የሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ ኢትዮጵያ ላይ ምን አንድምታ ይኖረው ይሆን?

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን ያሳወቁት እሁድ ምሽት ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን መልቀቂያ የተሰማው በአገሪቱ ውስጥ ለተከታታይ ሳምንታት ሲካሄድ በቆየውና እሁድ ዕለት ካርቱም ውስጥ የተደረገውን ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ ነበር።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን መልቀቅ ከአብደላ ሐምዶክ ጋር ስምምነት መስርተው ለነበሩት ወታደራዊ መሪዎች ራስ ምታት ነው ሲሉ የአገሪቱን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ይናገራሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ ከሥልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ ወታደራዊ ኃይሉ ሥልጣኑን ሊጠቀልል፣ አገሪቱም ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመሸገገር የምታደርገውንም ጥረት ሊያኮላሽ ይችላል።
ይህ ብቻ ሳይሆን አሁን በአገሪቱ ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ፣ ወታደራዊ ኃይሉን ወደ አምባገነናዊ አስተዳደር ሊመራው የሚችልበት እድል ሰፊ ነው።
አብደላ ሐምዶክ
አብደላ ሐምዶክ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ቃለ መሐላ ፈጽመው ሥልጣን ሲረከቡ ዋነኛ ግባቸው የነበረው አገሪቱን ማረጋጋትና ለገጠማት ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ መፍትሄ መፈለግ ሲሆን በዚያውም በሕዝብ የሚመረጥ መንግሥት ለመመስረት መንገድ ማመቻቸት ይገኝበታል።
የአብደላ ሐምዶክ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ለረጅም ዘመን ከወታደሩ በወጡ መኮንኖች ስትመራ የነበረችውን ሱዳንን፣ ከጦር ኃይሉ ተጽዕኖ በማላቀቅ ወደ ሲቪል መንግሥት ይመልሳታል የሚል ተስፋን በሕዝቡ ውስጥ ፈጥሮ ቆይቷል።
በ60ዎቹ አጋማሽ የሚገኙት አብደላ ሐምዶክ በምጣኔ ሀብት የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአፍሪካ አህጉራዊ ተቋማት ውስጥ በሙያቸው የረጅም ጊዜ ልምድ አላቸው።
አገራቸው በወሳኙ የሽግግር ወቅት እንዲያገለግሏት ስትጠራቸው አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ እያገለገሉ ነበር።
ቀደም ሲል ፕሬዝዳንት አልበሽር መሪ በነበሩበት ወቅት፣ ሐምዶክ ለገንዘብ ሚኒስትርነት ታጭተው የነበረ ሲሆን እርሳቸው ግን ሳይቀበሉት መቅረታቸው ይነገራል።
በሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የነበረው አለመግባባት ረግቦ የሽግግር መንግሥት ለመመስረት ከስምምነት የተደረሰ ቢሆንም፣ በጦር ኃይሉና በሲቪል ባለሥልጣናት መካከል የነበረው ግንኙነት የሰመረ አልነበረም። ይህ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲዋቀር በሚፈልጉ ለውጥ ጠያቂዎች ዘንድ ጥርጣሬን ፈጥሮ ቆይቷል።
በተለይ የጦር ኃይሉ ጄነራሎች ጎልተው መውጣት አገሪቱን መልሶ ወደ ወታደራዊ አስተዳደር አዙሪት ውስጥ ሊከታት ይችላል የሚል የዘወትር ስጋት ነበረ።
የኢትዮጵያ ሚና
ፕሬዝዳንት አልበሽር ከሥልጣን ተወግደው በሱዳን ፖለቲካዊ ኃይሎች መካከል አለመግባባቱ በጦዘበት ጊዜ፣ ጦር ኃይሉና ሲቪል ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ከስምምነት ደርሰው የተሳካ የሽግግር ሂደት እንዲኖር የኢትዮጵያ ሚና የጎላ እንደነበር ይታወሳል።
በሕዝባዊው ተቃውሞ ወቅት በተገደሉ ሰዎች ምክንያት የተቃዋሚ መሪዎች የጦር ኃይሉን መሪዎች ተጠያቂ በማድረግ በሽግግር መንግሥቱ ውስጥ እንዳይሳተፉ ሲጠይቁና ጄነራሎቹም የአገሪቱን ደኅንነት ለማስጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ እንደወስዱበት በሚናገሩበት ጊዜ ሌላ ዙር ደም መፋሰስ እንዳይከሰት ተሰግቶ ነበር።
በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ካርቱም በማምራት ሁለቱ ወገኖች ልዩነታቸውን አጥብበው ሱዳን ወደ ተረጋጋ የሽግግር ሂደት እንድታመራ ጥረት አድርገዋል። በዚህም በተቀናቃኞቹ ኃይሎች መካከል ስምምነት ተደርሶ አሳሳቢው ውጥረት ለጊዜውም ቢሆን ለመርገብ ችሎ ነበር።
ከኢትዮጵያ ጋር ረዥም ድንበር የምትጋራው ሱዳን በአል በሽር ትመራ በነረበት ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መምጣት በፊት ከነበረው አስተዳደር ጋር ጠንካራ ግንኙነት ገንብታ የቆየች ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የአመራር ለውጥ ከመጣ በኋላም ይህንኑ ለማስቀጠል ፍላጎት እንዳለ ታይቷል።
በተለይ አልበሽር ከሥልጣን ወርደው የሽግግር መንግሥት በሚቋቋምበት ጊዜ ለሱዳን መረጋጋት ኢትዮጵያ ያላትን ድጋፍ ለማሳየት ጥረት አድረጋለች። በተመሳሳይም ሱዳንን ከጎኗ ለማሰለፍ የምትፈልገው ግብፅም የበኩሏን ስታደርግ መቆየቷ ይታወሳል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ውጥረት የነገሰበት የድንበር ጉዳይ
ኢትዮጵያና ሱዳን ለረጅም ጊዜ መፍትሔ ሳያገኝ የቆየውን የድንበር ጥያቄያቸውን ለመፍታት ዓመታት የቆየ የድንበር ኮሚሽን አዋቅረው አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ቢያደርጉም የመጨረሻ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች የሚገኙበትና ሱዳን ይገባኛል የምትለው አል ፋሽቃ የተባለው ሰፊ ለም መሬት፣ አንድ ጊዜ አጀንዳ ሲሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲተው ቆይቶ ነበር። ሁለቱም አገራት የራሳቸው እንደሆነ ቢገልጹም ግንኙነታቸውን ከሚያበላሽ ደረጃ ላይ ሳይደርስ ለአመታት ቆይቷል።
ነገር ግን ትግራይ ውስጥ ጦርነት በተቀሰቀሰበት ጊዜ የኢትዮጵያ ወታደሮች የድንበር አካባቢውን ለቅቀው መውጣታቸውን ተከትሎ የሱዳን ሠራዊት በኃይል ቦታውን መቆጣጠሩ በኢትዮጵያ በኩል ቁጣን አጭሯል። በውስጣዊ አለመረጋጋር ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ ወረራ ያለችውን ድርጊት ለመከላከል እርምጃ ሳትወስድ ቆይታለች።
የሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በይፋ ወጥተው በኢትዮጵያ የተያዘባቸውን መሬት ማስመለሳቸውን ሲገልጹ፣ በኢትዮጵያ በኩል ግን ለችግሩ በውይይት መፍትሔ እንዲፈለግ በተደጋጋሚ እየጠየቀች ነው። በዚህም ሳቢያ በሁለቱ መንግሥታት መካከል የነበረው መተማመን ከዚህ በፊት በነበረው ደረጃ ላይ እንዳይገኝ ሆኗል።
ከዚህ በተጨማሪ በሕዳሴው ግድብ ግንባታና የውሃ አሞላል ሂደትን በተመለከተ ለዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራራቢ አቋም የነበራት ሱዳን ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ለውጦችን አሳይታለች።
ግድቡን በተመለከተ ከመጀመሪያው አንስቶ ተቃውሞ የነበራት ግብፅ የምታነሳቸው ሐሳቦችን በመደገፍ ወይንም ከዚህ በፊት ስምምነት በተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎችን በማንሳት ሱዳን ጫና ለመፍጠር ሙከራ ስታደርግ ተስተውሏል።
እንደ ኢትዮጵያ መንግሥት ገለጻ በዚህ ሳቢያ ሲካሄዱ የነበሩ ድርድሮች ግብፅ ወይም ሱዳን በሚያነሷቸው ጥያቄዎችና ተቃውሞዎች ምክንያት ውጤት ሳያስገኙ ቀርተዋል። በተጨማሪም የግድቡ ጉዳይ አስከ ፀጥታው ምክር ቤት ድረስ እንዲሄድ ለማድረግ ችለዋል።
ስለዚህም ኢትዮጵያና ሱዳን ካላቸው ረዥም የጋራ ድንበር በተጨማሪ ግንባታው እየተጠናቀቀ ሥራ ሊጀምር በተቃረበው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ መፍትሔ የሚፈልጉለት ነገር ነው።
