የአለም ጤና ድርጅት ወደ ትግራይ መድኃኒትና የህክምና ቁሳቁሶች በአየር ማጓጓዝ መጀመሩን ገለጸ

መድኃኒት ወደ ትግራይ ሲገባ

የፎቶው ባለመብት, WHO ETHIOPIA TWITTER PAGE

የአለም ጤና ድርጅት አስፈላጊ የሚባሉ መድኃኒቶች፣ የህክምና ግብዓቶችንና ቁሳቁሶችን በዛሬው ዕለት የካቲት 4፣ 2014 ዓ.ም ወደ ትግራይ መዲና መቀለ በአየር ማስገባቱን አስታውቋል።

የአለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ በዛሬው ዕለት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ 33.5 ሜትሪክ ቶን መድኃኒቶችንና የህክምና ግብዓቶችን በአየር በማጓጓዝ ወደ ክልሉ ለማስገባት እቅድ መያዙን አስፍሯል።

በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ አየር አገልግሎት በሁለት በረራዎች አማካኝነት የመጀመሪያው በየቀኑ እንዲደርስ የታሰበው 10 ሜትሪክ ቶን በዛሬው ዕለት መድረሱን ቢሮው አክሎ ገልጿል።

በተከታታይም በሚደረጉ በረራዎች መድኃኒቶቹና የህክምና ግብዓቶቹ በሚቀጥሉት ቀናት ይደርሳሉ ብሏል።

በትግራይ ከአምስት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ህይወት አድን የህክምና መገልገያዎችን ማድረሱን ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ከሁለት ሳምንት በፊት ገልጾ ነበር።

አለም አቀፉ ቀይ መስቀል መድኃኒቶችንና የህክምና መገልገያዎችን ወደ ክልሉ ማድረስ የቻለው በአየር ሲሆን ተጨማሪ በረራዎች እንደሚኖሩም መግለፁ ይታወሳል።

በወቅቱ ወደ ትግራይ በተለያዩ በረራዎች የገቡት ህይወት አድን መድኃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶች ኢንሱሊን፣ ሄሞዳያሊስስ፣ ኦክሲቶሲን፣ ቴታነስ፣ ቶክሶይድ፣ ጓንቶች እና የቀዶ ህክምና ቁሳቁሶች መሆናቸውም ተገልጿል።

ባለፈው ሳምንት በአንድ አለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አማካኝነት ከ14 ሜትሪክ ቶን በላይ መድኃኒቶች በአየር መግባቱን የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) በዛሬው እለት የካቲት 4፣ 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ያስታወቀ ሲሆን

ይህ የነፍስ አድን እርዳታ እንደ በጎ ቢያየውም ከሚፈለገውም በጣም ያነሰ ነው ብሏል።

ከዚህ ቀደም የዓለም ጤና ድርጅት በጦርነት ክፉኛ በተጎዳችው ትግራይ ክልል ካለፈው ዓመት ሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ የህክምና ቁሳሶቁሶችን ለማድረስ ፍቃድ አለማግኘቱን አስታውቆ ነበር።

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ድርጅታቸው በትግራይ ክልል የህክምና ቁሳቁሶች ለማቅረብ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ሊፈቀድለት እንዳልቻለ መግለፃቸው ይታወሳል።

ሆኖም በጦርነቱ ለተጎዱት ለአማራ ክልል 70 ሜትሪክ ቶን እንዲሁም ለአፋር 14 ሜትሪክ ቶን የህክምና ቁሳቁሶችን ማድረስ መቻሉም ተገልጿል።

የድርጅታቸው እንቅስቃሴዎች የከፉ ጦርነቶች ባሉባቸው እንደነ ሶሪያና የመን እንኳ ባልተገታበት ሁኔታ በኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ባልታየ ሁኔታ እግድ እንደሚጣልባቸው አውስተዋል።

በትግራይ ክልል የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች ህፃናትን ጨምሮ ህሙማን በከፍተኛ መድኃኒት እጥረት ምክንት እየሞቱ መሆናቸውን ባወጡት መግለጫ እንዲሁም ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት ከተጣለው እገዳ ጋር ተያይዞ መድኃኒት እና ሌሎች የህይወት አድን ቁሳቁሶች ወደ ሆስፒታሎች ባለመድረሳቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉ መንግሥት ምንም አይነት እገዳ እንዳልጣለና በአሁኑ ወቅት ለተፈጠረው ችግር ህወሓትን ተጠያቂ አድርገው ነበር።

በክልሉ መዲና መቀለ በሚገኘው ትልቁ የጤና ተቋም የሚገኙ ዶክተሮች እንደተናገሩት በቀዶ ህክምና ወቅት የሚያስፈልጉ በደም ስር የሚሰጡ (intravenous fluids) እና የሰመመን መስጫ መድኃኒቶች ባለመኖራቸው ቀዶ ህክምና ማድረግ አለመቻላቸውን ነው።

የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ሠራተኞች ባወጡት መግለጫ በተደጋጋሚ የሚከሰተው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እና ያልተሟላ የኦክስጂን አቅርቦት ለታካሚዎች ሞት ምክንያት ነው ብለዋል።

በተያያዘ ዜና በአፋር ክልል የቀጠለው ጦርነት ወደ ትግራይ እርዳታ እንዳይደርስ እክል መፍጠሩን የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) በዛሬው ባወጣው መግለጫው አስታውቋል።

የቀጠለው ጦርነት በአፋር መጠነ ሰፊ መፈናቀል እና ሰብዓዊ እርዳታዎችን ፍላጎት ጨምሯል ብሏል።

በትግራይ ከአምስት ሚሊዮን ህዝብ በላይ ምግብና ሌሎች መሰረታዊ ዕርዳታዎች ቢያስፈልገውም ወደ ትግራም በመኪና የሚደረገው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች መቋረጡንም ኦቻ ጠቁሟል።

በአጠቃላይ በክልሉ ያለው የሰብዓዊ እርዳታ ተቋርጧል ወይም በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል ያለው ኦቻ ለዚህም እንደ ምክንያትነት የጠቀሰው የነዳጅ፣ ገንዘብና እርዳታ እጥረትን ነው።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው በትግራይ ክልል ውስጥ 40 በመቶ የሚጠጉ ሰዎች በአስከፊ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆናቸውን ገልጿል።

ከአስራ አምስት ወራት በላይ ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ ኬንያና ሌሎች አገሮች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ አመራሮች መካከል ያለው ውይይት መቀጠሉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ ከሰሞኑ አስታውቀዋል።

ምክትል ዋና ፀሐፊዋ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "በአሁኑ ወቅት በእርግጠኛነት የተሻለ ቦታ ላይ ነን። ተጨማሪ ውይይቶችም አሉ" በማለት አስረድተዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፋላሚ ወገኖች በቅርቡ ለሰላም ያሳዩትን እርምጃ በበጎ እንደሚያዩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከቀናት በፊትም መግለጻቸው ይታወሳል።

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከዚህ ቀደምም ጦርነቱን ለማብቃትና ሰላም ለማውረድ የሚያስችል የሚታይ ጥረት እየተደረገ መሆኑ እንዳስደሰታቸው መግለጻቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል (ኤፒ) መዘገቡ ይታወሳል

የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መሪ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በህወሓትና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር እየተደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ይህ እየተደረገ ያለው ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት የተወሰነ ውጤት እያሳየ መሆኑንና የመሻሻል ምልክቶች እንዳሉ አመልክተው ነበር።

እየተካሄደ ነው ስለተባለው ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይትን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም።