በኬንያ ዘማሪዎችን የጫነ አውቶብስ ወንዝ ውስጥ ገብቶ የ23 ሰዎችን ሕይወት ቀጠፈ

በወንዙ ውስጥ የገባው አውቶብስ

የፎቶው ባለመብት, Citizen TV Kenya

በኬንያ ወደ ሰርግ ሲጓዝ የነበረ አውቶብስ በጎርፍ በተጥለቀቀለቀ ወንዝ ውስጥ በመግባቱ በትንሹ 23 ሰዎች ሰጥመው ሞተዋል ተባለ።

ከኬንያ መዲና ናይሮቢ በስተምስራቅ 200 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የኢንዚዩ ወንዝ ድልድይ ላይ የአውቶብስ አሽከርካሪው በፍጥነት የሚፈሰውን ውሃ ለመሻገር መሞከሩን ተከትሎ አውቶብሱ በውሃው መወሰዱንና ከዕይታ መጥፋቱን የወጣው የቪዲዮ ምስል ያሳያል።

አውቶብሱ የቤተ ክርስቲያን መዘምራን አባላትን አሳፍሮ ነበር።

ከሟቾቹ ውስጥ አራቱ ህጻናት ሲሆኑ በትንሹ 12 ሰዎች ደግሞ መትረፋቸውን የአካባቢው ዘገባዎች አመልክተዋል።

ይሁን እንጂ በወቅቱ ምን ያህል ሰዎች በአውቶብስ ውስጥ ተሳፍረው እንደነበር ግልጽ አይደለም።

አሽከርካሪው በምዊንጊ ኪቱይ ግዛት ያለውን መንገድ እንዲሁም በወንዙ ላይ ያለውን ድልድይ እንደማያውቀው የአገሪቱ ጋዜጣ ስታንዳርድ ዘግቧል።

የኪቱይ በጎ አድራጎት ድርጅት አስተዳዳሪ ንጊሉ በበኩላቸው "አስፈሪው" አደጋ የደረሰው ቅዳሜ ማለዳ ላይ ነው ብለዋል።

አክለውም እስካሁን ባለው 23 አስከሬኖች መገኘታቸውን ነገር ግን ሌሎች አሁንም በአውቶቡስ ውስጥ እንደተጣበቁ እና የማዳን ስራዎችም እሁድ እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

ድርቅ በተከሰተባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ጨምሮ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የኬንያ አካባቢዎች ያልተለመደ ከባድ ዝናብ እየጣለ ነው።

ከድርቅ ጋር በተያያዘ የቤትና የዱር እንስሳት በግጦሽ እጥረት ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።