ሩሲያ በዩክሬን ላይ 'መጠነ ሰፊ ጥቃት ልትፈፅም' እንደምትችል አሜሪካ አስታወቀች

ቭላድሚር ፑቲንና ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን ከፍተኛ ውጥረት የነገሰባት ዩክሬንን በተመለከተ በመጪው ማክሰኞ በቪዲዮ እንደሚነጋገሩ ዋይት ሃውስ አስታውቋል።

ከሰሞኑ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ሩሲያ በዩክሬን ላይ "መጠነ ሰፊ ጥቃት ለመፈጸም" እቅድ እንዳወጣች የሚያሳይ ማስረጃ አገራቸው እንዳገኘች ገልጸዋል።

ነገር ግን ፕሬዚዳንት ፑቲን ዩክሬንን ለመውረር የመጨረሻ ውሳኔ ላይ መድረሳቸው ግልጽ አይደለም ሲሉም አክለዋል።

ሩሲያ በበኩሏ የማጥቃትም ሆነ የመውረር ሃሳብን ውድቅ አድርጋ ዩክሬን ሰራዊቷን በከፍተኛ ሁኔታ እያጠናከረች ነው ስትል ከሳታለች።

የዋይት ሀውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ጄን ፓሳኪ ቅዳሜ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ ፕሬዚዳንት ባይደን "ሩሲያንና ዩክሬንን በሚያዋስነው ድንበር ላይ ሩሲያ የምታደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ አሜሪካ ያላትን ስጋት እንዲሁም አሜሪካ ለዩክሬን ሉዓላዊነትና ግዛታዊ አንድነት የምታደርገውን ድጋፍ" በተመለከተ ከሩሲያ ፕሬዚዳንት ጋር በሚያደርጉት የስልክ ልውውጥ ያነሳሉ ብለዋል።

ዩክሬን በበኩሏ ሃገራቱ በሚዋሰኑበት ድንበር ላይ የታጠቁ ተሽከርካሪዎች፣ የኤሌክትሮኒክ የጦር መሳሪያዎችን እና 94 ሺህ ወታደሮችን ሩሲያ ማሰማራቷን ገልጻለች።

በአውሮፓውያኑ 2014 ሩሲያ የክሪሚያን ግዛት ከዩክሬን ከወሰደች በኋላ ከፍተኛ የጦር መሳሪያና ወታደር በጋራ ድንበሩ ላይ ስታሰማራ የመጀመሪያው ነው።

የዩክሬን የመከላከያ ሚኒስትር ኦሌክሲይ ሬዝኒኮቭ የደህንነት ዘገባዎችን በመጥቀስ ሩሲያ በጥር ወር መጨረሻ ወታደራዊ ጥቃትን ልትፈፅም እንደምትችል ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ያለው የሩስያ ጦር እንቅስቃሴ በሩሲያ እና በአሜሪካ መካከል ቀደም ሲል ሻክሮ የነበረውን ግንኙነት የበለጠ ውጥረት እንዲነግስ አድርጎታል።

በያዝነው ሳምንት አርብ ዕለት ፕሬዚዳንት ባይደን "በርካቶችን እያስጨነቀ ያለውንና ሊያደርግ ይችላል ብለው እየጠበቁት" ያለውን ጉዳይ "አስቸጋሪ፣ በጣም ፈታኝ እንዲሆን አደርገዋለሁ" ሲሉ ፑቲንን አስጠንቅቀዋል።

ሩሲያ ጠንከር ያለ እርምጃ ከወሰደች አሜሪካ እና የአውሮፓ አጋሮቿ ማዕቀብ ለመጣል ተወያይተዋል።

ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ባትሆንም ከህብረቱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላት እና የአሜሪካ ጄቭሊን ፀረ ታንክ ሚሳኤሎችን ጨምሮ ከምዕራባውያን በርካታ የጦር መሳሪያዎች ድጋፎችን ታገኛለች።