አሜሪካና አጋሮቿ ታሊባን በቀድሞ የአፍጋኒስታን የጸጥታ ኃይሎች ላይ የሚፈጽመውን ግድያ እንዲያቆም አሳሰቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ እና አጋር አገራት ታሊባን የቀድሞ የአፍጋኒስታን የጸጥታ ኃይሎች አባላት ላይ ያነጣጠረ ግድያ እንዲያቆም አሳሰቡ።
አገራቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ ፤ 22ቱ አገራት እስላማዊው አገዛዝ በቀድሞ የመንግሥት እና የጸጥታ ሠራተኞች ላይ ጉዳት ላለማድረስ የገባውን ቃል እንዲያከብር ጠይቀዋል።
መግለጫው " ጅምላ ግድያ ፤ ጠለፋ እና እስርን በተመለከተ የሚወጡ ሪፖርቶች አሳስቦናል" ብሏል።
አገራቱ መግለጫውን ያወጡት በእስላማዊው አገዛዝ የተፈፀሙ ግድያዎችና እና አፈናዎችን የሚያመለክት ሪፖርት መውጣቱን ተከትሎ ነው።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በሂዩማን ራይትስ ዎች የወጣው ሪፖርት ታሊባን ከአራት ወር በፊት አገሪቷን ከተቆጣጠረ ጀምሮ ከ100 በላይ የቀድሞ የአፍጋኒስታን መንግሥት ባለሥልጣናት መገደላቸውንና መጠለፋቸውን ገልጿል።
ሪፖርቱ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነሐሴ 15 እና በጥቅምት 31 ባሉት ጊዜያት ብቻ በታሊባን የተያዙ ወይም እጃቸውን የሰጡ 47 የቀድሞ የአፍጋኒስታን የጸጥታ ኃይሎች አባላት መገደላቸውን ሰንዷል።
እስላማዊ አገዛዙ በቀድሞ የመንግሥት ሠራተኞች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያደርስ ቢገልጽም ግድያ መፈፀሙን ሪፖርቱ አመልክቷል።
አገራቱ ያወጡት አጭር መግለጫ የወጣው በአሜሪካ ሲሆን ዩናይትድ ኪንግደም፣ የአውሮፓ ሕብረት እና ሌሎች 19 አገራት ፈርመውበታል።
አገራቱ በሪፖርቱ ግኝቶች ላይ ያላቸውን ጥልቅ ስጋት በመግለጽ ሁሉም ተፈጸመ የተባሉት ጅምላ ግድያ እና ጠለፋዎች ላይ ምርመራ እንዲደረግ ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል።
መግለጫው "ታሊባንን በድርጊታቸው መመዘን እንቀጥላለን" ሲል ተጠቃሏል።
ታሊባኖች ቃል ከገቡት በሚጻረር መልኩ የፈጸሟቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። ከዚህ ቀደምም የወጡ የሰብዓዊ መብት ሪፖርቶች የተፈጸሙ ግድያዎችን አጋልጠዋል።
ነሐሴ ወር ላይ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የወጣ ሪፖርት 300 የታሊባን ተዋጊዎች ነሐሴ 30 የቀድሞ የመንግሥት ወታደሮች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደሚኖሩበት ዳሃኒ ኩል መንደር አቅራቢያ ወደሚገኝ አካባቢ መጓዛቸውን አመልክቷል።
ሪፖርቱ እንዳለው ተዋጊዎቹ ዘጠኝ ወታደሮች እጃቸውን ከሰጡ በኋላ የተገደሉ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ በተኩሱ ተገድለዋል።
የ17 ዓመት ታዳጊን ጨምሮ ሌሎች ሁለት ሰላማዊ ሰዎችም በውጊያው መገደላቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።












