ሲሪ ላንካዊው የነብዩ መሐመድን ስም አጠልሽቷል በሚል በደቦ ጥቃት መገደሉ ቁጣን ቀስቀሰ

በደቦ ጥቃት የተገደለው ሲሪ ላንካዊው የፋብሪካ ሠራተኛ ፕሪያንታ ዲያዋዳናግ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, በደቦ ጥቃት የተገደለው ሲሪ ላንካዊው የፋብሪካ ሠራተኛ ፕሪያንታ ዲያዋዳናግ

በፓኪስታን አንድ ግለሰብ የነብዩ መሐመድን ስም አጠልሽቷል በሚል በአሰቃቂ የደቦ ጥቃት ተገድሏል።

ሲሪ ላንካዊው ግለሰብ በአሰቃቂ የደቦ ጥቃት መገደሉን ተከትሎ በሲሪ ላንካ እና ፓኪስታን ቁጣን ቀስቅሷል።

ሲሪ ላንካዊው የፋብሪካ ሠራተኛ ፕሪያንታ ዲያዋዳናግ በፓኪስታን በድንጋይ ተወግሮ የተገደለው ዓርብ ዕለት ነበር።

የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካህን "ይህ ብሔራዊ የውርደታችን ዕለት ነው" ሲሉ ድርጊቱን አውግዘዋል።

አስከ አሁን በድርጊቱ ተሳትፈዋል የተባሉ ከመቶ ሰዎች በላይ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የሲሪ ሊናካዊው ሟች ቤተሰቦች በበኩላቸው ፍትሕን እንደሚሹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለቤቱ ኒሮሺ ዳሳናያኬ ሲሪ ሊንካ እና የፓኪስታን መንግሥት በጉዳዩ ዙርያ ሙሉ ምርመራ አድርጎ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለፍርድ እንዲያቀርብላት ጠይቃለች።

"ባለቤቴ ላይ የተፈጸመበትን አሰቃቂ ድርጊት በኢንተርኔት ተመልክቻለሁ፤ እኔና ሁለት ልጆቹ ፍትሕን እንሻለን" ብላለች ለቢቢሲ።

በግለሰቦች በተቀረጸው ቪዲዮ ባለቤቷን በድንጋይ ወግረው ከመግደል ባለፈ አስክሬኑ ላይ እሳት ለኩሰው ፎቶ አብረው ሲነሱ ይታያል።

ይህ የደቦ ጥቃት ሊፈጸም የቻለው ሲሪላንካዊው የፋብሪካ ሠራተኛ የነብዩ መሐመድ ስም ያለበትን ፖስተር ቀዳዶ ጥሏል በሚል ወሬ ከተዛመተ በኋላ ነበር።

ነፍሱን ለማዳን የሞከሩ የእሱ ባልደረቦች ግን ግለሰቡ ፖስተሮችን ያነሳው ሕንጻው ለዕድሳት እየተዘጋጀ ስለነበረ ብቻ ነው።

"ውሸት ነው፤ ፖስተር አልቀደደም፣ ባለቤቴ ሙስሊም አገር ለ11 ዓመት ሠርቷል። ይህን ሊያደርግ አይችልም፤ ሕጉን ያውቃል፤ ባለቤቴ ንጹህ ነው" ብላለች የሟች ባለቤት።

የሟች የአስክሬን ቅሪት ዛሬ ሲሪ ላንካ ይገባል። ይህን ተከትሎ በኮሎምቦ ሌላ ተቃውሞ ሊቀሰቀስ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።

የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ይህን አሳፋሪ ተግባር የፈጸሙ ጥፋተኞች ለሕግ እንደሚቀርቡ ቃል ገብተዋል።