አትሌት ሰለሞን ባረጋ ቃል የተገባለት መኪና እና መሬት እስካሁን ለምን አልተሰጠውም?

የፎቶው ባለመብት, Jean Catuffe
አትሌት ሰለሞን ባረጋ ከወራት በፊት ታላቁ ቤተ-መንግሥት በተካሄደ ስነ-ስርዓት መኪና በሽልማት መልክ እንደተበረከተለት ቢገለጽም መኪናው እስካሁን ድረስ እጁ አልደረሰም።
በ32ኛ የቶኪዮ ኦሎምፒክ በ10ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘው አትሌት ሰለሞን 3 ሚሊዮን ብር ያወጣል የተባለው መኪና ከፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ እጅ እንደተበረከተለት ቢገለጽም ከ7 ወራት በኋላ ሽልማቱ ከአትሌቱ እጅ አልደረሰም።
አትሌት ሰለሞን ባረጋ የቀድሞ የፌደራል ስፖርት ፌዴሬሽን የአሁኑ የስፖርት እና ባህል ሚኒስቴር ትብብር ባይነፈገውም በውጭ ምንዛሬ ችግር ምክንያት መኪናው እስካሁን እጁ እንዳልገባ ለቢቢሲ ተናግሯል።
"ሚኒስትሮች ተቀያይረዋል። አዲስ የመጡ ሰዎች ናቸው። እኔም 'የት ደረሰ' እያልኩ አልጠየቅኩም። ሞኤንኮ ያስገባል ተብሎ ነበር። ይመስለኛል ኩባንያው መኪናውን ለማስገባት የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሬ ማግኘት አልቻለም። እንዳደውም በጣም እየተባበሩኝ እኔ በምፈልግበት ሁኔታ እየሄዱ ነው ያሉት" በማለት አትሌት ሰለሞን ሁኔታውን አብራርቷል።
በባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ ለአትሌቱ ቃል የተገባለት ስጦታ በውጭ ምንዛሬ እጥረት እስካሁን እንዳልተሰጠው ተናግረዋል።
አትሌቱ ላስገኘው ድል የሚመጥን ስጦት ለመስጠት ከውሳኔ ከተደረሰ በኋላ፤ "የተመረጠው መኪና አገር ውስጥ ስለሌለ በጀቱ ተይዞ እንደሚቀርብ ተወስኖ ነው ፕሮግራሙ የተካሄደው" ብለዋል አምባሳደር መስፍን።
ልጁ አሸንፎ ይገባል የሚል ዝግጅት አልነበረም። ግን አሸንፎ አገር ቤት እንደገባ የአገርን ክብር የሚመጥን ሽልማት ሊደረግለት ይገባ ነበር።
ስለዚህ የተፈለገውን መኪና ሞዴል ተመርጦ ዝግጅቱ ተካሄደ። ሞኤንኮ 'አሁን እጄ ላይ መኪና የለም ከውጭ አስመጣለሁ' አለን።
በሸልማት ስነ-ስርዓቱ በፎቶ የታየው መኪና ቃል የተገባው እንጂ የተሰጠው አይደለም" ሲሉ ሚኒስትር ዲኤታው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Office of the President, Ethiopia
ነሐሴ 27/2013 ዓ.ም. በታላቁ ቤተመንግሥት የተዘጋጀውን የሽልማት ስነ-ስርዓቱን ያሰናዳው የፌደራል ስፖርት ኮሚሽን ስለመሆኑ መንግሥታዊ የሆኑ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በወቅቱ ዘግበው ነበር።
በዚህ ስነ-ስርዓት ላይ በቶኪዮ ኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ ላመጣው አትሌት 1.5 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የነሐስ ሜዳሊያ ላስገኙት አትሌቶች ደግሞ የ1 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ሽልማት ለመስጠት ቃል ተገብቶ ነበር።