ተቀማጭነታቸው ለንደን የሆነው የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አብዱራህማን ሰይድ እንደሚሉት ሱዳን በጄነራል ቡርሐን በሚመራ ወታደራዊ መንግሥት እጅ ከገባች የድንበርም የሆነ የሕዳሴው ግድብ ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ የማለቁ ነገር የጠበበይሆናል።

የሱዳንና የግብፅ ጦር
በሱዳን የሽግግር መንግሥት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የያዘው የሱዳን ጦር ኃይል ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ አጠቃላይ ፖለቲካዊ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ነበረው።
ይህ አካል ከኢትዮጵያ ጋር በማያስማማው የድንበር አካባቢ ተሰማርቶ አወዛጋቢ ቦታዎች ከመቆጣጠሩ ባሻገር ከግብፅ አቻው ጋር ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ የቀረበ ግንኙነት ለመመስረት ችሏል።
በዚህም የሁለቱ አገራት ሠራዊት የጦር ልምምድ ከማድረግ ባሻገር አስፈላጊ ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ በኩል ስጋት እንዲፈጠር በማድረግ በአካባቢው ያለውን ውጥረት ያብሰዋል።
የአማጺያንና ወታደራዊ እንቅስቃሴ
በሰሜን ኢትዮጵያ ካለው ጦርነትና በምዕራብ ኢትዮጵያ ከሚገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ የደኅንነት ስጋቶች እንዳሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።
በይፋ ከሱዳን በኩል ድጋፍ ያገኛሉ ባይሉም የኢትዮጵያ ወታደራዊ ባለሥልጣንት ከሱዳን በኩል ድንበር አቋርጠው ለመግባት የሚሞክሩ ታጣቂ ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰዳቸውን በተለያዩ ጊዜያት ሲገልጹ ቆይተዋል።
ይህም ኢትዮጵያ በምዕራባዊ ድንበሯ በኩል ለሚፈጸሙ ጥቃቶችና የጥቃት ሙከራዎች በሱዳን በኩል መተላለፊያ እንዳገኙ ያመለክታል። ይህንንም አገራቱ ከወዲሁ መፍትሔ ካላበጁለት ለአለመግባባት የሚያበቃ የፀጥታ ስጋት ሊሆን መቻሉ አይቀርም።
የድንበር ጉዳይን በተመለከተ ቢሆን፣ ኢትዮጵያ የሱዳን ጦር ወደነበረበት ተመልሶ ሲካሄድ በነበረው ውይይት አማካኝነት መፍትሔ እንዲፈለግ ብትጠይቅም ሱዳን ግን በመሠረተ ልማት ግብታ ይዞታዋን እያጠናከረች ነው።
በተደጋጋሚ እንደተዘገበውም የሱዳን ጦር በኢትዮጵያ ኃይሎች ጥቃት እንደደረሰበት እንዲሁም በቅርቡ ኢትዮጵያ ሠራዊቷን በድንበር አካባቢ እያሰፈረች ነው የሚል ክስ ሲቀርብ ይሰማል። ይህ ደግሞ ሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ ያለውን ውጥረት ሊያባብሰው ይችላል።
ከሐምዶክ በኋላ
ከሐምዶክ ሥልጣን መልቀቅ በኋላ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንበር ማን እንደሚመጣ አስካሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ ጦር ኃይሉ የሱዳን መንግሥት ሥልጣንን ጠቅልሎ የሚይዝ ከሆነ በአገሪቱ ውስጥ ያለው ቀውስ የበለጠ ሊባባስ ይችላል።
እንዲሁም ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ግንኙነት ላይ የጦር ኃይሉ ምን አይነት መንገድ እንደሚከተል በትክክል ባይታወቅም፣ ከዚህ በፊት በነበሩት የድንበር፣ የሕዳሴው ግድብ እና ከግብፅ ጋር ባዳበረው ግንኙነት የተነሳ ያለው ሁኔታ ላይረግብ የሚችልበት ዕድል አለ።
የምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ተንታኙ አብዱራህማን እንደሚሉት በቀጣናው የተለያየ ፍላጎት ያላቸው አገራት ጥቅማቸውን ለማስከበር ሲሉ የሚችሉትን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ እንዳማይሉ ይጠቅሳሉ።
ይህም ጄነራል አል ቡርሐን በሥልጣን ላይ ለመቆየት በአካባቢውና በሌሎች አገራት ተጽእኖ ስር ሆነው ያልጠተበቁ እና ሰላምን የማያመጡ ውሳኔዎችን ሊሰጡ የሚችሉብት ዕድል እንዳለ ያስረዳሉ።
በአጠቃላይ ግን የአብደላ ሐምዶክ ከሥልጣን መልቀቅ የሱዳን ጦር ኃይልን ከመንግሥት ኃላፊነት ገለል እንዲል የማድረጉን ተስፋ ከማጨንገፉ በተጨማሪ በአካባቢው ሰላምና ደኅንነት ላይ ተጽእኖ ይናረዋል ብለዋል የፖለቲካ ተንታኙ።















