ከቤተሰቦቻቸው ጋር መሣሪያ ደግነው ፎቶ የተነሱት የአሜሪካ ምክር ቤት አባል እየተተቹ ነው

የፎቶው ባለመብት, @REPTHOMASMASSIE
የአሜሪካ ኮንግረስ አባል የሆኑት ግለሰብ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መሣሪያ ደግነው ለገና የተነሱት ፎቶ ከሁሉም አቅጣጫ ትችት እንዲያስተናግዱ አድርጓቸዋል።
የኬንታኪ የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካይ የሆኑት ቶማስ ማሲ በትዊተር ገፃቸው የለጠፉት ይህ ፎቶ "መልካም ገና። ሳንታ እባክህ አሞን ይዘህ ና" የሚል ፅሑፍ የታከለበት ነው።
ይህ የኮንግረስ አባሉ ፎቶ ሰውዬው ከሁለቱም የአሜሪካ አውራ ፓርቲዎች ትችት እንዲዘንብባቸው አድርጓቸዋል።
ቢቢሲ የኮንግረስ አባሉን አስተያየት ለማካተት ጥረት እያደረገ ይገኛል።
ሰውዬው ፎቶውን ትዊተር ላይ ከሰቀሉ በኋላ ድጋፍ የሰጧቸውን ሰዎች 'ሪትዊት' በማድረግ ድምፃቸውን ሲያስተጋቡ የተቃወሟቸው ሰዎች ደግሞ ምላሽ ሲሲጡ ተስተውለዋል።
ቶማስ ፎቶውን የለጠፉት ሚሺጋን ውስጥ አንድ የ15 ዓመት ተማሪ የአባቱን ሽጉጥ ተጠቅሞ ትምህርት ቤት ውስጥ በከፈተው ተኩስ አራት ሕፃናት ሞተው ሰባት መቁሰላቸው ከተሰማ ከቀናት በኋላ ነው።
የተጠርጣሪው ወላጆች በሰው ልጅ ሞት እጃቸው አለበት፤ አደጋው ከመድረሱ በፊት ማስጠንቀቂያ አልሰጡም በሚል ቢከሰሱም ጥፋተኛ አይደለንም ብለዋል።
በጦር መሣሪያ ጉዳይ ለሁለት በተከፈለችው አሜሪካ መሰል አደጋዎች በየጊዜው ይከሰታሉ።
ከዚህ በፊት በነበሩ የትምህርት ቤት ተኩሶች ምክንያት ልጆቻቸውን ያጡ ወላጆች የኮንግረስ አባሉን ድርጊት በፅኑ ተቃውመውታል።
የፍሬድ ጋተንበርግ ሴት ልጅ ሃይሜ ከሶስት ዓመት በፊት ፓርክላንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ውስጥ በተከፈተ ተኩስ ነው ሕይወቷን ያጣችው።
ፍሬድ ከኮንግረስ አባሉ ፎቶ ሥር የልጁን ጉርድ ፎቶ እና የመቃብሯን ፎቶ ለጥፎ፤ "የቤተሰቦቻችንን ፎቶ እየለጠፍንም አይደል፤ ይሄ የኔ ቤተሰብ ፎቶ ነው። አንደኛው የልጄ ፎቶ ነው፤ ሌላኛው ደግሞ የመቃብሯ። ልጄን ያጣሁት በመሣሪያ ምክንያት ነው። በቅርቡ ተማሪዎችን የገደለው ተማሪም እንዲሁም እንዳንተ ቤተሰብ ከወላጆቹ ጋር መሣሪያ ይዞ ፎቶ ይነሳ ነበር" ሲል ፅፏል።
ሌላኛው ዮዋኪን የተሰኘው ልጁን በፓርክላንድ ትምህርት ቤት ተኩስ ሳቢያ ያጣው ማኔኤል ኦሊቨር የሰውየው ደርጊ ፍፁም ተቀባይነት የለውም ሲል ለሲኤንኤን ተናግሯል።
የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላትም ይህን የቶማስ ድርጊት በፅኑ አውግዘውታል።
የኢሊኖይ ግዛት የኮንግረሱ ሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አዳም ኪንዚንገር የፓርቲ አጋራቸውን ወቅሰዋል።
ይሁን እንጂ ሌሎች ትላልቅ ስም ያላቸው ወግ አጥባቂ የአሜሪካ ፖለቲከኞች ደግሞ ለሰውዬው ድጋፋቸውን አሳይተዋል።
የኮሎራዶ ተወካይ የሆኑትና የጦር መሣሪያ መብት ባለቤትነት መብት ተሟጋች የሆኑት ሎረን ቦበርት እንዲሁም ሌላኛው ሪፐብሊካን ሆዜ ካስቲሎ ለቶማስ ድጋፋቸውን ችረዋል።
ቶማስ ማሴ የኬንታኪ ተወካይ ሆነው ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረጡት በፈረንጆቹ 2012 ነበር። ሰውዬው 'ሰከንድ አሜንድመንት' በመባል የሚታወቀው የጦር መሣሪያ የመታጠቅ መብት ሕግ ቀንደኛ አቀንቃኝ ናቸው።
የጦር መሣሪያ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ በትምህርት ቤቶች የሚከሰተውን ግድያ አያቆመውም ብለውም ተከራክረዋል።
ባለፈው ሚያዚያ የጦር መሣሪያ የሚገዙ ሰዎች ዕድሜ ከ21 ወደ 18 ዝቅ ሊል ይገባል ብለውም ሞግተዋል።
በአሜሪካው ባለፈው ዓመት ብቻ 20 ሺህ ሰዎች በጦር መሣሪያ አመፅ ምክንያት ሞተዋል። ይህም ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ከታየው የላቀ ነው።