በቶኪዮ ኦሎምፒክ በ3ሺህ ሜትር መሰናክል የብር ሜዳሊያ ያስገኘው አትሌት ለሜቻ ግርማ ቃል የተገባለት የገንዘብ ሽልማት እንደተፈጸመ ለቢቢሲ ተናግሯል።
በተጨማሪም በ10ሺህ እና 5ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ያስገኙት አትሌት ለተሰንበት ግደይ እና ጉዳፍ ጸጋይ እያንዳንዳቸው ቃል የተገባላቸውን የ1 ሚሊዮን ብር ሽልማት መቀበላቸውን ቢቢሲ ለአትሌቶቹ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች ማረጋገጥ ችሏል።
አትሌት ሰለሞን ባረጋ ቃል የተገባለት የመኪና ሽልማት እስካሁን እጁ ባይደርስም በሁኔታው ቅር አለመሰኘቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።
"አገሪቱ ካለችበት ሁኔታ ጋር ተያይዞ የውጭ ምንዛሬ ስለሌለ እንጂ ሌላ ነገር ተፈጥሮ አይደለም። ይሄ ትንሽ ዘገየ እንጂ ከእኔ በፊት የነበሩ አትሌቶች እንደዚሁ ነው። ይዘገያል። ቆይቶ ነው የተሰጣቸው" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
"በጣም ነው እየተባበሩኝ ያሉት። እየተከታተሉ ነው። ዝም ብለው ነው ፌስቡክ ላይ የሚያወሩት። እኔ ያስገባሁት ቅሬታም የለም። ሲጀመር በዚህ ሰዓት አገራዊ ነገሮች ባልተስተካከሉበት ሰዓት መኪና አልተሰጠኝም የምልበት ጊዜ አይደለም" ብሏል

የፎቶው ባለመብት, Office of the President, Ethiopia
አትሌት ሰለሞን በሽልማት መልክ ሊሰጠው የነበረው መኪና ዋጋ በብር ተሰጥቶት፤ እርሱ በራሱ የውጭ ምንዛሬ የፈቀደውን መኪና ከቀረጥ ነጻ ለማስገባት ከስፖርት እና ባህል ሚኒስቴር ጋር ከተነጋገረ በኋላ ሚኒስቴሩ ትብብር እያደረገለት መሆኑን ለቢቢሲ አስረድቷል።
"ከቀረጥ ነጻ እንዳስገባ ስፖርት ሚኒስቴር የጻፈው ደብዳቤ አሁን ገንዘብ ሚኒስቴር" ይገኛል ብሏል አትሌት ሰለሞን ባረጋ።
በተመሳሳይ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በአትሌት ሰለሞን ጥያቄ መሠረት የመኪና ግዢ የሚፈጸምበት ገንዘብ ገቢ ተደርጎለት በራሱ የውጭ ምንዛሬ ከቀረጥ ነጻ መኪና እንዲያስገባ ደብዳቤ ለገንዘብ ሚኒስቴር ልኮ ጉዳዩ እንዲፈጸምለት እየተከታተልን ነው ሲሉ ለቢቢሲ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የወልቂጤ 10ሺህ ካሬ ሜትር
አትሌት ሰለሞን ከቶኪዮ ኦሎምፒክ ድሉ በኋላ ከመኪናው በተጨማሪ በወልቂጤ ከተማ 10 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት እንደሚሰጠው ሐዋሳ ከተማ ላይ በተደረገ ስነ-ስርዓት ተገልጾለት ነበር።
ይኹን እንጂ ይሄም ሽልማት በተመሳሳይ ከአትሌቱ እጅ አልደረሰም።
"ወልቂጤ ዞን ላይ ነው። 10ሺህ ካሬ ሜትር ነው። እነሱም ቦታ በማፈላለግ ላይ ናቸው። በስልክ እየተነጋገርኩ ነው። ጥሩ ቦታ እየመረጡ ነው ያሉት። 'ስናስጨርስ እንደውልልሃለን' ብለውኛል ስልክ እየጠበቀኩ ነው" በማለት አትሌት ሰለሞን ያለውን ሁኔታ ለቢቢሲ አስረድቷል።
በጉዳዩ ላይ የኢትዯጵያ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት አስተያየትን ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።












