኔዥያው አደጋ 189 መንገደኞችና የበረራ ሰራተኞች መሞታቸው ይታወሳል።
በ737 ማክስ አውሮፕላን ላይ የደረሱ ሁለት አደጋዎችን ተከትሎ ቦይንግ የአብራሪዎቹን አቅም ጥያቄ በማስገባትና ጥፋቱን ወደ ሌሎች አካላት በማዛወር ትችት ሲቀርብበት ነበር።
ነገር ግን በዚህ ዓመት ኃላፊነቱን መውሰድና ተጠያቂነቱን መቀበሉ ትልቅ ምዕራፍ እንደሆነም ተጠቅሷል።
አደጋው በደረሰበት ወቅት 737 ማክስ አውሮፕላን በቦይንግ ከፍተኛ ሽያጭ የነበረው ምርት ነበር።
ነገር ግን በአምስት ወራት ውስጥ ለበርካታ ሰዎች እልቂት የሆኑ ሁለት አደጋዎች ደረሱ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ናይሮቢ የሚያደርገውን ጉዞ ከጀመረ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ነበር አደጋው የደረሰው።
ከዚያም ቀደም ብሎ የኢንዶኔዥያው ላየን ኤይር ጄት በኢንዶኔዥያ ባሕር ላይ መከስከሱ በአውሮፕላኖቹ ላይ ከባድ ችግሮች እንዳሉ አሳይቷል።
አደጋዎቹን ተከትሎ በአውሮፕላኖቹ ላይ ምርመራ እየተከናወነ በነበረበት ወቅት ለ20 ወራት አገልግሎት እንዳይሰጡ ተደርጎ የቆየ ሲሆን ኩባንያው በሶፍትዌሩ እና በስልጠናዎች ላይ ከፍተኛ ለውጥ ካደረገ በኋላ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ተፈቅዶላቸዋል።












