በጋምቢያው ምርጫ ሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት አዳማ ባሮው አሸንፊያለሁ አሉ

ፕሬዝደንት አዳማ ባሮው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝደንት አዳማ ባሮው

የጋምቢያው ፕሬዝዳንት አዳማ ባሮው በአገሪቱ የተካሄደውን አጠቃላይ ምርጫ አሸንፊያለሁ ሲሉ አዋጁ።

አዳማ ባሮው የጋምቢያ የረዥም ጊዜ መሪ ያህያ ጃሜህ ሳይወዳደሩ የቀሩበትን ምርጫ በቀላሉ በድጋሚ ማሸነፋቸውን አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንት ባሮው ከቅዳሜውን ምርጫ ድምጽ 53 በመቶ አካባቢ ያገኙ ሲሆን፣ የቅርብ ተቀናቃኛቸው የሆኑት ጠበቃ ኦሳኢኖ ዳርቦ 28 ከመቶውን ድምጽ አግኝተዋል። ዳርቦ እና ሌሎች ተቃዋሚ ዕጩዎች የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበሉ ቀደም ብለው አስታውቀው ነበር።

ምርጫው የጋምቢያን የዴሞክራሲ ሥርዓት የሚፈተንበት ነውም ተብሎለታል። ባለፈው ምርጫ ያህያ ጃሜህ በባሮው የተሸነፉ ሲሆን ውጤቱን ለመቀበል ፍቃደኛ ባለመሆናቸው በስደት ለመኖር መርጠዋል።

የጃሜህ የ22 ዓመታት የሥልጣን ዘመን በበርካታ የበደል ውንጀላዎች የታጀበ ሲሆን በቅርቡ ለአገሪቱ የእውነት አፈላላጊ ኮሚቴ ቃላቸው የሰጡ የዓይን እማኞች በያያ ጃሜህ አስተዳደር ወቅት በመንግሥት የሚደገፉ ግድያዎች ስለመኖራቸው እንዲሁም የኤድስ ታማሚዎች የማይፈውስ የውሸት ሕክምና እንዲወስዱ ይገደዳሉ ብለዋል።

ጃሜህ በውጭ አገር ቢሆንም ተጽእኖ ፈጣሪነታቸው እንደቀጠለ ነው። ከአገር ውጪ ሆነው በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ደጋፊዎቻቸው ለባሮው ድምጻቸውን እንዳይስጡ ሲወተውቱ ነበር።

አዳማ ባሮው የተሳካላቸው የሪልስቴት አልሚ ሲሆኑ በአንድ ወቅት ለንደን ውስጥ የጥበቃ ሠራተኛ እንደነበሩ ይነገራል። እ.ኤ.አ. 2017 ላይ በተደረገው ምርጫ ጃሜህን ማሸነፋቸው ግርምትን የፈጠረ ነበር።

የማሸነፋቸው ዜና ሲሰማም ደጋፊዎቻቸው በጎዳናዎች ላይ በመውጣት ደስታቸውን እየገለጹ ነው።

ባሮው በጋምቢያ ዋና ከተማ ባንጁል ባደረጉት የድል ንግግር በአገሪቱ የፖለቲካ አንጃዎች መካከል አንድነት እንዲኖር ጠይቀዋል።

"የእናንተ የፖለቲካ ልዩነት ምንም ይሁን ምን ሁሉም የጋምቢያ ተወላጆች የፖለቲካ እና ሌሎች ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን ትተን እንደ አንድ ሕዝብ በመሰባሰብ ለአገራችን እድገት እንድንረባረብ ጥሪዬን አቀርባለሁ" ብለዋል።

ጋምቢያ በአፍሪካ ከሚገኙ ትንሽ አገራት መካከል አንዷ ሰትሆን፤ 2.4 ሚሊዮን ሕዝብ ብቻ አላት።