ሳዲዮ ማኔ በስሙ ስታድዮም ሊገነባለት ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሃገሩ ሴኔጋልን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት ያደረገው ሳዲዮ ማኔ በደቡብ ምዕራቧ ከተማ ሴዲዮ ስታዲዬም ሊገነባለት ነው።
የሊቨርፑሉ አጥቂ ማኔ የቴራንጋ አናብስት ግብፅን በፍፁም ቅጣት ምት አራት ለሁለት ሲረቱ የማሸነፊያዋን ጎል ማስቆጠሩ ይታወሳል።
ማኔ በአፍሪካ ዋንጫ ሶስት ጎሎችን ሲያስቆጥር ሁለት ኳሶችን ለጎል አመቻችቶ አቀብሏል። በዚህም የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ተብሏል።
የሴዲዮ ከንቲባ አድቡላዬ ዲዮፕ የክልሉ ስታድዮም የሚሰየመው በሳዲዮ ማኔ ነው ብለዋል።
የከተማዋ ከንቲባና የሴኔጋል ባህልና ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር የሆኑት ዲዮፕ "በደቡብ ምዕራብ የሚገነባው ስታድዮ ደ ሴዲዮ ስፍራው ባፈራው ተወዳጅ ልጅ ይሰየማል" ሲሉ አውጀዋል።
ማኔ የብዙዎችን ልብ ማሸነፍ የቻለው የአፍሪካ ዋንጫ ከማንሳቱ በፊት ነው።
ባደገበት አካባቢ ሆስፒታልና ትምህርት ቤት ለመገንባት ገንዘብ አሰባስቧል። መስጅድ እንዲገነባ አስተዋፅዖ አድርጓል። አልፎም ኮቪድን ለመከላከል የገንዘብ እርዳታ ለግሷል።
በፈረንጆቹ 2018 የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ከመካሄዱ በፊት ባደገበት ባምባሊ ከተማ ላሉ ደጋፈዎች የሊቨርፑልን ማሊያ መስጠቱም የሚታወስ ነው።
"በመንደሩ 2 ሺህ ሰዎች ይኖራሉ። 300 የሊቨርፑል ማሊያዎችን ገዝቼ በሰው ላኩኝ። ጨዋታውን ሲመለከቱ እንዲለብሱት በማለት ነው" ብሎ ነበር ማኔ በአንድ ወቅት።
ባምባሊ ማለት ማኔ የ13 ዓመት ታዳጊ እያለ አሁን የሚጫወትበት ሊቨርፑል ኤሲ ሚላንን በመርታት የ2005 አውሮፓ ቻምፒዬንስ ሊግን ሲያነሳ የተመለከተባት አነስተኛ ከተማ ናት።
ማኔ አሁን የደረሰበት ለመድረስ ብዙ ርቀት ተጉዟል።
ከሴኔጋል ፈረንሳይ በመሄድ ለሜትዝ ተጫውቷል፤ ከዚያም ለኦስትሪያው አርቢ ሳልዝበርግ፤ ቀጥሎ ወደ እንግሊዙ ሳውዝሃምፕተን፤ አሁን ደግሞ ለሊቨርፑል።
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን አንስቷል። የአውሮፓ ቻምፒዬንስ ሊግንም እንዲሁ። አሁን ደግሞ ሃገሩ ሴኔጋል ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ እንድታነሳ ማድረግ ችሏል።
ሴኔጋል በካሜሩን የተዘጋጀውን የአፍሪካ ዋንጫ ካነሳች በኋላ ማኔ እንዲህ ሲል ተደምጧል፡ "ይህ የሕይወቴ ትልቁ ምዕራፍ ነው።"












