ክሪስ ኩሞ የተባለ የሲኤንኤን ጋዜጠኛ ባለስልጣን ወንድሙን በመርዳቱ ከስራው ተባረረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካዊው የቴሌቪዥን አቅራቢ ክሪስ ኩሞ የቀድሞ የኒውዮርክ አስተዳዳሪ የነበሩት ወንድሙ በቀረበባቸው ወሲባዊ ትንኮሳ ውንጀላዎች ላይ በሰጠው እርዳታ ምክንያት መስሪያ ቤቱ ሲኤንኤን ከስራ አባሮታል።
ሲኤንኤን እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ክሪስ ኩሞ በታላቅ ወንድሙ ውንጀላ ላይ የነበረው ተሳትፎ ምን ያህል እንደሆነ ተጨማሪ መረጃ መውጣቱን ተከትሎም እንደሆነ አስታውቋል።
አንድሪው ኩሞ አቃብያነ ህግ በሰራተኞች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ፈፅመዋል የሚል ክስ ካቀረቡ በኋላ ከኃላፊነታቸው የለቀቁት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ነበር።
የ51 ዓመቱ ጋዜጠኛ ክሪስ ኩሞ ባወጣው መግለጫ የሲኤንኤን ውሳኔ እንዳሳዘነውና "በመስሪያ ቤቱ የነበረኝ ጊዜ በዚህ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አልፈልግም ነበር" ብሏል።
ጋዜጠኛው ከአውሮፓውያኑ 2013 በሲኤንኤን ሲሰራ የቆየ ሲሆን ከታወቁ የዜና አቅራቢዎች መካከልም አንዱ ለመሆን ችሏል። በባለፈው ዓመት በነበረው የአሜሪካ ምርጫም ላይ የሲኤንኤን ዘገባን ከመሩት መካከል አንዱ ነው።
የሲኤንኤን መግለጫ እንዳስታወቀው ክሪስ ኩሞ ፖለቲከኛ ወንድሙ ወሲባዊ ትንኮሳ ውንጀላ ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት ላይ አስተዋፅኦው ምን ይመስላል የሚለውን ለማጣራት "ስመ ጥር የህግ ተቋም" ቀጥሯል።
ነገር ግን መስሪያ ቤቱ እንዳለው ይህ ግምገማ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ሲኤንኤን አዲስ መረጃ በማግኘቱ የጋዜጠኛውን ኮንትራት እንዲቋረጥና ከስራም እንዲባረር የሚያስወስን ሆኖ አግኝቶቶታል ብሏል።
ክሪስ ኩሞ ወንድሙ ከገቡበት ቅሌት ለማውጣት በጀርባ በኩል ሆኖ ጥረት አድርጓል የሚለው መረጃ ከተሰማበት በኋላ ከስራ ታግዶ ነበር።
በወቅቱም ሲኤንኤን "ክሪስ ኩሞ ያለበትን ልዩ ቦታ እንደሚያጤነውና ጋዜጠኛው ቤተሰቡን ቢያስቀድምና በሁለተኛ ደረጃም ስራውን ቢያስከትልም እንደሚረዳ " ገልፆ ነገር ግን ለፖለቲከኛው ወንድሙ የሰጠው ምክር የጋዜጠኝነት ስነ ምግባርን መጣስ ነው በሚል እንደሆነ አስረድቷል።
በኒውዮርክ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሌቲሺያ ጀምስ በኩል ሰኞ ዕለት የወጡት ሰነዶች እንደሚያሳዩት ጋዜጠኛው ወንድሙን ለማትረፍ በሚል ትልቅ ሚና እንደተጫወተና የወንድሙ መስሪያ ቤት ሰራተኞችም ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳረፍ ያለማቋረጥ ይገፋፋም እንደነበር ነው።
"እኔን ልታምኑኝ ይገባል" ሲል ለወንድሙ ፀሐፊ ሜሊሳ ዴሮሳን የስልክ መልዕክት የላከ ሲሆን አክሎም "የማንወጣውን ስህተት እየሰራን ነው" ብሏል።
በተጨማሪም ሌሎች የአሜሪካ ሚዲያዎችን ለማነጋገርና ወደፊት የሚመጡ ወሲባዊ ትንኮሳ ክሶችንም እንደሚከታተል ቃል ገብቶ ነበር ተብሏል።
ለሲኤንኤን ሰራተኞች በተፃፈና ኒውዮርክ ታይምስ በተመለከተው ደብዳቤ ላይ የሲኤንኤን ፕሬዝዳንት ጄፍ ዙከር"እነዚህ ውሳኔዎች ቀላል እንዳልሆኑ እና ብዙ ውስብስብ ነገሮችም አሉ" ብለዋል።












